የሱዳንንና ደቡብ ሱዳን ሰላም | አፍሪቃ | DW | 04.05.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሱዳንንና ደቡብ ሱዳን ሰላም

ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋ ለጦርነት የሚጋብዛቸዉን መንስኤ ለማስቆም የአፍሪቃ ኅብረት ያቀረበላቸዉን የመፍትሄ ሃሳብ እንደምትቀበል አመልክታለች። ሁለቱ ሐገሮች በቀረበላቸዉ ሃሳብ መሠረት ወደ ድርድር ጠረጴዛ መጥተዉ ልዩነታቸዉን ለመፍታትም ሁለት


ሳምንት ተሰጥቷቸዋል። በተደጋጋሚ ወደ ግጭት ያዘነበሉት ኻርቱምና ጁባ የሚያግባባቸዉን ስልት ቢቀይሱ እንደሚበጅ የጠቆሙት በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበግር የሚገኘዉ የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪዩስ አታ አሳሞዋ ዘላቂ ሰላም ያሰፍናሉ ብሎ ከወዲሁ መተንበይ ግን እንደሚከብድ አመልክተዋል።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፤ ከደቡብ ሱዳን ራስ መቻል ማግስት አንስቶ የሚያቆራቁሳቸዉ ምክንያት እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አልታየም። የአፍሪቃ ኅብረት በሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ ፤ ብሎም በአዛዉንት ሸንጎዉ ሁለቱን ወገኖች ለማግባባት ከመጣርም አልቦዘነም። ትናንት ይፋ የሆነዉ ኅብረቱ ጁባንና ኻርቱምን ሊያግባባ ይችላል ሲል የቀረጸዉ የመፍትሄ ሃሳብ ሱዳንም ሆነች ደቡብ ሱዳን ተቀብለነዋል ማለታቸዉ ተነግሯል።

Sudan / Omar al Baschir / Präsident / Overlay-fähig

ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር

ሁለቱ ወገኖች ከአደራዳሪና ገላጋዮቻቸዉ የሚቀርቡ ሃሳቦችን እንደሚቀበሉ መግለፃቸዉ የተለመደ በመሆኑ የዚህኛዉ ተግባራዊነት እስከምን ድረስ ነዉ መባሉ አይቀርም ። ደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሩስ አታ አሳሞዋ ሁለቱ ወገኖች ሃሳቡን የመቀበል አዝማሚያ እንዳላቸዉ አመላካች ነገሮች አሉ ባይ ናቸዉ፤
«ለጊዜዉ የቀረበዉን ሃሳብ ሊቀበሉ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ ከሁለቱም ወገን በርካታ ጠቋሚ ነገሮች አሉ ብዬ አስባለሁ፤ ይህም ራሱ ሃሳቡ በዉስጡ ሁለቱም እንዲቀበሉት የሚያስችሉ በርካታ አዎንታዊ ነጥቦች አሉትና ነዉ። አንደኛ ሁለቱም ወገኖች አብዬን ጨምሮ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ግዛት መልቀቅ እንዳለባቸዉ፤ ለዚህም ጊዜ ወስኗል፤ በአካባቢዉ ሰላም ለማስፈን ከተፈለገ መደረግ እንዳለበትና ያንን የሚያመላክት መሆን እንዳለበትን አመልክቷል። በተጨማሪም ይህን በማያደርግ ላይ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል ተካቷል።»

እንደተመራማሪዉ ትንታኔም የመፍትሄዉ ሃሳብ ለአፍሪቃ ኅብተረት ከፍተኛ የአስፈፃሚ አካል የሚሰጠዉ ስልጣን ሁሉ ተካቶ ሁለቱ ወገኖች ወደሰላም እንደመጡ የሚገፋ አቅም የያዘነ ነዉ። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ ሲደራደሩና ሲሸመገሉ ወደስምምነት እንደቀረቡ እያመለከቱ መልሰዉ ያንን የሚንድ ርምጃ ሲወስዱ በተደጋጋሚ በመታየቱ የአፍሪቃ ኅብረትም ሆነ የተመድ ሁለቱ መንግስታት ዉላቸዉን ተጨባጭ እንዲያደርጉ ሊወስዱት የሚችሉት ርምጃ ምን ቢሆን ይበጃል ለሚለዉ፤ አንድሩስ አታ አሳሞዋ የተመድ እንዳስጠነቀቀዉ ማዕቀብ መጣልን ይመርጣሉ፤
«የደረሰቡቻዉን ስምምነቶች፤ አንዳንዴም የፈረሙባቸዉን ዉሎች መስበራቸዉን ከቀጠሉ እኔ የተመድ ያቀረበዉን የአማራጭ ዉሳኔ ነዉ የምመርጠዉ፤ ያም ማዕቀብ ነዉ። ምን እንኳን ሰፋ ያለ የማዕቀብ ይዞታን ብቃወምም፤ በሁለቱም ዋና ከተሞች በሚገኙ የተመረጡ እጆቻቸዉ ችግርና ጦርነትን በማባባስ ላይ ዉሏል የሚባሉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ይጣል የሚል ሃሳብ ነዉ ያለኝ። ያ በጣም አስፈላጊ ነዉ። በተጨማሪም ስማቸዉን ይፋ የማድረግና የማሳፈር ስልትም ሊኖረን ይገባል።»

Süd Sudan Präsident Salva Kiir

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር


የጆሃንስበርግ የፀጥታ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሩ አታ አሳሞዋ እንደገለፁት እስካሁን የሱዳንና የደቡብ ሱዳንን ግጭት ጦርነት ያባባሱና የሚያባብሱ ወገኖች ማንነት ይፋ አልሆነም። ለችግሩ መፍትሄ በመፈለግ ሂደት ግን ይህ ሁሉ መገለፅ እንደሚኖርበት ያምናሉ ። የሁለቱም መንግስታት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተዉ የሚነጋገሩበት መድረክ ቢመቻች ወደሰላም የመድረሻዉ መንገድ እንደሚያጥር ያመለከቱት አታ አሳሞዋ ከዚህ በፊት በሰላም አደራዳሪዎች ስምምነት የተደረሰባቸዉ ጉዳዮች ተግባራዊ መሆናቸዉ እየተረጋገጠ ቢሄድ ችግሩን ሊያቀለዉ እንደሚችልም ጠቁመዋል፤

«በተጨማሪም የአፍሪቃ ኅብረት ከፍተኛዉ አስፈፃሚ ምክር ቤት አዲስ የድርድር ግንባር ከመከፈቱ አስቀድሞ፤ እስካሁን ስምምነት የተደረሰባቸዉ ጉዳዮች ተግባራነታቸዉን እያጣራና እያረጋገጠ መሄዱ መልካም ይሆናል። ምክንያቱም የዉሳኔዎችን ተግባራዊነት እያጣራን ድርድሩን ካልቀጠልን፤ የአዲስ ጉዳዮች ድርድር ቀድሞ የተደረሰባቸዉን ነጥቦች ያጓትታል ። »

ይህ በእንዲህ እንዳለም የተመ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን የመጀመሪያ ጉብኝት የፊታችን ማክሰኞ እንደሚጀምሩ ተገልጿል። የጉዟቸዉ አላማም ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋ በድንበር ግጭቱ ምክንያት የተጎዱ ሲቪሎችን ይዞታ ለመነጋገር እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች