1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 10 2016

የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ዳሰሳ አድርገናል ። ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ስለሚካሄደው የቤልጂየም እና ስሎቫኪያ ግጥሚያን በተመለከተ ስለከተማው እና ደጋፊዎች ድባብ ከፍራንክፉርት ወኪላችን ጋ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። ስፔን ውስጥ በተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ መምረጫ ውድድር ስለተገኘው ውጤትም መረጃዎችን አካተናል ።

https://p.dw.com/p/4h94a
Deutschland Berlin 2024 | Pokal-Präsentation zur Fußball-EM
ምስል Juergen Engler/nordphoto GmbH/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የአውሮጳ እግር ኳስ መክፈቻ ውድድርን በአስደማሚ ውጤት ጀምሯል ። ረቡዕ ከሐንጋሪ ጋ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ያከናውናል ። እንግሊዝ በሠርቢያ ተፈትና እንደምንም አሸንፋለች ። ጣሊያን እና ስፔን እንደተጠበቁት ለድል በቅተዋል ። ለዋንጫ ከሚጠበቁ ሃገራት መካከል ቤልጂየም እና ፈረንሳይም ዛሬ ማታ የመጀመሪያ ግጥማያቸውን በተከታታይ ያከናውናሉ ። ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ስለሚካሄደው የቤልጂየም እና ስሎቫኪያ ግጥሚያን በተመለከተ ስለከተማው እና ደጋፊዎች ድባብ ከፍራንክፉርት ወኪላችን ጋ ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። ስፔን ውስጥ በተካሄደው  የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ መምረጫ ውድድር ስለተገኘው ውጤትም ዳሰሳ አድርገናል ።

እግር ኳስ

ጀርመን በሳምንቱ መጨረሺያ ላይ በመክፈቻው አስደማሚ ድል ያስመዘገበችበት የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ በዚህ ሳምንትም ቀጥሏል ። ዐርብ ዕለት በነበረው ግጥሚያ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ፍሎሪያን ቪርትስ እና ጃማል ሙሳይላ በተለይ ድንቅ ብቃታቸውን ዐሳይተውበታል።  ፍሎሪያን ቪርትስ ለዘንድሮ የአውሮጳ እግር ኳስ ቀዳሚ ሆና የተመዘገበችውን ግብ በ21 ዓመቱ ከመረብ በማሳረፍም በአውሮጳ ፉክክር በዕድሜ ትንሹ በመሆን ታሪክ ሠርቷል ።  ቀደም ሲል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2021 በዕድሜ ትንሽ ሆኖ በአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ያስመዘገበው የሀገሩ ልጅ ካይ ሐቫርትስ ነበር፤ በ22 ዓመቱ ። 

ፍሎሪያን ቪርትስ እና ጃማል ሙሳይላ በመክፈቻ ጨዋታው ብርቱ አጥቂ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ ተመልሰው ከተከላካይ መስመር ኳስ በመቀበልም ብርታታቸውን ዐሣይተዋል ።  በተለይ ፍሎሪያን እንደ ብዙዎቹ አጥቂዎች ከፊት መስመር ሆኖ ኳስ ከመጠበቅ ወደ ኋላ እየተመለሰም ኳሶችን በመቀበል ብቃቱን አስመስክሯል ።

ጃማል ሙሳይላ እና ፍሎሪያን ቪርትስ ከስኮትላንድ ጋ ባደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ ብቃታቸውን ዐሣይተዋል
ጃማል ሙሳይላ እና ፍሎሪያን ቪርትስ ከስኮትላንድ ጋ ባደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ ብቃታቸውን ዐሣይተዋልምስል Mika Volkmann/IMAGO

ጀርመን እንደ ጎርጎሮዮስ አቆጣጠር ከ2006 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የመክፈቻ ውድድሯን በድል ጀምራለች ። እናም ሁለቱ አጥቂዎች ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ የጀርመን ቡድን እንደ አጀማመሩ ከቀጠለ ከምድቡ ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ይችላል ። ጀርመን በመቀጠል ረቡዕ ዕለት ከሐንጋሪ ጋ ሽቱትጋርት በሚገኘው ኤምሐፔአ አሬና ስታዲየም ይጋጠማል ።

በአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ሰሞን የጀርመን ድባብ

ጀርመን 51ዱን የአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታዎች የምታስተናግድባቸው ዐሥር ስታዲየሞች ከሚገኙባቸው ከተሞች መካከል አንዱ ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ያለው የዶይቸ ባንክ ስታዲየም ተጠቃሽ ነው ። ንብረትነቱ የአይንትራኅት ፍራንክፉርት የሆነው ስታዲየም 58,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው ። የዛሬውን የቤልጂየም እና የስሎቫኪያ ጨዋታ ለማስተናገድ የተመረጠውም ይኸው ስታዲየም ነው ። ለመሆኑ የተመልካቾች ድባብ ከስታዲየሙ ውጪ ምን ይመስላል? የፍራንክፉርት ወኪላችን መሳይ ወንድሜነህ በፍራንክፉርት አም ማይን ወንዝ ዳርቻ ወደ ተዘጋጁ የመዝናኛ ስፍራዎች በማቅናት የጨዋታ ድባቡን ተመልክቷል ። ፍራንክፉርት የቤልጂየም እና ስሎቫኪያ ጨዋታን ዛሬ ስታስተናግድ ድባቡ ደማቅ እና ሰላማዊ እንደነሆነ ገልጧል ። 

እሁድ ሰኔ 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም  እንግሊዝ ሠርቢያን በትግል 1 ለ0 ካሸነፈች በኋላ የሁለቱ ሃገራት ጨዋታው በተካሄደበት የጌልዘንኪርሸ ከተማ ውስጥ ደጋፊዎች እርስ በእርስ በመጣላት አምባጓሮ ማስነሳታቸው ድባቡን አደብዝዞት ነበር ። ምግብ ቤት ውስጥ ሰዎች በወንበር እየተወራወሩ ሲጣሉም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተሰራጭቷል ። ከተማዋ ውስጥ ማለዳ ላይ የነበረውን የደጋፊዎች ጸብ በእርግጥ ፖሊስ ደርሶ አብርዶታል ። ፍራንክፉርት ውስጥ ደጋፊዎች በጋራ ጨዋታውን የሚከታተሉበትን ሥፍራ የጎበኘው መሳይ «እንደውም የተለያዩ ደጋፊዎች በጋራ ያሳዩ የነበረው ሰላማዊ ስሜት መሳጭ ነበር» ብሏል ።

በተለያዩ ምድቦች የእስካሁን ውጤቶች

በምድብ «ሠ» ሩማንያ ዩክሬን ዛሬ 3 ለ0 ድል አድርጋለች ። ከዚሁ ምድብ ቤልጂየም ከስሎቫኪያ ጋ እየተጋጠሙ ነው ። ምድብ «መ» ውስጥ የሚገኙት ፈረንሳይ እና ኦስትሪያ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ይጋጠማሉ ። ከምድቡ ኔዘርላንድ ፖላንድን ትናንት 2 ለ1 አሸንፋለች ።

የቤልጂየም ከስሎቫኪያን ጨምሮ አምስት ጨዋታዎች በፍራንክፉርት
ፍራንክፉርት ከተማ የቤልጂየም እና የስሎቫኪያን ጨምሮ አምስት ጨዋታዎችን ታስተናግዳለች ምስል Florian Gaul/picture alliance

ጀርመን በመክፈቻ ጨዋው ዐርብ ዕለት ስኮትላንድን 5 ለ1 ጉድ አድርጋለች ። ሌላኛዋ የምድብ «ሀ» ተጋጣሚ ስዊትዘርላንድ ቅዳሜ ዕለት ሐንጋሪን 3 ለ1 ስታሸንፍ፤ ከምድብ «ለ» ተጋጣሚዎች መካከል ስፔን ክሮሺያን 3 ለ0 ድል አድርጋለች ። ጣሊያን ብርቱ ተፎካካሪ ሆና የቀረበቻትን አልባኒያን 2 ለ1 አሸንፋለች ። ከምድብ «መ» ኔዘርላንድም በተመሳሳይ የ2 ለ1 ልዩነት ፖላንድን ትናንት አሸንፋለች ። በምድብ «ሐ» ታሸንፋለች ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ዴንማርክ በስሎቬኒያ ተፈትና በስተመጨረሻ አንድ እኩል ተለያይታለች ።

ከአጠቃላዩ የአውሮጳ እግር ኳስ ተጋጣሚ ሃገራት መካከል በተናጠል ምርጥ ተጨዋቾችን በማሰለፍ ተፎካካሪ የማይገኝላት እንግሊዝ ሠርቢያ እጅግ ፈትናታለች ። በዕለቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው ጁድ ቤሊንግሀም በጭንቅላት ገጭቶ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ ከጉድ ወጣች እንጂ የሠርቢያ አያያዝ ለእንግሊዝ ብርቱ ፈተና ደቅኖ ነበር ። በተለይ በተክለ ሰውነታቸው ገዘፍ ያሉት የሠርቢያ ተጨዋቾች የአካል ብቃት የበላይነታቸውን እና ረዣዥም ኳሶችን በመጠቀም እንግሊዝን አስጨንቀዋል ።

በምድብ «ረ» የሚገኙት ቱርክ እና ጆርጂያ በነገው ዕለት ይጫወታሉ ። ከሁለቱ ጨዋታ በኋላ በተመሳይ ምድብ ውስጥ የሚገኙት ፖርቹጋል እና ቼክ በሚያደርጉት ጨዋታም የአጠቃላዩ ምድቦች የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ይጠናቀቃሉ ። 

የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን
ከአጠቃላይ የአውሮጳ እግር ኳስ ተጋጣሚ ሃገራት መካከል በተናጠል ምርጥ ተጨዋቾችን በማሰለፍ ተፎካካሪ የማይገኝላት የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንምስል Action Foto Sport/NurPhoto/picture alliance

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ማጠቃለያ ትናንት በሀዋሳ ከተማ ተከናውኗል ። በፍፃሜው ኢትዮጵያ ቡና መቻልን 6-5 አሸንፎ የውድድሩ ባለ ድል ሆኗል ። ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ በመለያየታቸው አሸናፊው በመለያ ምቶች ነው የተለየው ። ለደረጃ የተደረገው ጨዋታም ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ በመለያ ምቶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 6-5 አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።  የሰኔ 3 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አትሌቲክስ

በስፔን ኔርሀ በተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ መምረጫ የአትሌቲክስውድድር በ10000 ሜትር የወንዶች ውድድር ዮሚፍ ቀጄልቻ 1ኛ ሆኖ አጠናቀቀ ። ሚኒማ  ማሟያ ሰአት 27 ደቂቃ ሲሆን። ዮሚፍ ውድድሩን ያጠናቀቀቅ  26፡31.01 በመሮጥ ነው ። በሪሁ አረጋዊ (26፡31.13) 2ኛ ደረጃን አግኝቷል ። ሰለሞን ባረጋ (26፡34.93) 3ኛ  ሲወጣ፤ ቢኒያም መሃሪ (26:37.93) 4ኛ እንዲሁም ገመቹ ዲዳ (26:42.65) 5ኛ፤ ታደሰ ወርቁ (26:46.80) 6ኛ ደረጃን ይዘዋል ።

በተመሳሳይ ርቀት የሴቶች ፉክክር በተቀመጠው (30:40.00) ሚኒማ በማሟላት ፎትዬን ተስፋይ (29፡47.71) 1ኛ ወጥታለች ። ፅጌ ገብረሰላማ (29፡49.33) 2ኛ፤ እጅጋየሁ ታዬ (29፡50.52)3ኛ ፤ እንዲሁም አይናዲስ መብራቱ (30.09.05) 4ኛ ደረጃ ወጥተዋል ።

ሚኒማ 3:33.50 በተያዘበት የ1500 ሜትር ርቀት የወንዶች ፉክክር አትሌት አብዲሳ ፈይሳ (3:32.37) 1ኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሳሙኤል ተፈራ (3:32.81) 2ኛ እንዲሁም ታደሰ ለሚ 3:33.84 3ኛ ደረጃ አግኝቷል ። እስከ 13ኛ ደረጃ ያገኙ ተፎካካሪዎች ሚኒማውን ያሟሉ ናቸው ። ኤርሚያስ ግርማ 3:34.88 5ኛ፤ መልክነህ አዘዘ 3:35.77 6ኛ ፤ መለስ ንብረት 3:36.78 7ኛ፤ ኩማ ግርማ 3:37.25 8ኛ፤ ወገኔ አዲሱ 3:37.65 9ኛ፤ አዳህነ ካሳዬ 3:37.68 10ኛ፤ አዲሱ ግርማ 3:38.23 13ኛ ።  የወንዶች 800 ሜትር ሚኒማ ለማሟላት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም ። 800 ሜትር ወንዶች /ሚኒማ 1:44.70 ነበር ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ