1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳናውያኑ ርዳታ ጠባቂዎች ሁኔታ

ሰኞ፣ መጋቢት 9 2005

የተመድ እአአ በ 2013 ዓም ለሱዳን ስለሚሰጠው የርዳታ እና የበጀት ዕቅድ ሰሞኑን ተወያይቶዋል። ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው ለጋሽ ሀገራት እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ምን ያህል የሱዳን ዜጎች ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በሱዳን መዲና ካርቱም ከተወያዩ በኋላ ነው።

https://p.dw.com/p/17ykO
ምስል Andreas Hansmann

የመረሳት ዕጣ ለገጠመው የዳርፉር ውዝግብ ሰለባዎች፡ እንዲሁም፡ በደቡብ ኮርዶፋን እና በብሉ ናይል ግዛቶች በቀጠለው ውጊያ ለሚሰቃየው ሕዝብ ለጋሽ ሀገራት በዚህ ዓመት ወደ አንድ ቢልዮን ዶላር ገደማ ርዳታ ያቀርባሉ ብለው የርዳታ ድርጅቶች ተስፋ አድርገዋል።
በሱዳን መዲና ካርቱሙ ሰሞኑን በተካሄደው የለጋሽ ሀገሮች ስብሰባ የተካፈሉት በሱዳን የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ መሥሪያ ቤት፡ በምሕፃሩ የ ኦቻ ቃል አቀባይ ዴሚያን ራንተስ እንዳስታወቁት፡ ዘንድሮ ወደ 4,3 ሚልዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ርዳታ ያስፈልጉታል። ከነዚህ መካከል ብዙዎቹ ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ ውዝግብ በቀጠለበት በዳርፉር ነው የሚገኘው። የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ዓመት በዚችው ሀገር ያካሄደው የርዳታ ተግባር በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የሰብዓዊ ርዳታ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ እንደነበር ራንተስ በመግለጽ ይህችው የአፍሪቃ ቀንድ ሀገር ዘንድሮም ተመሳሳይ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት አመልክተዋል።
 ኦቻ ባለፈው ዓመት ከጠየቀው ወደ አንድ ቢልዮን ዶላር ርዳታ ወደ 560 ሚልዮን ዶላር ገደማ፡ ማለትም፡ ከጠየቀው መካከል ሀምሣ ሦስት ከመቶው ርዳታ ብቻ መቀበሉን አመልክተዋል። ይህ እአአ በ 2011ዓም ካገኘው በጣም ያነሰ ነው። መሥሪያ ቤታቸው ምንም እንኳን 100,000 ሰዎች ርዳታ ለማቅረብ ዕቅድ ቢኖረውም፡ ለዘንድሮ የጠየቀው ከአምናው በስምንት ከመቶ ያነሰ ሲሆን፡ ወደ 983 ሚልዮን ዶላር እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል። የተመድ ደቡብ ሱዳን እአአ በ2011 ዓም ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ከሱዳን ጋ በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በሚገኙት የሱዳን የደቡብ ኮርዶፋን እና የብሉ ናይል ግዛቶች ውስጥ በሱዳን መንግሥት እና በዓማፅያን መካከል በሚካሄደው ውጊያ ችግር ያጋጠማቸውን 700,000 ሱዳናውያንን ለመርዳት ይፈልጋል። በርዳታ የሚገኘው ገንዘብ የውዝግብ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ችግር ለመቀነስ እንደሚያስችል ዴሚያን ራንተስ ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል።
« በርዳታ የምናገኘውን ገንዘብ በሱዳን ለሚታየው ግዙፍ የሰብዓዊ ችግር ማቃለያ እናውለዋለን፡ ለምሳሌ፡ በዳርፉር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለሚኖረው 1,4 ሚልዮን ሕዝብ የምግብ፡ ንፁሕ የመጠጥ ውኃ እና ሌላ አስፈላጊ መሠረታዊ ቁሳቁስ ርዳታ ለማቅረብ፡ እንዲሁም፡ በሌሎች የሱዳን ከፊሎች ከሚገኙ እና ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል ካላገኙት ዕድሜአቸው ከሦስት እስከ አሥራ አምሥት ዓመት የሆቸው ሦስት ሚልዮን ሕፃናት መካከል ቢያንስ 150,000 ን ወደ ትምህርት ቤት ለመላኪያ፡ 5,500 አዳዲስ መምህራንን ለማሠልጠን እና ለ 350,000 ሕፃናት መማሪያ የሚያስፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ ለመግዣ ለመሳሰሉት ተግባራት እናውለዋልን። »           
ይሁንና፡ በስብሰባው የተካፈሉት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት፡ በሶርያ በቀጠለው የርስበርስ ጦርነት እና በራሷ በሱዳን ውስጥ ርዳታውን ለተረጂዎቹ በማድረሱ ተግባር ላይ በተደቀነው ችግር የተነሳ የርዳታ ጥሪያቸው የሚፈልጉትን ዓይነት ምላሽ ማግኘቱ ይጠራጠሩታል። በቀጠለው ውዝግብ የተነሳ የሰብዓዊ ርዳታ አቅራቢዎች እንደልብ መንቀሳቀስ የማይችሉበት እና የሱዳን መንግሥትም በየጊዜው የሚያወጣቸው መመሪያዎች የርዳታ አቅርቦቱን ስራ እንዳደናቀፈው ተገልጾዋል። በባለፈው ዓመት ብቻ ሱዳን ውስጥ በተካሄደው ውጊያ ከአንድ መቶ ሺህ የሚበልጡ ሱዳናውያን ርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውን ዴሚያን ታንተስ ገልጸዋል።
« ለሱዳን የሰብዓዊ ርዳታ ላስፈለገበት አንዱ ምክንያት በሀገሪቱ የታየው ውጊያ ነው። እና በዚህም የተነሳ በወቅቱ በጣም አሳሳቢ የሆነውን ከመፀዳጃ ጉድለት ጋ የተያያዙትን ተቅማጥ፡ ወባ እና የተስቦ  በሽታዎች እንዳይባባሱ ባፋጣኝ አስፈላጊውን ርዳታ ማድረግ የግድ ይሆናል። ለምሳሌ፡ ነፍሰ ጡሮች በሰላም የሚገላገሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንፈልጋለን፤ ከሱዳን ሴቶች መካከል ሀያ ከመቶ የሚሆኑት መሠረታዊው የጤና እንክብካቤን አያገኙም። እና ከነዚህ ቀላል ነገሮች መካከል አንዳንዱን ማሟላት ብንችል የችግሩን መነሻ ልናስወግድ እንችል ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ሰሞኑን የነዳጅ ዘይት ምርት እንደገና እንዲጀመር እና ጦራቸውን ከድንበራቸው አካባቢ አርቀው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ቀጣና ለመመስረት የተስማሙበት ድርጊት የርዳታ አቅርቦቱን ስራ እንደሚረዳ ዴሚያን ራንተስ ተስፋ አድርገዋል።
« ይህ በዚሁ አካባቢ ወዳሉና አስቸኳዩ የሰብዓዊ ርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ማህበረሰቦች በቀላሉ መድረስ ያስችለናል በዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ አንዱ የስምምነቱ ውጤት ሊሆን ይችላል። እርግጥ፡ ይህ ገሀድ ይሆናል ብሎ አሁን መናገር መቻኮል ይሆናል፡ ግን፡ ተስፋ አድርገናል። »
በርዳታ የሚገኘው ገንዘብ በትክክል ስራ ላይ መዋል አለመዋሉን የተመድ ባዘጋጀው መርሀግብር እንደሚቆጣጥር ራንተስ አስረድተዋል።

Afrika Südsudan Südkordofan Flüchtlinge
ምስል Cap Anamur
Karte Sudan Blauer Nil Süd-Kordofan mit Südsudan
ምስል DW
Afrika Südsudan Südkordofan Flüchtlinge
ምስል Cap Anamur


አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ