የሰው ንክኪ የማይፈልገው የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 04.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የሰው ንክኪ የማይፈልገው የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን

የፈጠራ ስራዎች የሰዎችን ህይወት ከማሻሻል ባለፈ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሀገር ውስጥ የፈጠራ አቅምን መጠቀም ጥቅሙ የጎላ ነው። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን ከፈጠረ አንድ ወጣት ቆይታ ያደርጋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:05

የሰው ንክኪ የማይፈልገው የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን

የሰዎችን የዕለት ተዕለት ህይወት በማሻሻል ረገድ የፈጠራ ስራዎች  የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይለም።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የፈጠራ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።ወጣት አብርሃም ወልደአረጋይ ከነዚህ መካከል አንዱ ነው።ወጣቱ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ  ተመርቆ እንደወጣ ላለፉት አምስት አመታት በፈጠራ ስራ መቆየቱን ይናገራል።በአዲስ አበባ ከተማ አብየነት ኢንጅነሪንግ በተባለ የዲዛይንና የማምረቻ ድርጅት በስራ አስኪያጅነትም ይሰራል። በፈጠራ በቆየባቸው አምስት አመታት ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግል አሳንሰር እንዲሁም ለኮቪድ-19 ፅኑ ህሙማን መተንፈሻ ቬንትሌተርን  ጨምሮ አራት  የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሰው ንክኪ የማይፈልግ ዘመናዊ  የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን መስራቱንና በዚሁ የፈጠራ ስራ  የእውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱን ገልጾልናል።ለመሆኑ አዲሱ ፈጠራ ከዚህ በፊት ከነበሩ የእንጀራ መጋገሪያዎች በምን ይለያል?

«የኔ ፈጠራ ለየት የሚያደርገው እንጀራን በዘመናዊ መንገድ ለመጋገር ከዚህ በፊት የነበሩ ማሽኖች ትንሽ አስቸጋሪ ነበሩ። አንደኛ ማሽኑ የሚፈለገውን የእንጀራ ቁጥር ተሰጥቶት ማሽኑ እንዲሰራ ለማድረግ ነው።ሊጡን አንዴ ከሰጡት በኋላ ተጀምሮ እስኪያልቅ ራሱ ዕቃ አጥቦ እንዲሰጥ ነው።ራሱ የሚያስፈልገውን «ቴምፕሬቸር» ይመጥናል።የእንጀራ ቁጥር ግን ሰዎች እንዲሰጡት ተደርጎ የተሰራ ነው።»

ይህ ማሽን እንጀራውን የሚጋግረው በአራት ማዕዘን ቅርፅ ሲሆን የእንጀራውን ውፍረት እንደየ ሰው  ፍላጎት ለማስተካከልም ያስችላል።ማሽኑ ይህንን የሚከዉንበት ሶስት ደረጃዎችም አሉት።

«ማሽኑ ሶስት ደረጃዎች አሉት አንደኛው የመጀመሪያው ሊጡን የሚያፈስበት ወደ ምጣዱ የሚገባበት።ሁለተኛው ምጣዱ የሚያበስልበት ሶስተኛ እንጀራውን የሚያወጣበት »ስቴጅ» አለው።ያ ነገር በ«ኤለክትሮኒክ» በተደግፈ መልኩ መብሰሉን ተመራምሮ ሙቀትን ራሱ ሲበዛ ሲጨምር ተቆጣጥሮ ሲያንስ «ኮንትሮል» ያደርጋል።የእንጀራዉን ውፍረት መጀመሪያ ሰዎች «አጀስት» ያደርጉታል።ከሰጡት በኋላ የእንጀራውን ቁጥር የሚፈልጉትን ይሰጡታል ያንን ካደረጉ በኋላ ስራውን ራሱ ይሰራል።ሊጥም ሲያልቅ «አላርም» ያደርጋል።»

 እንጀራ በኢትዮጵያ በአብዛኛ ህዝብ ዘንድ የዕለት ተዕለት ምግብ ነው።ከሀገር ወጥተው ባሀር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይቀር እንጀራ ከምግብ ዝርዝራቸዉ ዉስጥ ጠፍቶ አያውቅም።የእንጀራና የኢትዮጵያውያንን ቁርኝት በመመልከት ይመስላል ዘ ስታርስ የተሰኘ  ጋዜጣ  በስድስት ደቂያ ንባብ  አምዱ ስር  በጥቅምት 2018 ዕትሙ  እንጀራ ከኢትዮጵያውያን ህይወት ጋር በእጅጉ የተዛመደና ምናልባትም ለሺህ አመታት አብሮ የዘለቀ ምግብ ሳይሆን አይቀርም ሲል አስፍሯል።ይህ  በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ በየዕለቱ የሚዘወተር ምግብ ታዲያ  ስራው  ብዙ ሂደት የሚያልፍና አድካሚ ነው።ይህ ስራ   በተለምዶ ለሴቶች ብቻ የተተወ በመሆኑም በእነሱ የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ያለው ጫና ቀላል አይደለም።ያም ሆኖ  አሰራሩን ቀላልና ዘመናዊ  እንዲሁም ጉልበትና ጊዜ ቆጣቢ ለማድረግ ብዙ ስራ  አልተሰራበትም። ለወጣቱ የፈጠራ ባለሙያም  መነሻው ይሄው ነው።

ማሽኑ ለጊዜው በኤለክትሪክ የሚሰራ ቢሆንም የኤለክትሪክ መብራት በሌለባቸው  አካባቢዎች እንዲሰራ የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።ማሽኑን ለመጠቀም የተለዬ እውቀት የማይጠይቅ ሲሆን በቀላሉ ለመስራትና አንብቦ ለመረዳት  በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ስለ አሰራሩ መመሪያ አብሮ መዘጋጀቱንም ይገልፃል።

የእንጀራ መጋገሪያው ማሽን ተመጥኖ የተሰጠውን ሊጥ ከማስፋት ጋግሮ እስከማስቀመጥ ያለውን ሂደት ያለ ሰው ንክኪ  የሚያከናውን ሲሆን ሊጡን ወደ ማሽኑ ማስገባትና የተጋገረዉን እንጀራ ወደ ሚፈለግበት ቦታ ማስቀመጥ ብቻ በሰው የሚከወን ነው ።ያ በመሆኑ  ፈጣንና ጊዜ ቆጣቢ መሆንም ያስረዳል።

የፈጠራ ስራዎች የሰዎችን ህይወት ከማሻሻል  ባለፈ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሀገር ውስጥ የፈጠራ አቅምን መጠቀም ይመከራል።ያም ሆኖ በኢትዮጵያ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማቃለል የሚረዱ በርካታ የፈጠራ ውጤቶች  በገንዘብ እጥረት ወደ ተግባር አለመቀየራቸው ተደጋግሞ ይሰማል።ይህ ችግር አብርሃምን ካልያዘው  የፈጠራ ስራውን በመጭው መስከረም ለተጠቃሚ ለማድረስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጾልናል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጨነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic