1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2016

እንግሊዝ በጁድ ቤሊንግሀም እና ሔሪ ኬን በባከነ ሰአት የተቆጠሩ ግቦች ከጉድ ተርፋለች ። ጀርመንን ያንገዳገደችው ስዊትዘርላንድ በሩብ ፍጻሜ ትጠብቃታለች ። ጀርመን እንደተፈራው ለሩብ ፍጻሜ ከስፔን ጋ ደርሶታል ። ከደጋፊዎቹ ነቀፌታ የቀረበበት የፈረንሳይ ቡድን ከቤልጂየም ጋ እየተፋለመ ነው ። ማን አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፍ ይሆን?

https://p.dw.com/p/4hkYE
ከአፍሪቃዊ ቤተሰቦች የተወለደው ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር በጀርመንና ዴንማርክ ግጥሚያ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተሰይሟል
ከአፍሪቃዊ ቤተሰቦች የተወለደው ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር በጀርመንና ዴንማርክ ግጥሚያ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተሰይሟል ምስል Christian Charisius/dpa/picture alliance

ለአውሮጳ እግር ኳስ ሩብ ፍጻሜ ማን ይደርስ ይሆን?

እንግሊዝ በጁድ ቤሊንግሀም እና ሔሪ ኬን በባከነ ሰአት የተቆጠሩ ግቦች ከጉድ ተርፋለች ። ሦስቱ አናብስት የማታ ማታ በጠንካሮቹ ስሎቫኪያዎች ተሰናብተው ታሪክ ሊቀየርም ነበር ። ጀርመንን ያንገዳገደችው ስዊትዘርላንድ በሩብ ፍጻሜ ትጠብቃታለች ። ጀርመን እንደተፈራው ለሩብ ፍጻሜ ከስፔን ጋ ደርሶታል ። ከደጋፊዎቹ ነቀፌታ የቀረበበት የፈረንሳይ ቡድን ከቤልጂየም ጋ እየተፋለመ ነው ። ማን አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፍ ይሆን?  

እግር ኳስ

በጀርመን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ በአጓጊነቱ እንደቀጠለ ነው ። ለዋንጫ ሲጠበቁ የነበሩት ጣሊያኖች ባልተጠበቀ መልኩ ሩብ ፍጻሜ ሳይገቡ ተሰናብተዋል ። ቅዳሜ ዕለት ጣሊያንን ያሰናበተችው ቀደም ሲል ከጀርመን ጋ አቻ የተለያየችው ስዊትዘርላንድ ናት ። ስዊትዘርናልድ ጣሊያንን 2 ለ0 ጉድ አድርጋ ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች ። እንደ ስዊትዘርላንድ ሁሉ ጀርመንም  ቅዳሜ ዕለት ዶርትሙንድ ከተማ ውስጥ በቦሩስያ ዶርትሙንድ ሜዳ ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ዴንማርክን ገጥማ 2 ለ0 ድል አድርጋለች ። ጨዋታው በጀመረ 35ኛው ደቂቃ ላይ የዶርትሙንት ሰማይ ተከፍቶ ነጎድጓዳማ ዶፍ ያወርደው ጀመር ። ለ25 ደቂቃ ግድምም ጨዋታው ሊቋረጥ ግድ ነበር ።

በማሸነፍ ጉጉት ብርቱ ትግል ያደረጉት ዴንማርኮች በ48ኛው ደቂቃ ላይ በዮአኺም አንደርሰን ቀዳሚ ግብ ቢያስቆጥሩም በቪዲዮ ረዳት ዳኛ ተጣርቶ ግን ግቡ ተሽሯል ። ለጀርመን ደጋፊዎች ታላቅ እፎይታ ። ብዙም ሳይቆይ 52ኛው ደቂቃ ላይ የመሀል ዳኛው የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ውሳኔን በቪዲዮ ለመልከት ተገደው ነበር ። በዚህ ጊዜ ግን የጀርመን ቡድን ነበር ፍጹም ቅጣት ምት ያገኘው ። በዚህ ጊዜም ቀደም ሲል ግቡ የተሻረበት ምስኪኑ ዮአኺም አንደርሰን ነበር የፍጹም ቅጣት ምቱ ሰበብ ።

ዶርትሙንድ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ሜዳ ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም  መዳረሻ ድልድይ
ዶርትሙንድ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ሜዳ ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም መዳረሻ ድልድይምስል Mantegaftot Sileshi/DW

53ኛው ደቂቃ ላይ ጀርመናዊው ካይ ሐቫርትስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ጀርመን ዴንማርክን 1 ለ0 መምራት ጀመረች ። ዶርትሙንድ ስታዲየም አካባቢ ተገኝተን እንደተመለከትነው ከሆነ ግቡ የጀርመን ተጨዋቾችንም ሆነ ደጋፊዎች አስፈንዝዟል ። በዚህ ጨዋታ የጀርመን አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን ቢጫ ካርድ ዐይተዋል።  68ኛው ደቂቃ ላይ ጃማል ሙሲያላ ያስቆጠራት ግብ ዴንማርኮች በድንጋጤ ፀጥ ያስባለ ነበር ።  ጀርመን ዴንማርክን 2 ለ0 ባሸነፈችበት የምሽቱ ጨዋታ ከአፍሪቃዊ ቤተሰቦች የተወለደው ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተሰይሟል ።

እንግሊዝ ከጉድ ተርፋለች

ትናንት ማታ በነበረው እና የእንግሊዙ ጁድ ቤሊንግሀም የምሽቱ ምርጥ ተጨዋችች ተብሎ በተሰየመበት ሌላ ግጥሚያ እንግሊዝ በትግል ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች ። በዚህ ጨዋታ ቀዳሚውን ግብ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረችው ስሎቫኪያ ነበረች ። ምናልባትም ጨዋታውን ስሎቫኪያ 1 ለ0 ልታሸንፍ ነው በሚል የእንግሊዝ ደጋፊዎችን በጥፍራቸው ያቆመ ግጥሚያ ነበር ። መደበኛው ጨዋታ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ግን ጁድ ቤሊንግሀም የተሻማለትን ኳስ አየር ላይ አክሮባት ሠርቶ በግሩም ሁኔታ እንዲሁምሐሪ ኬን በንቅላት በመግጨት ከመረብ በማሳረፍ አሸንፈዋል። የእንግሊዝ ቡድን በተራዘመው ጨዋታ 2 ለ1 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ ችሏል ።

እንግሊዝ ስሎቫኪያን 2 ለ1 አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ እንድታልፍ ያስቻሉት ጁድ ቤሊንግሀም የእና ሔሪ ኬን
እንግሊዝ ስሎቫኪያን 2 ለ1 አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ እንድታልፍ ያስቻሉት ጁድ ቤሊንግሀም የእና ሔሪ ኬን ምስል Bernadett Szabo/REUTERS

ቅዳሜ ዕለት ስዊትዘርላንድ ጣሊያንን 2 ለ0 አሸንፋ ሩብ ፍጻሜ ሳታደርስም አሰናብታታለች ። ስፔን አጀማመራቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ያስባላቸው ጆርጂያዎችን 4 ለ1 ሸንታለች ። በሩብ ፍጻሜው ከአዘጋጇ ጀርመን ጋ የፊታችን ዐርብ ሽቱትጋርት ውስጥ ይፋለማሉ ። በዛሬው ጨዋታ ከፈረንሳይ እና ቤልጂየም እንዲሁም ከፖርቹጋል እና ስሎቬኒያ አሸናፊ ወደ ሩብ ፍጻሜው ይገባል ።

ፈረንሳይ ወይንስ ቤልጂየም?

ፈረንሳይ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከቤልጂየም ጋ ዛሬ እየተጋጠመች ነው  ። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የፈረንሳይ ቡድን አቋምን በተመለከ የፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህን በስልክ አነጋግሬያታለሁ ። የፈረንሳይ ቡድን ከምድብ «መ» ከአውስትሪያ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በያዘው አምስት ነጥቡ ሁለተኛ ሆኖ ነው ያጠናቀቀው ። በምድብ ማጣሪያው  ባደረጋቸው ጨዋታዎች፦ ከኔዘርላንድ ጋ ያለምንም ግብ ሲለያይ፤  ከፖላንድ ጋ ደግሞ አንድ እኩል ወጥቶ ነበር  ። ማሸነፍ የቻለው ኦስትሪያን ሲሆን እሱንም 1 ለ0 በሆነ ጠባብ የግብ ልዩነት ነበር ። ሐይማኖት፦ የፈረንሳይ ቡድን ወቅታዊ አቋምን በተመለከተ የመገናኛ አውታሮች እና የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ምን እያሉ ነው?

ሐይማኖት ለሰጠሽን ማብራሪያ በአድማጮች ስም ከልብ አመሰግናለሁ ። ፈረንሳይ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ ከቻለች፦ የምትጋጠመው ከፖርቹጋል እና ስሎቬንያ አሸናፊ አለያም ከጀርመን እና ስፔን ከአንዱ ጋ ይሆናል ። አሁን ባለው ሁኔታም ምናልባት ለፍጻሜ መድረስ ከቻለች ቤርሊን ውስጥ እንግሊዝን ልታገኛትም ትችል ይሆናል ።

በነገው ዕለት ደግሞ ሮማኒያ ከኔዘርላንድ እንዲሁም አውስትሪያ ከቱርክ ጋ ተጋጥመው ወደ ሩብ ፍጻሜ አላፊዎች ይለያሉ ።

የጀርመን እና የዴንማርክ ደጋፊዎች ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ስታዲየም አቅራቢያ
የጀርመን እና የዴንማርክ ደጋፊዎች ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ስታዲየም አቅራቢያምስል Mantegaftot Sileshi/DW

አትሌቲክስ፥

ለ23ኛ ጊዜ በተካሄደውን የአፍሪቃ አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች ። ካሜሩን ውስጥ ከሚገኙ ትልልቅ ከተሞች አንዷ በሆነችው ዱዋላ ኢትዮጵያ በ32 ሴት እና በ36 ወንድ አትሌቶች በ21 የአትሌቲክስ የውድድር ተሳትፋ ነው የአራተኛ ደረጃ ያገኘችው ።

ኢትዮጵያ ውጤት ያስመዘገበችባቸው ውድድሮች የተካሄዱት፦ በ1500 ሜትር ሴቶች፤ በ3000 ሜትር መሠናክል ሴቶች፤ በ5000 ሜትር ወንዶች፤ በ400 ሜትር መሠናክል ሴቶች፤ በከፍታ ዝላይ ወንዶች፤ በስሉስ ዝላይ ሴቶች፤ በጦር ውርወራ ወንዶች እንዲሁም በ4X400 ሜትር ሪሌ ወንዶች ነበር ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር