የሰብዓዊ መብቶች ተስፋና ስጋት በኢትዮጵያ  | ኢትዮጵያ | DW | 27.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሰብዓዊ መብቶች ተስፋና ስጋት በኢትዮጵያ 

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ረኣድ አል ሁሴን በኢትዮጵያ ያለዉን የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የአራት ቀን ጉብኝታቸዉን ትናንት አጠናቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:45

ሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ 

ከእሁድ ጀምሮ ባደረጉት ጉብኝትም ከከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ እንዲሁም በቅርብ ከእስር ከተፈቱ ወገኖች ጋር ተገናኝተው በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር መሾማቸዉን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይሻሻላል የሚል ተስፋ መሰነቁ፤ በተቃራኒዉ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ሌሎች አፋኝ ሕጎች በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ አሁንም ስጋት መደቀኑን ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ካገኟቸው ሰዎች መረዳት እንደቻሉም ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ዘይድ፣ «በጣም ደስ የሚል ጉብኝት ነበር። ብዙ ሰዎችን እንዳዳምጥ ዕድል ሰጥቶኛል። በኦሮሚያ ክልል ከአባገዳዎች ጋር ተገናኝቻለዉ። በምልከታቸዉም ቀጥተኛ ነበሩ። በጣም ገርሞኝ ነበር። ምክንያቱም የመንግሥት ተወካዮች ከኛ ጋር ነበሩ። ግን ይሄም አባገዳዎቹን የተሰማቸዉን ለመናገር አልገደባቸዉም። ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያላቸዉን አድናቆት ከገለፁ በኋላ እሳቸዉ ቃል የገቡት ላይ ተስፋ ጥለዋል። በተቃራኒዉም ያገኘኋቸዉ ሰዎች ያላቸዉን ስጋት ገልፀዋል። በቅርቡ ከእስር የተፈታ ግለሰብ ቀደም ሲልም የተሰበረ/የታጠፈ ቃል ሰለቦች ስለሆኑ አሁንም ጭንቀት እንዳላቸዉ ነግሮኛል። አባ ገዳዎችም ሆኑ ከእስር የተፈቱት የሚናገሩት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መመርመር እንዳለበት፣ ከመጠን በላይ ኃይል ለሚጠቀሙ ተጠያቂነት ሊኖራቸዉ እንደሚገባና አፋኝ ሕጎች ዳግም መከለስ እንዳለበት ነዉ።»

 የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀማቸዉ፣ የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የፍትሕ ስርዓቱ ገለልተኛ አለመሆናቸዉ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነ ለመረዳት መቻላቸዉንም ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ዘይድ ረኣድ አል ሁሴን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። በቅርቡ ከእስር የተፈቱት በእስር በቆዩባቸዉ ጊዜያት ያጋጠማቸዉን እንዲያጋሯቸዉ ግለሰቦቹን ትላንት አግኝተው እንደነበር ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ዘይድ አክሎበታል።

ዘይድ፣ «ማለት ያለበኝ፣ የሰማኋቸዉ አንዳንድ ነገሮች አስፈሪ ናቸዉ። በጣምም ቅር የሚያሰኝ ነው። ከእስር መለቀቃቸዉ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ (ስልጣን ሲረከቡ) ያደረጉት ንግግርና አቀራረባቸዉ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ግን ተስፋው ጥንቃቄ ያልተለየው ተስፋ ነው።»

በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሚገኘዉ አዳራሽ ዉስጥ ትላንት እንደተሰበሰቡና ስብሰባዉም ከሁለት ሰዓት በላይ እንደፈጀ ተሳትፈዉ የነበሩት እና በቅርብ ከእስር የተፈታው በፍቃዱ ኃይሉ ለዶይቼ ቬሌ ገልጿል። ተሳታፊዎች እስር ላይ በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸዉን ለኮሚሽነሩ መናገራቸዉን በፍቃዱ እንዲህ ሲል ይጠቅሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ቢሮዉን ለመክፈት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ትናንት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ለዶይቼ ቬሌ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል። ቢሮዉን መክፈታቸዉ በአገሪቱ ያለዉን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በቅርበት ለመከታተል እንደሚያስችላቸዉም ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የተነሱት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመንግሥት ፖሊስ ዉስጥም ቦታ እንደሚጥሩም ገልጸዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ 

Audios and videos on the topic