የሱዳን አማፅያንና የመንግሥቱ ጦር ለዳግም ጦርነት? | አፍሪቃ | DW | 07.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን አማፅያንና የመንግሥቱ ጦር ለዳግም ጦርነት?

በሱዳን ግዛት ድንበር ላይ የሚዋጉት የመንግሥት ኃይላትና አማፅያን ለዉግያ ዝግጅት ላይ ነን ሲሉ ማስታወቃቸዉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ዘገበ።

በሱዳን፤ ዳርፉር፣ ብሉ ናይልና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች ውስጥ እየተካሄደ ያለዉን ግጭት ለመግታት ባለፈዉ ወር የአፍሪቃ ሕብረት አዲስ አበባ ላይ የተቀመጠበት ድርድር ያለምንም መፍትሄ መጠናቀቁ ይታወቃል። አደራዳሪዎች በምዕራብ ዳርፉር ግዛት ከጎርጎርዮሳዊዉ 2003 ዓ,ም ጀምሮ የሚንቀሳቀሱት አማጽያን፤ እንዲሁም ከሱዳን መንግሥት ጋር ከጎርጎርዮሳዊ 2011 ዓ,ም ጀምሮ ውጊያ የሚያካሂደው በደቡባዊ ብሉናይል ግዛትና በደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች የሚገኘው የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጭ ንቅናቄ ሰሜን « SPLM-N » የተኩስ አቁም ሥምምነት እንደሚደርሱ እና ወዳካባቢው የርዳታ ቁሳቁስ እንደሚገባ ተስፋ አድርገው ነበር።

በአካባቢዉ ላይ የዝናብ ወራት ተጠናቆ ደረቃማዉ ወራት እየገባና የመጓጓዣ መንገዱ አመቺ በመሆኑ በሁለቱም ወገን ያሉት ወገኖች ጦርነቱን እንደሚጀምሩ ነዉ የተመለከተዉ።

በኮርዶፋንና በብሉናይል ግዛት የሚገኙት የሱዳን ሕዝብ ነጻ አዉጭ ንቅናቄ- ሰሜን ተጠሪ አርኑ ሎዲ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት «እራሳችን ለመከላከል በመዘጋጀት ላይ ነን፤ ጦራችን፤ በተሟላ ዝግጅትና ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ ይገኛል »። የሱዳን ጦር ሠራዊት በበኩሉ በዳርፉር፤ በደቡብ ኮርዶፋንና በብሉናይል ግዛቶች ላይ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ መናገሩ ተዘግቦአል። የሱዳን ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮነሪል አህመድ ካሊፍ ኧል-ሻሚ ለዜና ወኪሉ እንደተናገሩት « እየተዘጋጁ እንደሆን እናዉቃለን እኛም እየተዘጋጀን ነዉ።»።

ባለፈዉ መስከረም ወር የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልባሽር የሁለት ወራት የተኩስ አቁም እንዲደረግና ካርቱም ላይ ብሔራዊ ዉይይት እንዲደረግ ጥሪ አድርገዉ ነበር። በዚህ ወራት ዉስጥ አካባቢዉ ላይ ከፍተኛ ዝናብ ስለሚጥል ለመጓጓዝ አመቺ ባለመሆኑ እንደነበር ተዘግቦአል። የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጭ ንቅናቄ ሰሜን « SPLM-N » በአንጻሩ በተኩስ አቁም ወራቶች ወቅት የካርቱሙ መንግሥት የአየር ድብደባ አድርሶአል ሲል ይከሳል።የአል በሽር መንግሥት በዳርፉር ለ12 ዓመታት ጦርነት ሲያካሂድ ቆይቷል ። የዳርፉር አማፅያን ትግል የጀመሩት ተገለናል ሲሉ ነው።

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ