የሰወስቱ ሐገራት አብዮት ድቀት | ዓለም | DW | 20.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሰወስቱ ሐገራት አብዮት ድቀት

ግብፆች ሕይወት፥ ደም አካላቸዉን መስዋዕት ያደረጉበት አብዮት የምክር ቤት እንደራሴዎቻቸዉን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በነፃ እንዲመርጡ አስችሏቸዋል።ፕሬዝዳታቸዉንም እንደዚሑ።ሕገ-መንግሥትም አፅድደቀዋል።ዳር ግን አልዘለቀም።ከ1952 ጀምሮ የግብፅን የሚቆጣጠረዉ ጦር ሐይል የግብፅ ሠላማዊ ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት እንዲሳካ ሥልጣኑን መልቀቅ አልፈቀደም።

Ägypten Wahlen

ግብፅ


በዘር አረብነት፥ በአሐጉር አፍሪቃዊነት የሚያስተሳስራቸዉ አንድ ናቸዉ።ግን ድንበር አስተዳደር የሚለያቸዉ ሰወስት ሐገራት።ደግሞ ሕዝባዊ አብዮት በማስተናገድ አንድ ሆኑ።ቱኒዚያ፥ ሊቢያ እና ግብፅ።የሕዝባዊ አብዮቱ አጀማመር፥ ሒደትና ግቡ ግን ያለያቸዋል።እንደገና አብዮቱ ከመክፍሽ አፋፍ መድረሱ አንድ ያደርጋቸዋል።ዘንድሮ ሰሞኑን ሰወስተኛ ዓመታቸዉ።የአንድም፥ ሰወስትም፥ ሐገራትን አንድ ሕዝባዊ አብዮት ብዙ ሒደት የመጨናገፍ ዉጤቱን ተመሳሳይ ላፍታ እንቃኛለን።አብራችሁኝ ቆዩ።

ጥር አስራ-አራት 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)።መሐመድ ቡአዚዚ እራሱን አንድዶ ቱኒዚያ ላይ ያቀጣጠለዉ አብዮት ከሃያ-ስምንት ቀናት ጠንካራ ሕዝባዊ ሰልፍ፥ ትግል መስዋዕትነት በኋላ «ከአኩሪ» ዉጤት ደረሰ።የቱኒዚያ የሃያ-ሰወስት ዓመት ገዢ ሥልጣን፥ ሐብት፥ ሐገራቸዉን ጥለዉ ኮበለሉ።«መዓሠላማ» ዘይን ኤል አቢዲኒ ቤን ዓሊ።ቱኒዝ በደስታ ቦረቆች።

አስራ-አንድ ሚሊዮን የማይሞላዉ የቱኒዝያ ሕዝብ ከዚያ የደረሰዉ የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት፥ ደም አካል ገብሮ ነዉ።ሕዝባዊ አብዮቱ ከተጀመረበት ከታሕሳስ ማብቂያ ቤን ዓሊ ከሥልጣን እስከተወገዱበት በተቆጠሩት ሃያ ስምንት ቀናት የቤን ዓሊ ታማኝ ወታደሮችና ታጣቂዎች አራት መቶ ያሕል ሰላማዊ ሠልፈኞችን ገድለዋል።ከሁለት ሺሕ በላይ አቁስለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አስረዋል።

የቤን ዓሊ ታማኞችን ጥቃት፥የሕዝባዊ አብዮቱን ምስቅልቅል ሒደት የፈሩ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ቱኒዚያዉያን አንድም ተሰደዋል።አለያም ከየቤታቸዉ ተፈናቅለዋል።

Tunesien / Tunis / Revolution / NO-FLASHእርግጥ ነዉ ቤን ዓሊ ከተወገዱበት እስካለፈዉ ሳምንት በተቆጠረዉ ሰወስት ዓመት ቱኒዚያዎች ባደረጉት ተመሳሳይ የአደባባይ ሠልፍ የቤን ዓሊ ታማኞችን ከሥልጣን አስወግደዋል።ነብሰ ገዳዮች፥ ጉቦች፥ ሙሰኞችን ለፍርድ አቅርበዋል። አስፈርደዉባቸዋልም። የመጀመሪያዉን ነፃ ምርጫ አስተናግደዋል።በምርጫዉ ሥልጣን የያዙት ወገኖች የአብዮቱን ዓለማ፥ የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት ለማሟላት እየጣሩ መሆናቸዉን ይናገራሉ።

«አብዮቱ ተጨባጭ ለዉጥ እና እድገት እንዲያመጣ ማንኛዉም መንግሥት ቢሆን አመታት ያስፈልጉታል።በተለይ እኛ አምስት አስርታት ከቆየ አምባገነናዊ ሥርዓት ገና መላቀቃችንን ከግምት ማስገባት ይገባል።»

ከጥቂት ወራት በፊት የመሐመድ ቡአዚዚን የትዉልድ ከተማ የጎበኘዉ የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደዘገበዉ ግን የሕዝቡ ስሜት ባለሥልጣናቱ ከሚሉት የሚቃረን ነዉ። ቱኒዚያዎች የሚፈልጉትን ነፃነት፥ የታገሉ፥ የሞቱ የቆሰሉለትን ፍትሐ፥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሠርትላቸዉ፥ የሥራ እድል የሚፈጥርላቸዉ ፖለቲከኛ እስካሁን አላገኙም።

ሕዝቡ የሚፈለገዉ ሥርዓት ሊመሠረት ቀርቶ ከሚፈልገዉ ሥርዓት የሚያደርሳቸዉ አቅጣጫ የመቀየሱ ጭላንጭል እንኳን አይታይም።እንደ ቡዓዚዚ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ድግሪ ይዞ የዕለት ጉርሱን ለማሟላት አትክልት ፍራፍሬ ለመቸርቸር የተገደደዉ የሲዲ ቡዛዲ ወጣት መሐመድ ተሒድ እንደሚለዉ ደግሞ ለሱና ለብጤዎቹ የተለወጠ ነገር የለም።

«መሐመድ ቡአዚዚ እራሱን አቃጥሎ የተጀመረዉ አብዮት እድገት ብልፅግና ያመጣል የሚል ተስፋ ነበረን።በሙስና የተዘፈቁ ዋልጌ ባለሥልጣናትን ያስወግዳል፥ ጉቦና ኢፍትሐዊነትን ያጠፋል የሚል እምነት ነበረን።ግን ተሳስተናል።የተለወጠ ነገር የለም።

ለቤን ዓሊ ሥርዓት ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ዶላር ሲያንቆረቁሩ የነበሩት ሐያላን መንግሥታትም በሕዝብ ድምፅ የተመረጡ መሪዎችን ሐይማኖታዊ-ፖለቲካዊ አቋም ከማብጠልጠል ባለፍ የሕዝባዊ አብዮቱን ጅምር ዉጤት ለማጠናከር የፈየዱት ነገር የለም።ቱኒዚያ።

Proteste in Tunesien gegen israelische Luftangriffe im Gazastreifen

ቱኒዚያ

የግብፅ ሕዝብ ለታላቁ ሕዝባዊ አብዮት አደባባይ መታደም የጀመረዉ የቱኒዚያዉ የሃያ-ሰወስት ዘመን አምባገነን ገዢ ቤን ዓሊ ከሥልጣን በተወገዱ በአስራ-አንደኛዉ ቀን ነበር።ጥር ሃያ-አምስት ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ።ተሕሪር አደባባይ።ጠንካራ፥ ሐይለኛ፥ ጨካኙን የግብፅ ገዢ ከሥልጣን ለማስወገድ ዕለታት በቂ ነበር።የካቲት አስራ-አንድ።የቀድሞዉ የአየር ሐይል ማርሻል፥ የሰላሳ ዘመኑ አምባገነን ገዢ ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ተወገዱ።

«ከፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸዉ ለቀዋል።የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥልጣኑን ይይዛል።ፈጣሪ ይባርካችሁ።»

የያኔዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዑመር ሱሌይማን።ለአስራ-ስምንት ቀናት በሕዝብ ቁጣ ሲንተከተክ የነበረዉ ታሕሪር አደባባይ በደስታ-ሲቃ ፈነደቀ።አስራ-ስምንቱ ቀናት ለተቃዉሞ ሠልፍኛዉ፥ የአደባባይ ሠልፍ ጊዜ ብቻ አልነበረም፥- የግጭት፥ ግድያ፥ የድብደባ፥ ዝርፊያ የመደፈሪያ ጊዜ ጭምር እንጂ። ሙባረክ ለመሰዋት የተዘጋጀዉን ሕዝባቸዉን አመፅ ማቆም እንደማይችሉ ተገንዘበዉ ሥልጣን እስከለቀቁበት ድረስ በትንሽ ግምት ስምንት መቶ ሐምሳ ሰዉ አስገድለዋል።ከስድስት ሺሕ አራት መቶ በላይ አስቆስለዋል።አስራ-ሁለት ሺሕ አስረዋል።ሕዝባዊዉን ማዕበል መግታት ግን አልቻሉም።

ግብፆች ሕይወት፥ ደም አካላቸዉን መስዋዕት ያደረጉበት አብዮት የምክር ቤት እንደራሴዎቻቸዉን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በነፃ እንዲመርጡ አስችሏቸዋል።ፕሬዝዳታቸዉንም እንደዚሑ።ሕገ-መንግሥትም አፅድደቀዋል።ዳር ግን አልዘለቀም።ከ1952 ጀምሮ የግብፅን ፖለቲካዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ፥ ማሕበራዊ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረዉ የግብፅ ጦር ሐይል የግብፅ ሠላማዊ ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት እንዲሳካ ሥልጣኑን መልቀቅ አልፈቀደም።

ሙባረክ የሾማቸዉ የግብፅ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች አዲሱን ምክር ቤት አግደዉ ሕዝቡ በድምፁ የመረጣቸዉን እንደራሴዎች በትነዉ ነበር።በአደባባይ ሠልፍ የሰላሳ ዘመኑን ፈርዖናዊ ሥርዓት የገረሰሰዉ ሕዝብ የርዝራዦቹን ዉሳኔ ለማስቀልበስ ዳግም መሠለፍ ግድ ነበረበት።

የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ እስኪቀለበስ ድረስ፥ ጦር ሐይሉ ሌላ ሙከራ አደረገ።የሙባረክ ታማኞች በፕሬዝዳንታዊዉ ምርጫ ሥልጣን እንዲይዙ የቀድሞዉን ማርሻል አሕመድ ሻፊቅን አሠልፉ። እንደ ምክር ቤቱ ሁሉ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር የመሠረተዉ የነፃነት እና የፍትሕ ፓርቲ እጩ መሐመድ ሙርሲ አሸነፉ።ሆስኒ ሙባረክ ሥልጣን ከለቀቁበት መሐመድ ሙርሲ ሥልጣን እስከያዙበት ድረስ በሥልጣን ላይ የነበረዉ ወታደራዊ ምክር ቤት ለተቃዉሞ አደባባይ የወጡ ከሰወስት መቶ በላይ ሰዎችን ገድሏል።አራት ሺሕ ያሕል አስሯል።

ያም ሆኖ የምክር ቤቱ መሪ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊ እንዳሰቡት ጦር ሐይሉ ሥልጣኑን እንደያዘ መቀጠል አልቻለም።ጦሩ ከግማሽ ምዕተ-ዓመታት በላይ ይዞት የነበረዉን ሥልጣን እንደገና የሚይዝበትን ብልሐት የሚያብሰለስል መሪ ግን በርግጥ አላጣም ነበር።ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲ።ድምፃቸዉን አጥፍተዉ ሲያደቡ፥ ተገቢዉን ጊዜ ሲያሰሉ ቆይተዉ ሐምሌ ሰወስት ላይ አጠቁ።መፈንቅለ መንግሥት።

ጄኔራሉ ለመከላከያ ሚንስትርነት የሾሟቸዉን፥ በሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን አስወግደዉ አሠሩ።በሕዝብ የተመረጠዉን ምክር ቤት አገዱ።በሕዝብ የፀደቀዉን ሕገ-መንግሥት ሻሩ።ጄኔራል አል-ሲሲ እንደመጋረጃ ያቆሙት ጊዚያዊ መንግሥት መንፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙትን ሠላማዊ ሠልፈኞች ባደባባይ በጥይት ያጭድ ገባ።

Libyen / Panzer / Kämpfe

ሊቢያካለፈዉ ሐምሌ እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ በትንሽ ግምት አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰዉ ተገድሏል። በሺሕ የሚቆጠር ቆስሏል።አብዛኞቹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር አባላት ናቸዉ።የማሕበሩ መሪዎችና ደጋፊዎች በገፍ እየታፈሱ ታስረዋል።ተፈርዶባቸዋልም።የማሕበሩ ሐብት ንብረቶች ተወረሱ። ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፥ጽሕፈት ቤቶች ተዘጉ።በሕዝባዊ አብዮት ከሥልጣን የተወገደዱት፥ ምናልባት ግምት ለስምት መቶ ሐምሳ ሰዎች ሞት ተጠያቂ የሆኑት ሙባረክ ባንፃሩ ከወሕኒ ቤት ተለቀዉ በቁም እስረኝነት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸዉ።

ሙባረክ ከሥልጣን የተወገዱበት ሰወስተኛ ዓመት ሊዘከር ሳምንታት ሲቀሩት ትናንት ዕሁድ ጄኔራል አልሲሲ የሰየሙት መንግሥት ያስረቀቀዉ አዲስ ሕገ-መንግሥት ፀደቀ።ለረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ድምፅ የሰጠዉ ሕዝብ፥ ድምፅ መስጠት ከሚችለዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ሰላሳ ስምንት ከመቶዉ ብቻ ነዉ።ሰማንያ አምስት ሚሊዮን ከሚገነተዉ የግብፅ ሕዝብ ከሐምሳ ሚሊዮን የሚበልጠዉ ድምፅ መስጠት ይችላል ተብሎ ይገመታል።


«እንደሚመስለኝ ድምፅ ለመስጠት የወጡትና ለረቂቁ ይሁንታቸዉን የሰጡት አብዛኞቹ ግብፆች አመፅ ሁከቱ የሰለቻቸዉ፥ መረጋጋት የሚፈልጉ ናቸዉ።ሐገሪቱ ሙባረክ ከተወገዱ በሕዋላ ካላባራ አለመረጋጋት ዉስጥ እንደተዘፈቀች ነዉ።ሕዝቡ በተለይ በዕለት ከዕለት ኑሮዉ እያየለ በመጣዉ የወንጀለኞች ዘረፋና ጥቃት ተሰላችቷል።»

ይላሉ ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኝ ዮርግ ታይልማን።ችግር አስገድዶት የጄራል ሲሲን ረቂቅ ሕገ-መንግሥት ለማፅደቅ አደባባይ ከወጣዉ ሕዝብ ከዘጠና ስምንት ከመቶ በሚበልጠዉ ረቂቁን አፅድቋል።

ሕገ-መንግሥቱ የሴቶችን እኩልነት፥ የማሕበራዊ መብትን በማስከበር ረገድ፥ በፕሬዝዳት ሙርሲ ዘመን ከነበረዉ ሕገ-መንግሥት የተሻለ የሚባል ነዉ።በሙርሲ ዘመን የፀደቀዉን ሕገ-መንግሥት የሚቃወሙት ወገኖች ደጋግመዉ ያነሱት የነበረዉ እና ለሲሲ መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ የሆነዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር የሚመራዉ መንግሥት ያፀደቀዉ ሕገ-መንግሥት እስልምና የግብፅ የበላይ ሐይማኖት እንዲሆን ያዛል በሚል ነበር።

ሊቢያ

ታይልማን እንደሚሉት ትናንት በዘጠና ስምንት ከመቶ የድጋፍ ድምፅ የፀደቀዉ ሐይማኖትን በተመለከተ ከቀድሞዉ በብዙ መልኩ የተለየ አይደለም።

«የተወሰኑት ልክ እንዳለፈዉ ናቸዉ።እንዳለፈዉ ሕገ-መንግሥት ሁሉ በዚሕኛዉም ሕገ-መንግሥት እስልምና የሐገሪቱ መንግሥት ሐይማኖት ነዉ።ሸሪዓ የሕጎች ሁሉ ምንጭ ነዉ።በ(ፕሬዝዳት) ሙርሲ ዘመን በሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት በፀደቀዉ ሕገ-መንግሥት በአንዳድ አንቀፆች በግልፅ ተጠቅሶ የነበረዉ የሸሪዓ መርሆች ባሁኑ ሕገ-መንግሥት ተበታትኖ በተለያዩ ሥፍራዎች በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሷል።»

ከሁሉም በላይ አዲሱ ሕገ-መንግሥት ጦር ሐይሉን ለምክር ቤትም፥ለሥራ-አስፈፃሚዉ ተጠያቂነት የሌለበት ብቸኛ ተቋም ያደርገዋል።ይሕ ማለት ጦር ሠራዊቱ «የመንግሥት ዉስጥ መንግሥት» የመሆን ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ይኖረዋል።የግብፅ አብዮት ፍፃሜ ይሆን?

የሊቢያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የቤንጋዚ ሕዝብ የአርባ ሁለት ዓመት ገዢዉን በመቃወም አደባባይ የወጣዉ የቱኒዚያዉ አምባገነን ገዢ ከሥልጣን በተወገዱ በሰወስተኛ ሳምንቱ፥ ሙባረክ ሥልጣን እንደለቀቁ ነበር።የካቲት መጀመሪያ።የሊቢያ አብዮት በርግጥ እንደ ሁለቱ ጎረቤቶቹ ከሕዝባዊነቱ ይልቅ ጎሳዊነቱ፥ ከወስጣዊነቱ ይልቅ ዉጪያዊነቱ፥ ከሠላማዊነቱ ይበልጥ ጦርነታዊነቱ የጎላ ነበር።

ከዋሽግተን እስከ ሪያድ፥ ከፓሪስ እስከ ዶሐ፥ ከለንደን እስከ አንካራ ሐብታም፥ ሐያላንን ለዉጊያ ያሳደመዉ፥ አብዮት ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት የተቀየረዉም በቅፅበት ነበር።በጦርነቱ ሐብታሚቱ ሐገር ወድማለች።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት ገብራለች።የአርባ ሁለት ዓመቱ ገዢዋ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፍን ከተማረኩ በሕዋላ ባደባይ አስረሽና ከነ-ሥርዓታቸዉ ቀብራለች።ዛሬም በሰወስተኛ ዓመቷ ዋዜማ ግን ጦርነት ላይ ናት።የጎሳ ታጣቂዎች፥ ወሮበሎች የፈለጉትን ግዛት እየቆረሱ የየራሳቸዉን ትናንሽ ነገስታት መሥርተዉባታል።

ሰሞኑን የጠናዉ የሊቢያን የባሕር ዳርቻ ግዛት እና የነዳጅ ዘይት ማምረቻ ተቋማትን በተቆጣጠሩ ታጣቂዎች እና ከትሪፖል ሌላ ሌሎች አካባቢዎችን ማስተዳድር ባልቻለዉ ጊዚያዉ መንግሥት ጦር መካካል የሚደረገዉ ዉጊያ ነዉ።እና ብዙ የተነገረ፥ ብዙ ተስፋ የተጣለበት፥ ብዙ ሕዝብ ያለቀ፥ የተሰደደበት፥ ሕዝባዊ አብዮት ወይም ዓለም አቀፋዊ ጦርነት፥ ብልጣብልጦችን ቤተ-መንግሥት ከመዶሉ ባለፍ ለሰወስቱ ሐገራት ሕዝብ ከሌላ ጥፋት ባለፍ እስካሁን የተከረዉ የለም።ሥለ ማሕደረ ዜና ያላችሁን አስተያየት ላኩልን ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ


Audios and videos on the topic