የሰዎች አዘዋዋሪዎች የወንጀል አድማስ | ዓለም | DW | 02.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሰዎች አዘዋዋሪዎች የወንጀል አድማስ

በጨቋኝ መንግስታት ግፍ እና በደል ተማረው ከሃገር የሚሰደዱ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እና ለጋሽ ድርጅቶች ዜጎቻቸውን ለሚያፍኑ እና በሙስና ለተዘፈቁ መንግስታት የሚሰጡት የቀረጥ ከፋዮች የገንዘብ ድጋፍ ለትክክለኛ ዓላማ መዋሉን ክትትል እና ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባ በመስኩ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ፓኦሎ ካምፓና አሳሰቡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37

ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች

ከሃገር ሃገር በሚፈልሱ ስደተኞች ላይ በባህር እና በበረሃ የመደርሰውን አሰቃቂ የሞት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቀነስ ሰዎች በገፍ በሚፈልሱባቸው ጎረቤት ሃገራት አቅራቢያ የሚሰፍሩባቸውን ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፖች ማቋቋም መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል በመስኩ ጥናት ያደረጉ አንድ ባለሙያ ገለጹ ::በብሪታንያ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ምርምር እና ጥናት ማእከል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ፓኦሎ ካምፓና ለዶቸቨለ እንደገለጹት አፍሪቃውያን ስደተኞችን ለሞት ለስቃይ ለባርነት እና ለእንግልት የሚዳርገውን የሰዎች አዘዋዋሪ የወንጀለኞች ቡድን ኔትወርክ ህገወጥ ድርጊት ለመዋጋት ሁሉም በጋራ መስራት ይኖርበታል ብለዋል :: 

በቅርቡ ለህትመት የበቃው በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እና የማፍያ ቡድኖች ኔትዎርክ ላይ ትኩረቱን ያሳረፈው አንድ ሰፊ የባለሙያ የምርምር ጥናት የመገናኛ ብዙሃንን እና የተለያዩ

ተቋማትን ትኩረት እየሳበ መቷል :: በብሪታንያው ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ጥናት እና ምርምር ተቋም ባለሙያው ዶክተር ፓኦሎ ካምፓና ለውይይት የቀረበው ይኸው ሰፋ ያለ ጥናት ከ 4 ዓመታት በፊት በርካታ የኤርትራ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ስደተኞችን ጭኖ ሲጓዝ  የኢጣሊያ ላምፔዱሳ ደሴት የባህር ሰርጥ ሰጥሞ 360 ተሳፋሪዎች በአሳዛኝ ሁኔታ ያለቁበትን ክስተት መነሻ ያደረገ ነው :: ዶክተር ፓኦሎ ዜናው ከተሰማ በኋላ የኢጣልያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ግብረሃይል ቡድንን አነጋግረዋል :: በህይወት የተረፉ ስደተኞችንም ጠይቀዋል :: ሰዎችን ከሃገር ሃገር በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ራሳቸውን በዓለም ዙሪያ በኔትዎርክ ያደራጁ የማፍያ ድርጅቶችን እና ወንጀለኞችንም ግለ ታሪክ ለማጥናት ሞክረዋል :: ባለሙያው በጥናታቸው ያረጋገጡትን ለዶቸቨለ ገልጸዋል ::" የአፍሪቃ ስደተኞችን ከሃገር ሃገር ለማጓጓዝ ራሱን በኔትዎርክ ያደራጀው ዓለማቀፉ የማፍያዎች እና ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች ዋና መናኸሪያ የሆነችው ሱዳን ነች :: ወንጀሉ ከዛ ነው የሚጀምረው :: መድረሻው ደግሞ ስዊድን  መሆኑን በጥናት ደርሰንበታል :: "

በአፋኝ መንግስታት ጭቆና መንስኤም ይሁን የተሻለን ኑሮ ፍለጋ ከሃገር ሃገር የሚደረገው አሰቃቂው እና ህገወጡ የሰዎች ዝውውር ሰብአዊ መብት የሚረገጥበት የሰው ልጅ ክብር የሚዋረድበት ግለሰቦች ያለፍላጎታቸው የሚደፈሩበት መሆኑን ነው ካምፓና የስረዱት :: ከዜህ ሌላ ለበርካታ ቀናት የሚላስ የሚቀመስ እንዲሁም ህክምና እና መጠለያ ጭምር አጥተው ሲንገላቱ የቆዩ

ስደተኞች ተጨማሪ የገንዘብ ክፍያ እየተጠየቁ በአደባባይ በግፍ የሚገደሉበት ከነህይወታቸው ባህር ውስጥ የሚወረወሩበት በርካቶች በባርነት እና በጉልበት ብዝበዛ የሚማቅቁበት አምራች ወጣት ዜጎች ሳይቀሩ የባህር እና የበረሃ ሲሳይ ሆነው የትም ወድቀው የሚቀሩበት በአንጻሩ ግፈኞች እና ወንጀለኞች የገቢ ምንጫቸው አድርገው የተንደላቀቀ ኑሮ የመሰረቱበት መሆኑ ችግሩን አሳሳቢም አሳዛኝም ያደርገዋል ይላል የባሙያው ጥናት :: ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ 20 ሺህ ስደተኞች የጣሊያንን ድንበር ሲሻገሩ 20 ሺህ የሚገመቱት ደግሞ በጉዞው ወቅት ህይወታቸውን እንዳጡም በጥናቱ ተመልክቷል ::በእንዲህ አይነቱ እንግልት ተስፋን ሰንቀው በአጋጣሚም ይሁን በእድል የባህር እና የበረሃ ጉዞ የቀናቸው ስደተኞች የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰለባ የሚሆኑበት አጋጣሚው ሰፊ መሆኑን  ተመራማሪው ዶክተር ፓኦሎ ያስረዳሉ ::
" በአሮጌ እና አስተማማኝ ባልሆኑ መርከቦች ለቁጥር የሚታክቱ ስደተኞችን ጭኖ በባህር ላይ የሚደረግ ጉዞ እጅግ አደገኛ ነው :: ብዙን ጊዜ የመርከቦች የቴክኒክ ብልሽት እና የባህር ላይ ወንበዴዎች ድንገተኛ ጥቃት ስለሚያጋጥም በየእለቱ ብዙ ተጓዥች ህይወታቸውን ያጣሉ :: በስደት እና ህመም የተንገላቱ አቅመ ደካሞቹም እንዲሁ በቀላሉ ባህር ውስጥ ወድቀው ይሞታሉ :: በአጠቃላይ የህይወት አድን ሰራተኞችን ጨምሮ ወንጀልን እና የባህር ላይ ውንብድናን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች ቁጥር አናሳ መሆኑ ጉዞውን ይበልጥ አደገኛ ያደርገዋል "

ዶክተር ፓኦሎ ካምፓና በጥናታቸው ማጠቃለያ በስደተኞች ላይ የሚፈጸምን ግፍ ለመከላከል እና ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞችን ድርጊት ለመዋጋት ይጠቅማሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ጠቁመዋል :: የመጀመሪያው በአደገኛውን የበረሃ እና የባህር ጉዞ የሚከሰተውን የሰዎች እልቂት ለማስቀረት ግጭቶች እና ፍልሰቶች በሚኖሩባቸው ሃገራት አቅራቢያ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያዎችን ማጠናከር ነው :: ተመራማሪው ሌሎች መፍትሄዎችንም ሰንዝረዋል :: 

" በሙስና በተዘፈቁ እና ሰብአዊ መብትን በሚጥሱ መንግስታት ተማረው ስደት የሚወጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም :: እንደ አውሮፓ ህብረት የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅቶች እንዲሁ ዩናይትድስቴትስን የመሳሰሉ ለጋሾች ከቀረጥ ከፋዩ ሰብስበው የሚለግሱት ገንዘብ በእንደነዚህ ዓይነቶቹ አፋኝ መንግስታት እጅ እንዳይገባ ጥረት ማድረግ አለባቸው :: ገንዘቡ ለታሰበለት የልማት እና የሰብአዊ አገልግሎት ላይ መዋሉንም ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል :: "
 
እራሱን በዓለም ዙሪያ በኔትወርክ ያደራጀው ድንበር የለሹ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ የማፊያዎች ቡድን እ. ኤ.አ በ2015 ዓ. ብቻ ከስደተኞች እና ከቤተሰቦቻቸው ከ 6ቢልዮን ዶላር በላይ ማጋበሱን የዶክተር ፓኦሎ ጥናት ያትታል::  የአውሮፓውያኑ የፖሊስ ተቋም - አውሮ-ፖል ከሁለት ዓመታት በፊት ከቱርክ መንግስት ጋር ባደረገው ውል እና ሥምምነት የማፍያ ቡድኑ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ የሚያሸጋግርበት መስመር መቋረጥም በጥናቱ ተመልክቷል ::
እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic