የሰብዓዊ መብት ይዞታ በአፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 24.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሰብዓዊ መብት ይዞታ በአፍሪቃ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው አመታዊ ዘገባ የአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ይዞታ በሰላማዊ ሰልፈኞች፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ላይ በሚፈጸሙ የታቀዱ ጥቃቶች የተሞላ መሆኑን አትቷል። ዘገባው እንደሚለው ረዥም ጊዜ ባስቆጠሩ ግጭቶች ሰላማዊ ሰዎች የማያቋርጥ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:08

ኢትዮጵያና ኤርትራ ስቅየት ከሚፈጽሙት ጎራ ተጠቅሰዋል

በዓለም ዙሪያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እያሽቆለቆለ መሆኑን የሚጠቁም አመታዊ ዘገባውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሐሙስ ይፋ አድርጓል። 159 አገሮችን የፈተሸው ዘገባው መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም አሊያም ሲፈጸም በቸልታ በማለፍ "በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መብቶች አመንምነዋል" ሲል ኮንኗል። 

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 የአፍሪቃ አገሮችን አካቷል። በመላው ዓለም የታየው የሰብዓዊ መብት ይዞታ ማሽቆልቆል በአፍሪቃ ይብስ እንደሁ እንጂ የተሻለ ግን አይደለም። "አኅጉሪቱ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃት የሚጸምባት፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚታሰሩባት እና የሚከሰሱባት ሆና ቀጥላለች። ሁለተኛው እና አሳሳቢው ጉዳይ የደም አፋሳሽ ግጭቶች ተፅዕኖ መቀጠል ነው" የሚሉት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ነፃነት በላይ ናቸው። 

አቶ ነፃነት "አንጎላ፣ ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ቶጎን ጨምሮ ከ20 በላይ በሚሆኑ አገሮች ሰዎች የመቃወም መብታቸውን ሲነፈጉ ታዝበናል። ከ30 በላይ በሚሆኑ አገሮች ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ገደብ ተጥሎባቸዋል። በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና አቀንቃኞች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሲፈምም ተመልክተናል። በካሜሩን የሲቪክ ማኅበራት አራማጆች እና የሰራተኛ ማሕበራት መሪዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ በኤርትራ በሺሕዎች የሚቆጠሩ አራማጆች ዛሬም እስር ላይ ናቸው" ሲሉ ያክላሉ። እንደ ኃላፊው ገለጻ በአፍሪቃ መሪዎች ለተቃውሞ ትዕግስት ማጣታቸው እየጨመረ መምጣቱን ለማሳየት የዘንድሮው ዘገባ እንደምሳሌ የጠቀሳቸው በርካታ አገሮች አሉ። 

ኢትዮጵያ በሰላማዊ ተቃውሞዎች ላይ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ አሊያም ሌላ ገደብ ከጣሉ አገራት ጎራ ተሰልፋለች። ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ተደንግጎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጅምላ ታስረው እንደነበር የአምነስቲ ዘገባ አስታውሷል። አምነስቲ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሪታኒያ፣ ናይጄሪያ እና ሱዳን ስቅየትን መሰል ተግባራት ይፈፅማሉ የሚል ጥቆማ እንደደረሰውም አትቷል። 

አምነስቲ በዘገባው እንዳለው ረዥም ጊዜ ለዘለቁ ግጭቶች ዓለም አቀፍ እና የየቀጣናው አካላት መፍትሔ ማጣታቸው የዘፈቀደ ግድያና ኹከቶችን አባብሷል። ድህነትን በመቀነስ ረገድ የታየው ለውጥ ዘገምተኛ መሆኑ ለችግሩ አንዱ ምክንያት መሆኑንም አትቷል። 
የአፍሪቃ መሪዎች ካለፈው ስህተታቸው አለመማራቸው ለአምነስቲ አሳሳቢ እንደሆነበት አቶ ነፃነት ይናገራሉ። "በተለይ ግጭት በተባባሰባቸው አካባቢዎች በቂ የሆነ የፖለቲካ ፈቃደኝነት አልተመለከትንም። በደቡብ ሱዳን በአፍሪቃ ኅብረት ይቋቋማል ተብሎ የነበረው ፍርድ ቤት እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። በአብዛኞቹ አገሮች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት አለመኖሩን ተመልክተናል"

በአምነስቲ ዘገባ መሠረት ተስፋ የፈነጠቁ ምልክቶች አልጠፉም። የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአገሪቱ መንግሥት የዳዳብ መጠለያ ለመዝጋት ያሳለፈውን ውሳኔ ማገዱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በግዳጅ ወደ ሶማሊያ ከመመለስ አድኗቸዋል። በናይጄሪያ እና በጋምቢያም ድርጅቱ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ረገድ መሻሻል ለመኖሩ ምልክቶች እንዲያይ የረዱ ማሻሻያዎች ነበሩ። 

"በተወሰኑ አገሮች የተደረጉ በርካታ አበረታች ማሻሻያዎች አሉ። ለዚህ ምሳሌ ማቅረብ እችላለሁ። በጋምቢያ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል። ቡርኪና ፋሶ እና ማሊን ብንመለከት በተለይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ከጥቃት ለመከላከል ልዩ ሥልት ነድፈዋል። ከአፍሪቃ ኅብረትም የግጭት መስፋፋትን ለመግታት እጅግ ሰፊ የሆነ እቅድ ቀርቧል። ሁሉም ነገር ጭለማ አይደለም። ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የታለሙ የተወሰኑ ማሻሻያዎች አሉ"

ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መልቀቋ አይዘነጋም። ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሐይማኖት መሪዎች ይገኙበታል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የተሻለ ሆኖ ያገኘው እንቅስቃሴ ግን በሕዝቦች ዘንድ የታየው የመጠየቅ ልምድ ይመስላል። አቶ ነፃነት እንደሚሉት በአፍሪቃ የፍርሐት ፖለቲካ እየሸሸ ሳይሆን አይቀርም። 

"ሶስተኛው አስደናቂ እና አበረታች ጅምር ሕዝቦች ለመብቶቻቸው ለመታገል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጨመር ነው። እንደታዘብንው በአፍሪቃና በበርካታ አካባቢዎች የፍርሐት ፖለቲካ እየሸሸ ይመስላል። የተለያዩ ፖለቲካዊ ክልከላዎች እና በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ የሚጣሉ ገደቦች ሰዎች መብቶቻቸው እና ነፃነቶቻቸው እንዲከበሩ ለመጠየቅ ወደ አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ምናልባት ይህ የአፍሪቃ ትልቁ ተስፋ ሳይሆን አይቀርም"

ከባሕላዊ ልማዶች የሚመነጨው እና ፍትኃዊ ባልሆኑ ሕግጋት ተቋማዊ የሆነ የሴቶች እና ልጃገረዶች መድሎ በአፍሪቃ አገራት አሁንም መዝለቁን የዘንድሮው ዘገባ አትቷል። በተለይ ግጭት እና መፈናቀል በበረታባቸው አገራት ሴቶች እና ልጃገረዶች ተገደው እንደሚደፈሩ፤ ወሲባዊ ትንኮሳም እንደሚደርስባቸው ይኸው ዘገባ ገልጿል። ሴራሊዮን እና ኤኳቶሪያል ጊኒን በመሳሰሉ አገሮች ነፍሰ-ጡር ልጃገረዶች ከትምህርት ገበታቸው መገለላቸው በዘገባው የተጠቀሰ ሌላ አስከፊ ድርጊት ነው። 


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች