የሱዳናዉያን አዲስ ዘመን | የጋዜጦች አምድ | DW | 10.01.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የሱዳናዉያን አዲስ ዘመን

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የመጨረሻ የሚሆነዉን የሰላም ስምምነት ሰነድ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናንና በቅርቡ ስልጣን የሚለቁት የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የወጪጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓዉል በተገኙበት ተፈራረሙ።

የስምምነቱን ሰነድ ሁለቱ ተፋላሚዎች ለታዛቢዎች ሲያሳዩ

የስምምነቱን ሰነድ ሁለቱ ተፋላሚዎች ለታዛቢዎች ሲያሳዩ

በናይሮቢ ስታዲየም የተከናወነዉን የስምምነት ዉል የፍፃሜ ስነስርዓት ለመከታተል ከተለያዩ አገራትም በርካታ መሪዎችና የመንግስታት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በሁኔታዉ የተደሰቱት ሱዳናዉያንም በባህላዊ ጭፈራ አድምቀዉታል።
ከወገባቸዉ በላይ ራቁታቸዉን በመሆን የነብር ቆዳ ያገለደሙት የዲንካ ጎሳ ወንዶች እየዘለሉና እየጨፈሩ ነበር ደስታቸዉን በባህላዊ ዜማቸና ዉዝዋዜ የገለፁት።
ከዚያም ሌላ የትግል ትርኢት አሳይተዋል በናይሮቢ ስታዲየም የአገራቸዉ የረጅም ጊዜያት ተፋላሚ ኃይላት የመጨረሻዉን ስምምነት ሲፈራረሙ።
በእለቱ በተመሳሳይ ሁኔታም በሺዎች የሚቆጠሩትና በግጭቱ ሳቢያ ከደቡብ ተፈናቅለዉ በካርቱም የሚገኙት ዜጎችም ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀላቸዉን ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በደስታ እየገለፁ ነዉ።
የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ንቅናቃ መሪ ጆን ጋራንግና የሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት አሊ ኦስማን ሞሃመድ ጠሃ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የመጨረሻ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀዉን የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ በርካታ እማኞች ተገኝተዋል።
የደቡቡ ክርስቲያንና እምነት የለሽ አማፂ ቡድን ከሰሜኑ አረብኛ ተናጋሪ ሙስሊም ወገኖች ጋር ያጋጫቸዉ ዋነኛ መንስኤ የአመለካከት ልዩነት መሆኑን በማንሳት እዉነተኛ ሰላም ሱዳን ዉስጥ ይታያል ወይ ያሉ ወገኖች አሉ።
በዚች ሰፊና ብዙ ህዝብ ባላት ሆኖም በርካታ ሰዎች ከባህላቸዉ ተለይተዉ በመበታተን ከሚኖሩባት አገር በጣም ሰፊ የአመለካከት ልዩነት ያላቸዉ ሁለቱ ወገኖች ስምምነትና መግባባት መፍጠር ይችላሉ ወይ? በማለት የጠየቁት የዑጋንዳዉ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ነበሩ።
በተለያዩ ጎሳዎች የቀረበዉን ትርኢት ካዩ በኋላም ሱዳን ዉስጥ ያለዉን እዉነት ማየት የቻል ነዉ ዛሬ ነዉ በማለት ሊተኮርበት የሚገባዉን የመከባበር ባህል አጉልተዉ ለማሳየት ሞክረዋል።
500 የተለየዩ ጎሳዎች፤ 130ቋንቋዎች፤ ክርስትና፤ እስልምናና የአፍሪካ ባህላዊ እምነቶችን አካታ እንደያዘች የሚነገርላት ሱዳን ይህን መሰሉ ፈታኝ ሃላፊነት ከፊቷ ተጋርጧል።
በናይሮቢ ስታዲየም ደስታቸዉን በጭፈራ ሲገልፁ የነበሩት በርካታ ሱዳናዉያን ግን መግባባት ይኖራል በሚል እርግጠኝነታቸዉን ሲገልፁ ተስተዉለዋል።
በደቡብ ሱዳን በምትገኝ ቶሪት ከተማ የተወለዱት የ65 አመቱ ሙስሊም ነጋዴ አባስ ኤል ሺክ አንዳቸዉ ለሌላኛዉ ታማኝ ከሆኑ ሰሜናዉያኑና የደቡቡ ህዝብ በሰላም መኖር ይችላሉ ይላሉ።
ለምሳሌ የእሳቸዉ አባት የሰሜን ሙስሊም ሲሆኑ እናታቸዉ ደግሞ የዲንካና የአረብ ቅይጥ መሆናቸዉን በመግለፅ ግንኙነታቸዉ መግባባትን እንደፈጠረ ይናገራሉ።
በእሳቸዉ አመለካከት ወጣቱና የአሁኑ ትዉልድ በዉጊያ ቀጣና ዉስጥ የተለያዩ መጥፎ ነገሮችን እያየ በመወለዱና በማደጉ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ምሬት ይታይበታል።
ሆኖም ግን ወደሰሜን የመሰደድ እጣ የገጠማቸዉ የደቡብ ወጣቶች ለሰሜናዉያኑ ሃዘኔታ ሲያሳዩ ይታያል ባይ ናቸዉ አባስ።
በካርቱም ከሚገኙት የደቡብ ሰዎች አንዱ የሆኑት የ55 አመቱ ገበሬ ጆሴፍ ላንግ በሰሜናዉያኑ ወገኖቻቸዉ ላይ ጥላቻ እንደሌላቸዉ ነዉ የለፁት።
ሰሜናዉያኑ እንደሰዉ ካየናቸዉ ጥሩዎች ናቸዉ እንደ መንግስት ግን በጣም አስቸጋሪዎች ናቸዉ ላለፉት ሁለት አስርታት ጦርነት ዉስጥ ነበርን ያም ችግር ዉስጥ ስለከተተን አሁን አማራጩን እየሞከርን ነዉ ይህ የሰላም ዉል የምንፈተንበት ይሆናል ባይ ናቸዉ ጆሴፍ።
በሰሜን ለሚገኙት የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች የሰላም ስምምነቱ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ የሚመለሱበትን ተስፋ የሰነቀ አጋጣሚ ነዉ።
ብዙዎቹ ካርቱም ዉስጥ ይጠለሉ እንጂ ስራ የላቸዉም እናም የሚሉት ዉሉ በተሳካ ሁኔታ
ከተከናወነ ወደ አካባቢያቸዉ መመለስ ብቻ እንደሚፈልጉ ነዉ።
የአማፅያኑ መሪ ጆን ጋራንግ የሰላም ዉሉ ለሱዳን ለዉጥ ያመጣል በማለት እምነታቸዉን የገለፁ ሲሆን በአዲሲቷ ሱዳን የሃይማኖት፤ የዘር፤ የጎሳና የፃታ አለመከባበር ቦታ የላቸዉም ባይ ናቸዉ።
ልዩነት ያለመመሳሰል ምንጭ ሆኖ በሱዳን መቆየቱንና ያም አገሪቱን ወደመከፋፈል እየገፋት መሆኑን ያስታወቁት ጋራንግ ሁሉም የተቻላቸዉን በማድረግ ይህን ለማስወገድ ቆርጠዉ መነሳት እንደሚኖርባቸዉ አሳስበዋል።
አሁንም የጦርነቱ ግንባር ቀደም ተጠቂ የሆኑት የሱዳን ዜጎች የሚጠይቁት ግን የሰላም ዉሉ በተግባር ዉሎ ለማየት መናፈቃቸዉን ብቻ ነዉ።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ስምምነት ላይ የደረሱባቸዉ ነጥቦችም ከነዳጅ ዘይት የሚገኘዉን ገቢ እኩል መካፈልና የደቡቡ ክፍል ራስ ገዝ ሆኖ በመቆየት ከስድስት አመት በኋላ ህዝበ ዉሳኔ ማካሄድ ግንባር ቀደሞቹ ናቸዉ።
የስራ እድልን በተመለከተም በማዕከላዊ መግስት አስተዳደር ዙሪያ 30 በመቶ የሚሆነዉ ለደቡብ የሚሰጥ ሲሆን የእስላማዊ ህግ ደግሞ በሰሜኑ አካባቢ ብቻ ተግባራዊ እንዲሆን ተስማምተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከአዲሱ የሱዳን የነዳጅ ሃብት ክምችት በየቀኑ 320,000 በርሜል ድፍድፍ ይመረታል።
ሰላም በአገሪቱ ከፀናም ለሱዳንና ሱዳናዉያን አዲስ ዘመን ማለት ያኔ ይሆናል።