የሰዎች ለሰዎቹ ካርልሃንዝ በኸምና ሽልማታቸዉ | ኢትዮጵያ | DW | 05.09.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሰዎች ለሰዎቹ ካርልሃንዝ በኸምና ሽልማታቸዉ

ላለፉት 26ዓመታት በኢትዮጵያ በግብረ ሰናይ ተግባር ተሰማርተዉ ሰፋ ያለ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ የሚገኙት Menchen für Menchen ማለትም የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሪ ካርል ሃይንትዝ በኸም ላደረጉት ጥረት ሽልማት አገኙ።

ካርል ሃይንዝ በኽም

ካርል ሃይንዝ በኽም

ሽልማቱን የሰጣቸዉ በዙሪክ ስዊትዘርላንድና በሚላን ጣሊያን ፅህፈት ቤት ያለዉ የባልዛን ድርጅት ነዉ። በኸም ላደረጉት ግብረ ሰናይ ጥረት ያገኙት ሽልማቱ የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ነዉ።

የቀድሞዉ ኦስትሪያዊ የፊልም ሰዉ በግብረ ሰናይ ተግባር ከተሰማሩ ዓመታት ነጉደዋል። ካርል ሃንይንዝ በኸም ሰዎች ለሰዎች የተሰኘዉን ድርጅት በመመስረት በኢትዮጵያ ባደረጉት እንቅስቃሴም የክብር ዜግነት ያገኙ የአገልግሎታቸዉ ተጥቃሚ የሆኑ ወገኖችም አባታችን በማለት የሚያወድሷቸዉ ሆነዋል። ለእሳቸዉ የገንዘብ ሽልማቱን የሰጠዉ ድርጅት ዓለም ዓቀፍ ባልዛን የተሰኘዉ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በሳይንሳዊ ምርምር ዉጤት ላሳዩም ሆነ ለሰላም ትርጉም ያለዉ ስራ ለሰሩም ሲሰጥ ቆይቷል። ከአዉሮፓዉያኑ 1981ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ የጀመረዉ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በተለይ በጀርመን ታዋቂ በሆነዉ Wetten, dass በተሰኘዉ የZDF ቴሌቪዥን ፕሮግራም ለአፍሪቃ የእርዳታ ማሰባሰብ ሃሳባቸዉን ካቀረቡ በኋላ ነዉ።

አሁን ያገኙት ሽልማት የተሰጣቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተሰማሩበት ግብረ ሰናይ ተግባር ባሳዩት የስራ ዉጤት ነዉ። በስጦታዉ የተደሰቱት ካርል ሃይንዝ በኸም በምንም መንገድ ቢሆን የሚያገኙት ገንዘብ መግቢያዉ አንድ፤ የሚዉለዉም የአገሬ ህዝብ ለሚሉት ወገን መሆኑን ነዉ የሚናገሩት፣

«በጥቅሉ የምለዉ መቶ በመቶ እዉነታዉን ነዉ። ከጀርመንም ሆነ ከስዊዝ፤ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ከሚኖሩ ወገኖች የምናገኘዉ የእርዳታ ገንዘብ የሚሄደዉ ወደአንድ ማዕከል ነዉ። ያ ባይሆን ኖሮ ለቢሮክራሲዉ ብዙዉ ገንዘብ በከፈልን ነበር። በኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበዉ ዘገባ እንደሚጠቁመዉ እድሜያቸዉ ለትምህርት ከደረሰ ህፃናት ልጆች መካከል ለመማር የሚችሉት ከግማሽ በታች ናቸዉ። ስለዚህ የእኛ ዋነኛዉ ትኩረት ትምህርት ቤት መገንባት ሆኗል።»

በመንግስት ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ እድሜያቸዉ ለትምህርት ከደረሰ ልጆች መካከል የመማር እድሉን ሊያገኙ የሚችሉት ገሚሱን እንኳ እንደማይሆኑ ነዉ። ይህን መሰሉ እዉነታ ደግሞ ካርል ሃይንዘ በኸምን ያስደነቀ ብቻ ሳይሆን ያሳዘነም ሆኗል። ግንባር ቀደም ያደረጉትም ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንደሆነ የሚገልፁት በኽም የመጀመሪያ፤ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሊሰጥባቸዉ የሚችሉ የ173 ትምህርት ቤቶች ግንባታ በድርጅታቸዉ መጠናቀቁን ጨምረዉ ገልፀዋል። ከኢትዮጵያ ህፃናት መካከል 53.7በመቶዉ ትምህርት ያለማግኘታቸዉ ሁኔታም ከህብረተሰቧ መካከል ግማሹ ታዳጊ በሆነባት እንደኢትዮጵያ ባለችዉ አገር ልጆች በትምህርት ካልታነፁ በምን መልክ ልታድግ ትችላለች የሚለዉ ጥያቄም እንዳስጨነቃቸዉ በኽም ይናገራሉ፣
«እንዴትስ ነዉ ወደፊት መሄድ የሚቻለዉ? ስለዚህ በእዉነቱ ለእኔ ትምህርት ቤቶችን መገንባት አማራጭ የሌለዉ ቀዳሚ ነገር ነዉ። በዚህ ረገድም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ መተባበሩም በጣም ጥሩ ነዉ።»

በኸም እንደገለፁት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ካስገነባቸዉ ትምህር ቤቶች በተጓዳኝ ለመምህራንና ለቤተሰቦቻቸዉ መኖሪያም ሰርቷል። ድርጅቱ ለሚያከናዉናቸዉ ተግባራት ማስፈፀሚያ የሚዉለዉን ገንዘብ የሚያገኘዉ ከተለያዩ ሀገራት በተለይ ደግሞ ከጀርመን፤ ኦስትሪያና ስዊዝ በጎ አድራጊ ኗሪዎች ነዉ። በተለያዩ ጊዜያትም ድርጅቱ ለጋሾቹ ባሉባቸዉ ስፍራዎች የሚያከናዉናቸዉ የቅስቀሳም ሆነ የፍሬ ማሳያ ዝግጅቶች አሉት። ከዚህ መካከል ሰሞኑን እዚህ ጀርመን ዉስጥ የሚያቀርበዉ የጎዳና ላይ ትርኢት አንዱ ነዉ።
«በእነዚህ በሶስቱ ሀገራት ማለትም በጀርመን፤ በኦስትሪያና በስዊዝ የሚገኘዉ ህዝብ ለእኛ ድርጅት ልገሳዉን የሚሰጠዉ በእምነት በመሆኑ በገንዘቡ ምን እንደተሰራበት በተቻለ መጠን በተለያዩ መንገዶች ሁሉ ልናሳዉቅ እንፈልጋለን። ነገሩ እንደሌላዉ የምታኔ ሃብት ድጋፍ ሁሉ እያንዳንዷ ሳንቲም የምትሄድበትን ደጋግሞ የመመልከት ብቻ ሳይሆን ለእኔ ትልቁና የማምንበት ነገር እያንዳንዱም ሆነ እያንዳንዷ ለጋሽ ምን እንደተሰራ ማወቅመፈለጉ አይቀርምና የጎዳናዉን ትርኢት መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነዉ»

በጎዳናዉ ትርኢትም ፕሮጀክቱ በተለያዩ ስፍራዎች ያከናወናቸዉን ተግባራት የሚያሳይ በፎቶ የተደገፈ አዉደ ርዕይ ማለትም ኤግዚቢሽን ይኖራል። እዉቁ የአፍሪቃ በተለይም የኢትዮጵያ ወዳጅ የ79 ዓመቱ ካርል ሃይንዝ በኸም የተሰጣቸዉ ሽልማት ላደረጉት ተግባር ማበረታቻ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም በጀመሩት ጎዳና ለመግፋት ያላቸዉን ፅኑ እምነት ገልፀዋል።