የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ምክንያትና መዘዙ | አፍሪቃ | DW | 30.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ምክንያትና መዘዙ

ምክንያቶቹ የስልጣን ጥማታቸዉን ለመሸፈን የሰጡት ሊሆን ይችላል።ምናልባት አንዳዶች እንደሚጠረጥሩት የካይሮዉ ሞክሼያቸዉ፣ የሪያድና የአቡዳቢ ወዳጆቻቸዉ ማበረታቻ፣ ወይም ከ63 ዓመት በፊት እንደነበረዉ የCIA «ቀጥል» የምትል ቀጭን ትዕዛዝ ወይም ድጋፍ ደርሷቸዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።ከሁሉም ምክንያቶች በአንዱ ግን የማይስማማ የለም

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:21

ሱዳን ከጦር ኃይሉ አገዛዝና ተፅዕኖ ተላቅቃ አታዉቅም

የሱዳን ፖለቲከኞች ለመሪነት ሉዓላዊ ምክር ቤት የሚል ስብስብ ይወዱታል፤ ደግሞም ይጠሉታል።ጥር 1956 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሉዓላዊ ምክር ቤት ነበራቸዉ።ሕዳር 1958 ጄኔራል ኢብራሒም አቡድ አፈረሱት።በ1964 የመጀመሪያዉን ሉዓላዊ ኮሚቴ መሠረቱ።ባመቱ የመጀመሪያዉን አፍርሰዉ «ሁለተኛ» ያሉትን ሉዓላዊ ኮሚቴ መሰረቱ።በ28ኛ ቀኑ ኢስማኤል አል አዝሓሪ አፈረሱት።የሶስቱም ምክር ቤት ወይም ኮሚቴዎች አርማ አዉራሪስ ነበር።ነሐሴ 2019 አዉራሪሱን ንስር በመሰለ አሞራ ለወጡትና አዲስ  ሉዓላዊ ምክር ቤት መሰረቱ።ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን አፈረሱት።ምክር ቤትና ኮሚቴዎች እየተመሰረቱ ሲፈርሱባት፣መስራቾች ተወግደዉ፣ አፍራሾች እየገዙ ሲወድቁባት እነሆ 65 ዘመን አስቆጠረች።ሱዳን።ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ። 
                                   
ሱዳን ከአንግሎ-ግብፅ ጥምር ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከመዉጣትዋ ከሁለት ዓመት በፊት በ1954 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኢስማኤል አል አዝሓሪ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኑ።አዝሐሪ አዝጋሚዉን ሽግግር በጥንቃቄ የመሩ፣ ሐገሪቱን ከነፃነት በኋላ የተፈራዉ ክፍፍል እንዳይፈጠር የጣሩ፣ የብሪታንያ ግብፆችን ጫና በጥንቃቄ ያስታመሙ በመሆናቸዉ ይመሰገናሉ።
ይሁንና አል አዝሓሪ ያኔ የጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ የቀንድ ከብት ምርትና ሽያጭ ጥገኛ የሆነዉን የሰፊዋን ሐገር ምጣኔ ሐብት አላማሻሻለቸዉ በዉጤቱም የሕዝቡን ችግር ለማቃለል ብዙም ባለመጣራቸዉ  ከመወቀስ-መተቸት አላመለጡም።ወቀሳ ትችቱ በማየሉ ሱዳን በ1956 ነፃ በወጣች ማግሥት አል አዝሓሪና የሚመሩት የሱዳን ብሔረተኞች አንድነት ፓርቲ ሥልጣን ለቅቀዉ የኡማ ፓርቲን የሚመሩት ሰይድ አብደላሕ አል ኻሊል የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ያዙ።

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት የተመሰረተዉም ያኔ ነበር።ምክር ቤቱ የሁለቱን ተቀናቃኝ የሲቢል ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ልዩነት

አቻችሎ፣ ፖለቲከኞች በሐገረ-መንግስት ምሥረታ፣ በዘላቂ ሕገ-መንግስት ቀረፃ ከሁሉም በላይ የሕዝቡን ምጣኔ ሐብታዊ ጥያቄ በመመልስ ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳል ነበር ተስፋዉ።ከተስፋ አላለፈም።
ሁለቱ ዕዉቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር «ሲናጩ» ዉዝግብ-መጠላለፉን በቅርብ የሚከታተሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ኢብራሒም አቡድ ለንጭት-ጥልፍልፉ ጥሩ መፍትሔ አገኙለት።መፈንቅለ መንግስት።ሕዳር 1958።
ፊሊፕ በርኔት አጊ የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ሰላይ እንደፃፈዉ ለወትሮዉ ፖለቲካ ብዙም የማይጥማቸዉ የጦር ጄኔራል መፈንቅለ መንግስት እንዲደርጉ የገፋፋና የረዳቸዉ ሲአይኤ ነዉ።ጄኔራል አቡድን  ሲ አይ ኤ ደገፋቸዉም አልደገፋቸዉ የመፈንቅለ መንግስቱ መሰረታዊ ምክንያት የሱዳን የሲቢል መሪዎች የሕዝባቸዉን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ እርስበርስ በመካሰስ-መወቃቀስ ጊዚያቸዉን ስላባከኑ ነበር።
የመጀመሪያዉ የሱዳን የሲቢል መንግስት ወይም ሉዓላዊ ምክር ቤት በመፈንቅለ መንግሥት በፈረሰ በ63ኛ ዓመቱ ዘንድሮ አራተኛዉ ሉዓላዊ ምክር ቤት በመፈንቅለ መንግስት ፈረሰ።ባለፈዉ ሰኞ።
                                  
«በሽግግሩ ወቅት የመሪነት ሚና የሚጫወት የሰለጠነ መንግሥት መመስረት አንፈልጋለን።አንዳድ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ቢታገዱም፣የሕገ-መንግስቱን አጠቃላይ ደንቦች እናከብራለን።መላዉን የሱዳን ሕዝብ የሚያረካ መንግሥት እንመሰርታለን።»
ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን።የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ።ጄኔራሉ መፈንቅለ መንግስቱን ለማድረጋቸዉ የሰጧቸዉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።ምክንያቶቹ የስልጣን ጥማታቸዉን ለመሸፈን የሰጡት ሊሆን ይችላል።ምናልባት አንዳዶች እንደሚጠረጥሩት የካይሮዉ ሞክሼያቸዉ፣ የሪያድና የአቡዳቢ ወዳጆቻቸዉ ማበረታቻ፣ ወይም ከ63 ዓመት በፊት እንደነበረዉ የCIA «ቀጥል» የምትል ቀጭን ትዕዛዝ ወይም ድጋፍ ደርሷቸዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።ከሁሉም ምክንያቶች በአንዱ ግን የማይስማማ የለም።የሲቢል ፖለቲከኞቹ ክፍፍል።የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሒም ከጠቀሷቸዉ ምክንያቶች አንዱ የሲቢል ፖለቲከኞቹ ልዩነቻቸዉን አጥብበዉ በጋራ አለመቆማቸዉ ነዉ።
ሱዳን በ1956

ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ የበቀደሙን ጨምሮ 18 መፈንቅለ መንግስቶችንና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን አስተናግዳለች።ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት የሱዳንና የግብፅ ጦር ኃይል ሚና እንደብዙዎቹ የዓለም ሐገራት የሐገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነትን ማስከበር ብቻ አይደለም።
ጦር ኃይሉ ከፖለቲካ እስከ ምጣኔ ሐብቱ የሚገኙ መዋቅሮችን ይቆጣጠራል።ጠንካራም ነዉ።
                                   
ፖለቲካዉን ከዚሕ ከስልሳ ዘመናት በላይ ከፀናዉ የጦር ኃይል ተፅዕኖ  ለማላቀቅ የሱዳን የሲቢል ፖለቲከኞች በጋራ መቆም፣አበክሮ መጣርና የሕዝባቸዉን ፍላጎት ማርካት ነበረባቸዉ።ግን አላደረጉትም። በዚሕም ምክንያት በ1958 ጄኔራል አቡድ፣ በ1969 ኮሎኔል ጅዓፈር አል ኑሜሪ፣ በ1985 ማርሻል አብድል ረሕማን ስዋር አል-ዳሐብ፣ በ1989 ኮሎኔል ዑመር ሐሰን አል-በሽር፣
በ2019 ጄኔራል አሕመድ አዋድ ኢብን አሩፍ (ላንድ ቀንም ቢሆን) ያደረጉትን ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ዘንድሮ ደገሙት።
መፈንቅለ መንግሥቱ ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት የሚጠበቅ ነበር።ምልክቶችም ታይተዋል።
                                              
ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክና ተባባሪዎቻቸዉን ግን ምልክቶቹን እያዩም አሁን የሆነዉ እንዳይሆን ያደረጉት ሙከራ በጣም ትንሽ ነዉ።ከሁሉም በላይ ከምዕራባዉያን ያገኙትን ድጋፍ ለመቃረም ከፓሪስ፣ለንደን፣ ብራስልስ፣ ዋሽግተን ሲባትሉ የሕዝባቸዉን የዳቦ ጥያቄ «በይደር» ማለፋቸዉ ስልጣኑን ጠቅልለዉ ለመያዝ ለሚያደቡት ጄኔራሎች ጥሩ ምክንያትና አጋጣሚ አቀበሏቸዉ።ጄኔራል ኢብራሒም አቡድ የያኔዉን የሲቢል አስተዳደር ያስወገዱት የኑሮ ዉድነት

ባስመረረዉ ሕዝብ ድጋፍ ነዉ።
አቡድን ከስልጣን ያስወገደዉ «የጥቅምት አብዮት» ተብሎ የሚጠራዉ የ1964ቱ ሕዝባዊ አመፅ ነበር።የአመፁ ምክንያት ዳቦ ነበር።ኑሜሩ ከስልጣን የተወገዱት በኑሮ ዉድነት የተማረረዉ ሕዝብ ባነሳዉ አመፅ ነበር።ለአልበሽር ከስልጣን መወገድ ሰበቡም የደቡብ ሱዳን መገንጠል፣ የዳርፉር ጦርነት፣ የኮርዶፋኖች አመፅ አልነበርም።የዳቦና የፉል ዋጋ መወዳድ ያስመረረዉ ሕዝብ ሕዳር 2018 ኻርቱም ላይ ያቀጣጠለዉ አመፅ እንጂ።
                                   
ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ያደረጉትን መፈንቅለ መንግስት ካንጀትም ሆነ ካንገት የተለያዩ ወገኖች እያወገዙት ነዉ።የአፍሪቃ ሕብረት ሱዳንን ከአባልነት አግዷል።የዓለም ባንክና ዩናይትድ ስቴትስም ለሱዳን የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጠዋል።የአዉሮጳ ሕብረትም ተመሳሳይ እርምጃ ለመዉሰድ ዝቷል።የዉጪዉ ጫና ሐገር ዉስጥ ከሚደረገዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ጋር ተዳምሮ የኻርቱም ጄኔራሎችን ዉሳኔ ማሻር-አለማሸሩ ጊዜ የሚመልሰዉ ጉዳይ ነዉ።
መፈንቅለ መንግሥት አድርጊዎቹ በያዙት ስልጣን ቀጠሉም፣ለጫናዉ ተንበረከኩ፣ ወይም ምስቅልቅሉ ቀጠለ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢዉ ሐገራት ላይ የሚያሳድረዉ አሉታዊ ወይም አወንታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ


 

Audios and videos on the topic