የሱዳን ፕሬዝዳንትና «አይ ሲ ሲ» | አፍሪቃ | DW | 19.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን ፕሬዝዳንትና «አይ ሲ ሲ»

የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦማር ኧል በሽር በዳርፉር በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን ፈፅመዋል በሚል የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ከቆረጠባቸዉ ይሄዉ ከስምንት ዓመት በላይ ሆነ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:17

ኧል በሽርና «አይ ሲ ሲ»

ፕሬዝደንቱ በሌሎች አፍሪቃ፣ እስያ ወይም መካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት ጉዞ ሲያደርጉ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቱን አስረዉ እንዲያስረክቡ ይጠይቃል። ይሁን እንጅ አንዱም እስካሁን ፍቃደኛ ኧልሆኑም። ለዚህም ነዉ የፕሬዝደንት ኦማር ኧል በሽር እና የፍርድ ቤቱ ግንኙነት ጉዳይ የድመትና አይጥ ጨዋታ የመሰለዉ።


ሰሞኑንም ፕሬዝደንቱ በሩዋንዳዉ የ27ኛዉ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ሲሳተፉ ፍርድ ቤቱ አስተናጋጅዋ ሀገር እንድታስራቸዉ ጠይቆ ነበር። የሩዋንዳ መንግሥት በሽርን እንደማያስር፣ ፍርድ ቤቱ የተቋቋመበት የሮሙ ዉልም ፈራሚ አባል ስላልሆነች ምንም ግዴታ እንዴሌለባት ጠቅሷል። ፕሬዝደንቱ የሚሄዱባቸዉ ሃገራት የ«ICC» ፈራሚ አባል ባይሆኑም ለምን ከለላ እንደሚሰጡት ፕሪቶርያ የሚገኘዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም የፕሮግራም ኃላፊ እና ከፍተኛ ተመራማር የሆኑትን ኦትሊያ አናሞንጋኒዜን ጠይቄ ነበር፣ «እንግዲህ አንዳንድ ሀገሮች የሚከራከሩት እሳቸዉ የአገር መሪ በመሆናቸዉ ከለላ ሊሰጣቸዉ ይገባል በሚል ነዉ። ሌሎች ደግሞ ለሰላም ሲባል መታሰር የለባቸዉም ባዮች ናቸዉ። በተመሳሳይ ደግሞ አንዳንዶች ምንም መከራከሪያ ማንሳት አይፈልጉም፤ በደፈናዉ ፕሬዝዳንቱ ከለላ ሊደረግላቸዉ ይገባቸዋል ይላሉ። ይሁን እንጅ ፕሬዝዳንቱ በብዙ ምክንያቶች ከፍትህ ማምለጥ ቢችሉም፣ በመጨረሻዉ ቀን ግን በተፈፀመዉ ወንጀል ተጎጅ የሆኑት ሰዎች ናቸዉ በዚህ ሁኔታ የኋላ ኋላ የሚጎዱት። ስለዚህ ስለ በሽር በታሰበበት ወይም እሳቸዉ ላይ ባተኮሩ ቁጥር፣ ስለተጎጅዎቹ እና እሳቸዉ ስለፈጸሙባቸዉ ወንጀሎች የሚሰጠዉ ትኩረት ዝቅ ሊል ችሏል።»


ኧል በሽር እስካሁን በተጠረጠሩበት ጥፋት ወደ ፍትህ አለመቅረባቸዉ ለሌሎች የአፍሪቃ መርዎች ጥሩ ማሳያ ሊሆንላቸዉ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። በተቃራኒዉ ሚዛናዊ አይደለም በሚሉት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መዳኘቱን የማይፈልጉት አፍሪቃዉያን የራሳቸዉን ፍርድ ቤት በአህጉሪቱ ማቋቋም እንደሚሻላቸዉ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። ኦትሊያ ይህን አስመልክተዉ ሲናገሩ፣ «ኧል በሽር ለሌላ የአፍርቃ መሪዎች በምሳሌነት እንደማይወሰዱ ተስፋ እናደርጋለን። ግን ባሁኑ ሰዓት የአፍሪቃ አህጉር ሁኔታን ስንመለከት አፍርቃ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከምትዳኝ ይልቅ የራሷ የሆነ ፍርድ ቢኖራት ለአፍሪቃ መሪዎች መሸሸጊያ ይሆናል የሚል ስጋት አለ። እናም አስቸጋሪ የሆነዉ ነገር አንዳንድ መሪዎች ይህን ዕድል ተጠቅመዉ እስከሚፈልጉ ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ያስችላቸዋል። ስልጣን ላይ መቆየት ኧል በሽር እንዳይታሰሩ አድርጓል። ይህን ነዉ እኛ በመፋለም ላይ ያለነዉ። የምንታገለዉ ለሰላም፣ ለፍትህ እና ደህንነት ብቻ ሳይሆን፤ ለዴሞክራሲ መዳበር እንዲሁም ሰዎች ከክስ ለማምለጥ ስልጣን ላይ መቆየት መምረጣቸዉንም ጭምር ነዉ።»


ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አፍሪቃ መሪዎች ላይ ለምን አነጣጠር በማለት የሚተቹም አሉ። በዶቼ ቬለ ድረገጽ ላይ አስተያየታቸዉን ከሰጡን መካከል «ሲጀመር ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አለ ወይ?» ብለዉ በመጠየቅ ፍርድ ቤቱ የምዕራብ ኃያላን ሃገራት መጠቀሚያ እንጂ ለፍትህ የቆመ አይደልም በማለት የወቀሱም አሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic