1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን መንግስት፤ የዳርፉር ችግርና የአፍሪካ መሪዎች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 1997

በዳርፉር የሰላም ጉዳይ ሊቢያ ትሪፓሊ በመካሄድ ላይ የሚገኘዉ የአፍሪካ መሪዎች ዉይይት የካርቱም መንግስትና አማፅያኑን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ዉስጥ በናይጀሪያ እንዲወያዩ ለማድረግ የሚያስችል መግባባት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/E0jz
የሊቢያዉ መሪ ሙአመር ጋዳፊ በዳርፉር ጉዳይ ላይ ሊመክር በተሰበሰበዉ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ
የሊቢያዉ መሪ ሙአመር ጋዳፊ በዳርፉር ጉዳይ ላይ ሊመክር በተሰበሰበዉ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይምስል AP

በተጨማሪም እነዚሁ መሪዎች ትሪፓሊ ላይ ባካሄዱት ጉባኤ በዳርፉር በተለያዩ ጎሳዎች ላይ ጥቃት የፈፀሙ የጦር ወንጀለኞች በዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ በአማፅያኑ የሚደረገዉን ጥረት ችላ በማለት ለሱዳን መንግስት ከፍተኛ የፓለቲካ ድጋፍ መለገሳቸዉን AFP ዘግቧል።
የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ለጋዜጠኞች እንደገለፁት የአቡጃዉ ድርድር በወሩ ማለቂያ ላይ ማብቃት አለበት።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ሱሌይማን አዋድም እንደተናገሩት ይፋ ዉይይቱ በመጪዉ ግንቦት 24 ቀን ይጀመራል።
የመጨረሻዉና ቁርጥ ያለዉ ቀን የሚታወቀዉ ለሁለት ቀናት የተካሄደዉና ዛሬ ማምሻዉን የሚጠቃለለዉ የመሪዎቹ ዉይይት ሲጠናቀቅ ነዉ።
ጉባኤዉ የሊቢያዉን መሪ ሞአመር ጋዳፊ፤ የግብፁን ሆስኒ ሙባረክ፤ የቻዱን ኢድሪስ ዴቢ፤ የናይጀሪያዉን ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፤ የኤርትራዉን ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የሱዳኑን ኦማር አል በሺር እንዲሁም የጋቦኑን ምክትል ፕሬዝደንት ዲጆብ ዲቩንጊ ዲ ዲንጌ አካቷል።
በሺር እንደሚሉት በዚህ ጉባኤ የተገኙ አገራት ሁሉ ተወካዮቻቸዉን ወደ አቡጃ በመላክ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደዉን ዉይይት እንዲከታተሉና ልዩነታቸዉን የሚያጠቡ ሃሳቦችን እንዲሰነዝሩ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በዳርፉር የሚገኙት ዋነኛ ሁለት አማፅያን ቡድኖች የሱዳን የነፃነት ንቅናቄ SLM እና የፍትህና የእኩልነት ንቅናቄ JEM ተጠሪዎች በትሪፓሊ ከተማ ቢገኙም በጉባኤዉ አልተሳተፉም።
ሆኖም SLM በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በናይጀሪያ አቡጃ በሚካሄደዉ ዉይይትና ድርድር ላይ ለመሳተፍ በድጋሚ አረጋግጧል።
በተጨማሪም የተኩስ አቁም ስምምነቱም ጨምሮ ከካርቱም መንግስት ጋር የተደረሰዉን ስምምነት በመፈፀም ረገድ ያለዉን ቁርጠኝነት ገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት በናይጀሪያ ዋና ከተማ የሚያዘጋጀዉ ሁለቱን ወገኖች የሚያቀራርበዉ የዉይይት መድረክ ካለፈዉ ታህሳስ ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ በተከሰቱ የተኩስ አቁሙን ስምምነት በጣሱ ጥቃቶች ሳቢያ ተቋርጦ ነበር።
ጉባኤዉ ከመከፈቱ በፊትም SLM ተሳታፊዎቹ የካርቱም መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዉሳኔዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።
በዚህም ይላል ቡድኑ ሱዳን የወንጀለኞች ገነት መሆኗ መቆም ይኖርበታል።
ሆኖም በትሪፓሊ የሚገኘዉ የአፍሪካ መሪዎች ስብስብ በዳርፉር ሰብአዊ መብትን በመርገጥ የጅምላ ግድያ፤ ማሰቃየት፤ አስገድዶ መድፈርና ለደረሰዉ ዉድመት ተጠርጣሪ መሆናቸዉ በመንግስታቱ ድርጅት የተጠቆመዉን 51 ሰዎች ላለማቅረብ ያሳየዉን እምቢተኝነት በማስተዛዘን አልፎታል።
ባለፈዉ መጋቢት የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት የዳርፉር የጦር ወንጀለኞች ክስ ሄግ በሚገኘዉ በአለም ዓቀፉ የፍትህ ችሎት መቅረብ እንዳለበት መጠየቁ ይታወሳል።
የሱዳን የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ኦስማን ኢስማኤልም ሱዳን በተቻላት አቅም በአፍሪካዉያን ድጋፍ የፍትህ ሂደቱ ሱዳን ዉስጥ በሱዳን ስርዓት እንዲካሄድ እንደምታደርግ ለጋዜጠኞች ገልፀዋል።
በዉሳኔዉ መሰረትም የፍርድ ሂደቱ በአፍሪካዉያን የህግ አማካሪዎች ድጋፍ በሱዳን እንደሚካሄድና አፍካዉያን ያልሆኑት ደግሞ በተለያዩ አስፈላጊ ነገሮች አቅርቦት ይተባበራሉ።
ከወዲሁም ግብፅ ልዩ በሆነዉ የዳርፉር የጦር ወንጀለኞች የፍትህ ሂደት የሚያግዙ የህግ ባለሙያዎችን ወደ ሱዳን ለመላክ ጠይቃለች።
በትናንትናዉ እለት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የናይጀሪያዉ ኦባሳንጆ በዳርፉር ያለዉን ሁኔታ በማረጋጋት ረገድ ከአለም አቀፉ ህብረተሰብ ይልቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ሃላፊነት መዉሰድ ይኖርባታል። በተለይም ደግሞ ወታደራዊ ሃይልን በተመለከተ።
በዚህ ጉባኤ ወቅትም የሱዳኑ በሽርና የኤርትራዉ ኢሳያስ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለዉ ቅራኔ እንዳለ ሆኖ ከረጅም አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ተወያይተዋል።
ሱዳንና ኤርትራ አንዱ ሌላዉን ለተቃዋሚ ቡድኖች ድጋፍና መሸሸጊያ ይሰጣል በማለት መረር ባለ ጠላትነት መተያየት ከጀመሩ ሰንበት ብለዋል።