የሰዉ ንግድ | አፍሪቃ | DW | 16.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሰዉ ንግድ

በወጣቶቹ የሚነግዱትን ለፍርድ ለማቅረብ ሰወስተኛዉና ከባዱ ምክንያትም እዚያዉ ደቡብ ናይጄሪያ ያለዉ እምነት ነዉ። ጁጁ-ይሉታል እነሱ። ጥንቆላ ነዉ። ሴቶቹ ለሚወስዳቸዉ ሰዉ ታማኝ ሆነዉ ካልሰሩና የሚፈለግባቸዉን ገንዘብ ካልከፈሉ እነሱ ወይም የሚወዱት ሰዉ እንደሚሞት ጠንቋዩ ያስጠነቅቃቸዋል። ጠንቋዮችም የጥቅሙ ተካፋይ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:26

የሰዉ ንግድ

ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ 2015 ዓመት ከአራት ሺሕ የሚበልጡ የናይጄሪያ ዜጎች የሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠዉ ኢጣሊያ ገብተዋል። አብዛኞቹ ሥደተኞች በሰዉ ለሚነግዱ ደላሎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ከፍለዉ ወይም ለመክፈል ቃል ገብተዉ አዉሮጳ የገቡ ናቸዉ። ሰዎችን በተለይ ወጣቶችን ከአፍሪቃ ወደ አዉሮጳ የማስገባቱ ምግባር ብዙ ትርፍ የሚገኝበት ንግድ ሆኗል። የአዉሮጳም ሆኑ የአፍሪቃ መንግሥታትም በሰዉ የሚነግዱ ወገኖችን ይዘዉ ለፍርድ አቅርበዉ አያዉቁም። በዚሕም ምክንያት ያን ፊሊፕ ሾልስ እና አድሪያን ኪርሽ እንደሚሉት ሰዉ የማሸጋገሩ አትራፊ ንግድ እንደቀጠለ ነዉ። ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የፍሎሬንስ-ኢጣሊያዊቱ አቃቢት ሕግ አንጌላ ፒትሮይስቲ ሥራ በዝቶባቸዉ ቢሯቸዉ ካመሹ ሁሌም የሚያዩት ትርዒት ነዉ። ጨለምለም ሲል በመስኮታቸዉ አሻግረዉ ሲመለከቱ ከአዉራ ጎዳናዉ ግራ ቀኝ ፈንጠር፤ ፈንጠር እያሉ ይደረደራሉ። ሴቶች ናቸዉ። ወጣቶች። ኢጣሊያ ዉስጥ አርባ ሺሕ የዉጪ ሐገር ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ ይገመታል። ከአዉሮጳ-የሩሜንያ፤ ከአፍሪቃ ደግሞ የናጄሪያ ዜጎች ከፍተኛዉን ቁጥር ይይዛሉ።

ሁሉም የሰዉ አሸጋጋሪ ሰለቦች ናቸዉ። በተለይ ናጄሪያዉያኑን ለሴተኛ አዳሪነት የሚያስኮበልሉት አብዛኞቹ በዚሁ ሥራ የከበሩ ሴቶች ናቸዉ። «ማዳም» ይሏቸዋል። አቃቢት ሕግ ፒትሮይስቲም ይሕን ያዉቃሉ አንድም «ማዳም» ግን ለፍርድ አልቀረቡም። በሁለት ምክንያት።«ተበዳዮቹ ፖሊስን በጣም ሥለሚፈሩ መረጃ አይሰጡም።»

ምክንያት ሁለት፤-«ከፍተኛ የሆነ የአስተርጓሚ ችግር አለብን። የአነጋገር ቅላፄያቸዉ ጠንካራ ሥለሆነ የሚሉትን በትክክል የሚተረጉምልን ሰዉ የለም።»

አብዛኞቹ ቤኒን ሲቲ የተባለችዉ የደቡብ ናይጄሪያ ከተማና አካባቢዋ ተወላጆች ናቸዉ። በወጣቶቹ የሚነግዱትን ለፍርድ ለማቅረብ ሰወስተኛዉና ከባዱ ምክንያትም እዚያዉ ደቡብ ናይጄሪያ ያለዉ እምነት ነዉ። ጁጁ-ይሉታል እነሱ። ጥንቆላ ነዉ። ሴቶቹ ለሚወስዳቸዉ ሰዉ ታማኝ ሆነዉ ካልሰሩና የሚፈለግባቸዉን ገንዘብ ካልከፈሉ እነሱ ወይም የሚወዱት ሰዉ እንደሚሞት ጠንቋዩ ያስጠነቅቃቸዋል። ጠንቋዮችም የጥቅሙ ተካፋይ ናቸዉ።

የቀድሞዋ የሰዉ አሻጋሪ ሠለባ ጆይ ኬ ግን ተጨማሪ ምክንያት አለ ባይነች። ግፉን የሚፈፀመዉም የሚፈፀምባቸዉም በዉጪ ሐገር ተወላጆች ነዉ። የኢጣሊያ መንግስት ዜጎቹ ሥለማይነኩ ጉዳዩን ከቁብ አይቆጥረዉም። ጆይ በ17 ዓመቷ በልጅ አሳዳጊነት ትሠሪያለሽ ብለዉ ወደ ኢጣሊያ አመጧት። ላንዲት ማዳም አስረከቧት። ማዳም «አንቺን ለማስመጣት 30 ሺሕ ዩሮ ስላወጣሁ እሱን ለመክፈል መሥራት አለብሽ» ብላ ጎዳና ላይ ገተረቻት። የኢጣሊያ ፖሊስ ይዞ ወደ ሐገሯ መለሳት።

«ለፍርድ እንዲቀርቡ እፈልጋለሁ። የኢጣሊያ እና የናጄሪያ መንግሥታት ይሕን ለማስቆም መጣር አለባቸዉ። የኔ ማዳም ብቻ አይደለችም። ከኔ ማዳም የባሱ መጥፎ ማዳሞች አሉ።»

ትላለች ዘንድሮ 23 ዓመቷ። ሰዉን የሚያሸጋግሩት የተለያዩ ትናንሽ ቡድናት ናቸዉ። ማሸጋገሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ የሚዛቅበት ንግድ ሆኗል። አብዛኞቹ የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ ሜድትራኒያን ባሕር የሚያሻገሩባት አጋዴዝ የተባለችዉ የኒዠር ከተማ አለቅጥ ደምቃለች። ሰባት ባንኮች ቅርንጫፍ ከፍተዉባታል። የገንዘብ መለዋወጫ ሱቆች ደግሞ እንደ አሸን ፈልተዉባታል። ደላሎቹን የሚቆጣጠር የለም። የአጋዴዝ አገረ-ገዢ መሐመዱ ፎዴ ካሜራ እንደሚሉት መንግስታቸዉ ሁሉንም ለመቆጣጠር አቅም የለዉም።

«የበረሐዉ ጉዞ አደገኛ ሲሆን ወይም በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበራችን መጣሱን ስናዉቅ እና ተጓዦቹ ወጣቶችን ለሴተኛ አዳሪነት እያሻገሩ መሆኑን ስንደርስበት ስደተኞቹን እንይዛለን። ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ግን ባሁኑ ወቅት መሣሪያዉ የለንም።»

መፍትሔዉ በርግጥ ግልፅ አይደለም። ዛሬ ቤኒን ሲቲ የምትኖረዉ የቀድሞዋ ሴተኛ አዳሪ ጆይ ኬ ግን በሷ የደረሰዉ በሌሎች እንዳይደግም የምችለዉን ሁሉ አደርጋለሁ ትላለች።

«ናይጄሪያ ዉስጥ ኑሮ ቀላል እንዳልሆነ አዉቃለሁ። ባሕር ማዶም ለኛ ቀላል አይደለም። ከአንድ ሰዉ ጋር ብቻ አይደለም የሚተኛዉ፤ በየሌሊቱ ከ15 እስከ 18 ሰዉ ጋር መተኛት ግድ ነዉ። ሥለዚሕ ሁሉንም ማዳን አለብኝ። ናይጄሪያ ዉስጥ የፈለገዉን ያክል ከባድ ቢሆንባቸዉም ከወዲያ ማዶዉ እንደማይብስ ማወቅ አለባቸዉ።»

ይሳካላት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic