የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ እና ኢትዮጵያ | አፍሪቃ | DW | 27.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ እና ኢትዮጵያ

ሱዳን ሽግግር መንግሥቱ በወታደራዊው ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋሉ ሰላሟን አናግቶታል። ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ያሻግራል የሚል ተስፋ የተጣለበት ሲቪል ፖለቲከኞች የተካተቱበትን መንግሥት ያስወገደውን የጦር ኃይሉን ርምጃ የሚቃወመው የሕዝቡ አድማ ዛሬም ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:42

የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ

መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄደው የሱዳን ጦር ኃይል ሲቪል አስተዳደሩን ከመበተኑ አልፎ አንዳንዶቹን ማሰሩ ነው የሚነገረው። የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድ በምርጫ የሚሰየም መንግሥት እንደሚኖር ቃል ቢገቡም ከበስተጀርባቸው ግብጽና አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ጠንካራ ድጋፍ በመኖሩ ያሉትን እውን መሆኑ እያጠናየቀ ነው። ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር በአንድ ወገን በድንበር ፤ በሌላው ደግሞ ከኅዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ የምትወዛገበው ሱዳን ውስጣዊ ፖለቲካ ቀውስ መባባስ በአንድም በሌላም ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የሱዳን ይዞታ አሁን ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ እንደማይታወቅ ያመለከቱት የፖለቲካ ሣይንስ ምሁሩ ዶክተር አስናቀ ከፍአለ  መረጋጋቷ ለኢትዮጵያ እንደሚበጅ አጽንኦት ይሰጣሉ።

Putsch im Sudan General Abdel Fattah al-Burhan

ጀነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን

«ሰላማዊ ላልሆነች ሱዳን ለኢትዮጵያ ጥቅም አታመጣም፤ ሰላማዊ፣ የተረጋጋች፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነች ሱዳን መኖር ለኢትዮጵያ ትርፉ ከጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛል። ሱዳን ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትርምስ አሁን ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ ማወቅ አይቻልም።»

ሱዳን በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እጇን ሳታስገባ እንደማትቀር ለሚጠረጥሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ቻላቸው ታረቀኝ አስተያየት ከዚህ ይለያል።

«እንደዚህ አይነት ነገሮች፣ በእርግጥ ለሌሎች ክፉ መመኘት ጥሩ ባይሆንም አንዳንዴም መልካም ሁኔታ ሊኖራቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ።»

እንደእሳቸው የኢትዮጵያን ምዕራባዊ ድንበር ጥሳ የገባችው ሱዳን የውስጥ ሰላሟን አግኝታ መንግሥቷ መደላደል ከቻለም ትርምሱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲባባስ ከማድረግ ወደኋላ አትልም። ከዚህም ሌላ መፈንቅለ በሱዳን መንግሥት ያካሄዱት የጦር ኃይሎች መሪ ጀነራል አብደል ፈታህ አልሁርሃን ግብጽ ውስጥ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ወደሥልጣን የመጡት የፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ድጋፍ እንዳላቸውም አስታውሰዋል። ከኅዳሴ ግድቡ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ጋር እሰጥ አገባ የገቡት ሁለቱ ሃገራት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አዲስ አበባን ለማዳከም መንገድ መሻታቸው እንደማይቀርም አጽንኦት ሰጥተዋል። በምሥራቅ አፍሪቃ በውስጣዊ ችግር እየታመሰች የምትገኘው ሱዳን ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ አንድ ዓመት ሊደፍን በተቃረበው ትግራይ ተጀምሮ  ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ባለው የዜጎች ግድያ እና፣ መፈናቀል፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያም በሚሰማው የጎሳ ግጭት እና የዜጎች መፈናቀል አልተረጋጋችም።

Sudan | Abdullah Hamduk

አብደላ ሀምዶክ

በአፍሪቃው ቀንድ የሃገራቱ ውስጣዊ ሰላም አለመረጋገጡ ለቃጣናው አጠቃላይ ስጋት እንደመሆኑ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት በእንግሊዘኛው ምህጻር ኢጋድ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ላይ እንደሞከረው በዚህ ረገድ ሊጫወት የሚችለው ሚና ይኖር ይሆን? ዶክተር አስናቀ ከኢጋር ይልቅ የአፍሪቃ ሕብረት የተሻለ ሚና ሊኖረው ይችላል ነው የሚሉት።

«እኔ ከኢጋድ ይልቅ የአፍሪቃ ሕብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክርቤቱ ነው ነገሩን እየተከታተለ ያለው። ኢጋድ ሶማሊያ ላይ ገምቢ ሚና ተጫውቶ ነበር፤ በደቡብ ሱዳን ጉዳዮች ላይ እንዲሁ፤ ኢትዮጵያን እና ሱዳንን በመሳሰሉ ከፍ ባሉ የቀጣናው ሃገራት ላይ ያለው ሚና ያንያህል ጎልቶ ይወጣል ብዬ አልገምትም።»

የአፍሪቃውን ቀንድ ሃገራት ከማረጋጋት አኳያ ለአቶ ቻላቸው የሁለቱም የአፍሪቃ ተቋማት አቅም ጥያቄ ላይ የወደቀ ነው።

«በመሠረቱ ኢጋድ ብዙም አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፤ በእርግጥ ጉዳዩ ይመለከተዋል፤ግን ኢጋድ የሚባለው ጠንካራ የሆነ ስብስብ አይደለም። ኢጋድ ይቅርና የአፍሪቃ ሕብረትም እኮ በጣም ጠንካራ የሚባል ድርጅት አይደለም እስካሁን ድረስ።»

በእሳቸው እይታም ለአፍሪቃውያኑ ሃገራት ውሳጣዊ የፖለቲካ ውጥረትና አለመረጋጋት የምዕራባውያን ሃገራትም ሚና የጎላ ነው።  እስካሁን ከኢጋድ የተሰማ ነገር ባይኖርም የአፍሪቃ ሕብረት የሲቪል አስተዳደሩ ወደ ቦታው እስካልተመለሰ ድረስ ሱዳንን ከአባልነት መሰረዙን ዛሬ አስታውቋል። የዓለም ባንክ ደግሞ ለሱዳን የሚሰጠውን ርዳታ ለጊዜው ማቋረጡን ዛሬ ገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ 

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic