የሱዳን ቀዉስ የዐብይ ሚና | አፍሪቃ | DW | 10.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን ቀዉስ የዐብይ ሚና

ፕሬዝደንት አል-በሽር ደቡብ ሱዳን ላይ ሲዋጉ በማዕቀብ የቀጧቸዉ ዳርፉር ላይ ሲዋጉ በፍርድ ቤት የወነጀሏቸዉ የለንደን-ዋሽግተን መንግሥታት የሱዳን ሕዝብ ባደባባይ ሲረሸን ከዕለታዊ «መግለጫ» ባለፍ ምንም አለማለታቸዉ በርግጥ ያስተዛዝብ ይሆናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:29

የሱዳን ቀዉስ፣የዐብይ ሚና

የሱዳን ወታደራዊ ሁንታ ሠላማዊ ተቃዋሚዎቹን መግደል፣ማቁሰል፣ ማሰሩን የለንደን-ዋሽግተን ኃያላን ያወግዛሉ።የሪያድ፣ ካይሮዎችን ፍላጎት ከማስከበር ባለፍ ጥርስ-ጥፍር አልባዉ የዓረብ ሊግ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስን «አሳሳቢ» ይለዋል።የአፍሪቃ ሕብረት በማዕቀብ ያስጠነቅቃል።የኢትዮጵያ መሪ ለሽምግልና አንድ ሁለት እንዳሉ ነዉ።ሱዳኖች ከካርቱም እስከ ለንደን ዋሽግተን እንዳደሙ፣ ባደባባይ እንደጮሁ ነዉ።ጦር ኃይሉ የገደለዉ ተቃዋሚን መቁጠር-መቅበሩ ቀጥሏል።118 ዛሬ።ተቀናቃኞች  ከመደራደር መወያየት ይልቅ፣ ጄኔራሎቹ ለተጨማሪ የኃይል ርምጃ፣ ተቃዋሚዎቻቸዉ ለሕዝባዊ አመፅና አድማ እየዛቱ ነዉ።እስከ መቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ከብሪታንያና ከግብፅ ጥምር ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ከጥር 1956 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ሶስት ጉሉሕ ፖለቲካዊ ታሪክ አላት።ጦርነት፣መፈንቅለ መንግስት እና ሕዝባዊ አመፅ።ሱዳን።ከጥር 1956 እስከ ሚያዚያ 2019 ድረስ «የሉዓላዊ ምክር ቤት» ከተባለዉ ስብስብ ዉጪ ሐገሪቱን ከገዙት ስድት መሪዎች አራቱ የጦር መኮንኖች ናቸዉ።

ከሁለቱ ሲቢል መሪዎች አንዱ ለአንድ ወር (በጊዚያዊነት) ሁለተኛዉ ለሶስት ዓመት፣ምክር ቤቶቹ ባጠቃላይ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ከመምራታቸዉ በስተቀር የሱዳንን ፖለቲካ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ የዘወሩት የጦር መኮንኖች ናቸዉ።እንደ ፖለቲከኛ ቤተ-መንግሥቱን እንደ ወታደር ጦር ሠራዊቱን ለበርካታ ዓመታት የተቆጣጠሩት ጄኔራሎች እንደ ጦር አዛዥ አዋግተዉ፣ እንደ ፖለቲከኛ-ዲፕሎማት ተደራድረዉ ያሸነፉት አድም ጦርነት የለም።

በየጦርነቱ ሚሊዮኖችን አስጨርሰዉ፣ የደሐይቱን ሰፊ ሐገር ጥሪት ከስክሰዉ፣ ሰፊይቱን ሐገር እየገመሱ ለጠላቶቻቸዉ እያስረከቡ

በኃይል የያዙቱን ስልጣን በተረኛ ኃይለኛ እየተቀሙ ሔደዋል።ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል-ቡርሐንም ሆኑ ተከታዮቻቸዉ ከጄኔራል ኢብራሒም አቡድ፣ ከጀዓፈር ኑሜሪ ወይም ከሐሰን አል-በሽር የተለዩ አይደሉም።እስካሁን የተለየ አላደረጉምም።በየአካባቢዉ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ሥልጣን፣ኃይል፣ተቀባይነታቸዉን የገዘገዘዉን ዑመር ሐሰን አል በሽርን በቀላሉ አስረዉ የካርቱምን ቤተ-መንግስት ተቆጣጠሩ።ሚያዚያ 11 2019።ከዚያ እስካሁን ለሕዝብ የገቡትን ቃል ክደዉ ሰላማዊ ሕዝባቸዉን ይገድሉ፣ያስሩ፣ያስፈራሩታልም።

 የካርቱሙ ነዋሪ ትናንት እንዳለዉ ደግሞ ዜጋቸዉን እሸበሩ ነዉ።

«ሕዝቡ እየተሸበረ፤በከፍተኛ ስጋትም እየተሸማቀቀ ነዉ።የሱዳን ሕዝብ በሙሉ በስጋትና ፍርሐት እንደተዋጠ ነዉ።ከየቤቱ መዉጣት፣ ሥራ መሔድ አይችሉም።ምንም ማድረግ አይችሉም።ሁሉም ነገር ቆሟል።ሁኔታዉ በጣም መጥፎ ነዉ።ሰዉ መብላት፣መንቀሳቀስ፣መስራት አይችልም።እቤትሕ እንኳን በሰላም መቀመጥ አትችልም።ትሸበራለሕ።ሁሉንም ትፈራለሕ።»

ጄኔራል ቡርሐን የሚመሩት ወታደራዊ ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት ሠላማዊ ሰዎችን ባደባባይ ሲረሽን የዓለም ኃያላን መንግሥታት የሱዳንን ሕዝብ ጭንቀት-ፍርሐት የተረዱ መስለዉ ነበር።የቀድሞዋ የሱዳን ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ከብዙ ብጤዎችዋ ቀድማ ግድያዉን ጠንከር ባሉ ቃላት ተቃዉማለች።በብሪታንያ ዉጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳይ ሚንስትር ሐሪየት ባልደዊን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የሱዳን ጦር ሥልጣኑን  ለሲቢላዊ አስተዳደር ማስረከብ አለበት።«በተቻለ ፍጥነት» አሉ ሚንስትሯ።

«ሱዳን ዉስጥ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ሥለተወሰደዉ እርምጃ የደረሰን አስተማማኝ ዘገባ በጣም አሳምሞናል።የሱዳኑ አምባሳደር እዚሕ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዲመጡ አስጠርቻቸዋለሁ።

ሱዳን ዉስጥ በደረሰዉ ሁኔታ የብሪታንያ መንግስት በጣም ማዘኑን ለጊዚያዊ ወታደራዊዉ መንግስት እንዲያስረዱ እነግራቸዋለሁ።ከሰላማዊ ሰልፈኞቹ ጋር ድርድሩን እንዲቀጥሉ እናሳስባለን።ሱዳን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሲቢላዊ አስተዳደር መሻገር አለበት።»

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴርም ተቀራራቢ መግለጫ አዉጥቷል።የብሬግዚት ጣጣ ወጥሮ የያዘቸዉ የለንደንም ሆኑ፣ ከቻይና እስከ ሜክሲኮ በንግድ፤ ከኢራን እስከ ሰሜን ኮሪያ፣ ከሩሲያ እስከ ቬኑዙዌላ ከሚገኙ ሐገራት ጋር በፖለቲካ ዉዝግብ የተጠመደዉ የትራምፕ መስተዳድር የደሐቱን ሱዳንን ጉዳይ ከጋዛጤዊ መግለጫ በላይ «ጉዳዬ» የሚሉበት ጉዳይ የላቸዉም።

የኪል-ዩኒቨርስቲ፣ ለንደን፣ ረዳት ፕሮፈሰር አወል ቃሲም አሎ እንደሚሉት ደግሞ ኃያሉ ዓለም ስለሱዳን ብዙ የማይጨነቀዉ የሚያስጨንቀው ጥቅም ስለሌለዉ ነዉ።

ከካርቱም አልፎ ለንደን፣ዋሽግተን ሰሜን አፍሪቃም አደባባይ የሚሰለፈዉ የሱዳን ሕዝብ ከወታደራዊዉ ሁንታ እኩል ለወታደራዊዉ ሁንታ ድጋፍ የሚሰጡትን የሪያድ-የአቡዳቢና የካይሮ ገዢዎችን ማዉገዙ አልቀረም።ፕሬዝደንት አል-በሽር ደቡብ ሱዳን ላይ ሲዋጉ በማዕቀብ የቀጧቸዉ ዳርፉር ላይ ሲዋጉ በፍርድ ቤት የወነጀሏቸዉ የለንደን-ዋሽግተን መንግሥታት የሱዳን ሕዝብ ባደባባይ ሲረሸን ከዕለታዊ «መግለጫ» ባለፍ ምንም አለማለታቸዉ በርግጥ ያስተዛዝብ ይሆናል።

ይሁንና በዶከተር አዉል አገላለፅ በገንዘብ ዝዉዉር Transactional ላይ የተመሠረተዉ የምዕራቡ ዓለም አቋም በሰወስቱ የአረብ ሐገራት እርምጃ የሚለካ ነዉ። ለኢትዮጵያ ግን የሱዳን ጉዳይ ከጉርብትናም ባለፍ ለራስዋ ለኢትዮጵያ ሠላም፣ደሕንነትና መረጋጋትዋም ወሳኝ ነዉ።

በዚሕም ምክንያት ካርቱም በደም አበላ በጨቀየች ማግሥትä የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ተንደርድረዉ ካርቱምን መጎብኘታቸዉ ሲያስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።ጠቅላይ ሚንስትሩ ከወታደራዊዉ ገዢዎችና ከተቃዋሚዎቹ መሪዎች ጋር በየተራ ባደረጉት ዉይይት ሁለቱም ወገኖች የጠቅላይ ሚንስትሩን አደራዳሪነት መቀበላቸዉን በየፊናቸዉ አስታዉቀዋል።

ተቃዋሚዎቹ ባወጡት መግለጫ እንደጠቀሱት የተወሰኑ ቅድመ-ሁኔታዎች  ከማስቀመጣቸዉ በስተቀር በኢትዮጵያ ሸምጋይነት  

ከወታደራዊ ገዢዎቹ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ናቸዉ።ይሁንና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የማደራደሩን ዉክልና አረብኛ ቋንቋን አቀላጥፈዉ ለሚናገሩት ለአንጋፋዉ ዲፕሎማታቸዉ ለማሕሙድ ዲሪሪ ሰጥተዉ አዲስ አበባ እንደገቡ የሱዳን ወታደራዊ ሁንታ ጠቅላይ ሚንስትሩን ካነጋገሩ የተቃዋሚ መሪዎች ቢያንስ ሁለቱን ማሰሩ ነዉ ዚቁ።ቃል እየገቡ ቃል የሚያጥፉት ወታደራዊ ገዢዎች በተቃዋሚዎቻቸዉ ላይ የወሰዱት እርምጃ ተቃዋሚዎቹን ለተጨማሪ አድማና አመፁን አጠናክሮታል።

ከትናንት ጀምሮ የፀናዉ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ወትሮም ዉጥረትና ሥጋት ያልተለያትን ካርቱምን ወና አድርጓታል።ጦር ኃይሉ ትናንት ብቻ ካርቱም እና እንዱሩማን ዉስጥ በተቃዋሚዎች ላይ በከፈተዉ ጥቃት አራት ሰዉ ገድሏል።የወታደራዊዉ ሁንታ ቃል አቀባይ ሌትናንት ጄኔራል ጀማለዲን ዑመር እንዳስጠነቀቁት የተቃዋሚዎቹን አድማ ለመበትን ጦር ኃይሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመዉሰድ ወስኗል።

«ወታደራዊዉ ምክር ቤት ተጨማሪ ጦር ሠራዊት ለማስፈር ወስኗል።የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን ወደነበረበት ለመመለስ፣ያልታጠቁ ሰዎችን ደሕንነት ለመጠበቅ፣ መንገዶችን ለመክፈት፤ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለማስከበር፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስቀጠል፣ ስልታዊ ተቋማትንና ገበያዎችን ለመጠበቅ፣ ተጨማሪ ፈጥኖ ደራሽና መደበኛ ጦር እናሰፍራለን።»

የወታደራዊዉ ምክር ቤትና የተቃዋሚዎቹ ዉዝግብ፣ግጭት፣እርምጃ-አፀፋ ርምጃና ዛቻዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርን የማደራደር ጅምር ጥረትን በጅምር እንዳያስቀረዉ ያሰጋል።ዶክተር አወል ግን ጥረቱ መቀጠል አለበት ባይ ናቸዉ።የተጠና ስልት፣የሌሎችን ትብብርም ማካተት አለበት።

ሱዳን ዉስጥ ሲቢላዊ

አስተዳደር እንዲመሠረት የብሪታንያ ባለስልጣናት ያሳስቡ፣ሌሎች ይጠይቁ ይሆናል።የሱዳን ወታደራዊ ገዢዎች ስልጣናቸዉን ለሲቢላዊ አስተዳደር እንዲያስረክቡ ወይም ለድርድር እንዲገዙ ለማስገደድ እስካሁን ጠንከር ያለ እርምጃ የወሰደ ወይም ለመዉሰድ ያስጠነቀቀዉ የአፍሪቃ ሕብረት ብቻ ነዉ።

የአረብ ሊግ፣የአዉሮጳ ሕብረት፣የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመገናኛ ዘዴዎች መግለጫ በስተቀር ያደረጉት የለም።ለማድረግ ያሰቡት መኖር አለመኖሩም አይታወቅም።

የወታደራዊዉ ምክር ቤት መሪዎች  አድመኞችን ባደባባይ በጥይት ማስደብደብ የጀመሩት ካይሮ፣አቡዳቢና ሪያድን ጎብኝተዉ በተመለሱ ማግስት በመሆኑ የ«አይዞሕ» ባዮቻቸዉን ማንነት ለማወቅ የአዋቂዎች ትንታኔ አላስፈለገም።የካርቱም ጄኔራሎችን የሚበረታቱት የአረብ ገዢዎች የኢትዮጵያም፣የኤርትራም ወዳጆች፣የዋሽግተኖች ተላላኪዎች ናቸዉ።የዐብይ የማደራደር ጥበብ ጥቅም ያጠላለፈዉን ሴራ መፍታት ይችል ይሆን? 

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ

 

 

Audios and videos on the topic