የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ተቃርኖዎች | ኢትዮጵያ | DW | 28.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ተቃርኖዎች

የኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት በታህሳስ 18 ውሎው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብርን አጽድቋል፡፡ በስህተት ለእስር ለተዳረጉ ሰዎች የሚሰጥ ካሳ የህግ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅለት በመርሃ ግብሩ ተጠቅሷል፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በምርመራ ወቅት በቅርብ ሰው የመጎብኘት መብታቸው ገደብ ሊጣልበት እንደሚቻል የተቀመጠው ተተችቷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:25 ደቂቃ

ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጣረስ የመርሃ ግብሩ ይዘት ተተችቷል

ሰብዓዊ መብቶች ትጥሳለች በሚል በዓለም አቀፍ ተቋማት ተደጋጋሚ ትችቶች የሚደርስባት ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ስታዘጋጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ወደ 140 ገጾች ያሉት ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት ለውይይት የተበተነው የዛሬ ዓመት ግድም ነበር፡፡ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ በመዳሰስ መሻሻልና መስተካከል የሚገባቸውን የሚለይ እንደሆነ እና ለዚህም አፈጻጸም አቅጣጫ የሚተልም እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡

በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለው መርሃ ግብሩ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መሰረቶችን፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን እንደዚሁም የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የባህል መብቶችን የሚቃኙ ክፍሎች አሉት፡፡ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለይቶ መብቶቻቸው ላይ ትኩረት የሚሰጥ ክፍልም አካትቷል፡፡ ለአምስት ዓመት የሚቆየው መርሃ ግብር በዕቅድ ዘመኑ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እና ለማስጠበቅ መከናወን የሚገባቸውን ዋና ዋና ተግባራት፣ የሚፈጸሙበት ጊዜና የውጤት አመላካቾቻቸውን ዘርዝሯል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ መርሃ ግብሩ ከመጽደቁ በፊት እንደመረመረው ተዘግቧል፡፡ የኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ስለ መርሃ ግብሩ የተዘጋጀበትን ምክንያት ለዶይቸ ቨለ እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

“በመጀመሪያ ደረጃ መርሃ ግብሩን ስናዘጋጅ መነሻችን የኤፌዲሪ ህገ መንግስት ነው፡፡ በዚህ ህገ መንግስት ውስጥ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ትልቅ ቦታ ነው የተሰጠው፡፡ ሁለተኛ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች እና ስምምነቶች የሀገሪቱ የህግ አካል እንደሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው እነዚህን ስምምነቶች እና እኛም በሀገራችን ደረጃ በወሳኝነት እንዲከበሩ የምንፈልጋቸውን የቡድን መብቶች በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብቶችን በተሻላ ሁኔታ ለማክበር እና የግለሰብ መብቶችንም በዚያው ልክ ለማረጋገጥ ነው” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር ቀርጻ ያዋለችው በ2005 ዓ.ም ሲሆን ለሁለት ዓመት ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል፡፡ አቶ ጴጥሮስ ሁለተኛው የድርጊት መርሃ ግብር ሲዘጋጅ በመጀመሪያው ላይ ግምገማ ተካሄዶ የነበሩ እጥረቶች መለየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ላይ ተመርቶ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ይገልጻሉ፡፡ መንግስታዊ ያልሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ዳኜ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡

“ሁለተኛው መርሃ ግብር የወጣው በመጀመሪያው መርሃ ግብር አፈጻጸም ላይ ጥልቅ የሆነ ግምገማ እና ዳሰሳ ተደርጎ ወይም ተለይቶ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ነው አንደኛ መሰረታዊ ችግር ብለን የምናስበው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ የሰቪል ማህብረሰብ ተቋማትን ተሳትፎ የሚመለከት ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት አሉ፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ድርጅቶች ናቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰሩት፡፡ እነኚህ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብሩ አወጣጥ ላይም ይሁን አተገባበር ላይ በግምገማ እና ክትትል ወቅት የሚሳተፉበት ስርዓት አሁንም አልተዘረጋም፡፡ ሌላው ቀርቶ መርሃ ግብሩ በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተደረገበት ጊዜ እነኚህ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት አልተጠሩም” ሲሉ ያብራራሉ፡፡    

ሰመጉ አስተያየቱን በምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንዲያቀርብ ባይጋበዝም መርሃ ግብሩን በህግ ባለሙያዎች አስገምግሞ የደረሰበትን ድምዳሜ ለተወካዮች ምክር ቤት ማስገባቱን ምክትል ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤቱ አቶ ጴጥሮስ አዲሱ መርሃ ግብር የተጓደሉ ነገሮችን ለማሟላት ህግ እስከማሻሻል ድረስ አቅጣጫ መቀመጡን ምሳሌ ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡

“[መርሃ ግብሩ] አዳዲስ ሀሳቦች አሉበት፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ በተሳሳተ ማስረጃ የሚፈረድባቸውና የፍርድ ቤት ሂደታቸው አልቆ የታሰሩ ሰዎች ጉዳያቸው በአግባቡ እንደገና እየታየ በዚያው በፍርድ ቤት በኩል ምላሽ የሚያገኙበት ስርዓት ከዚህ በፊት አልነበረም፡፡ አሁን ያንን ሁሉ በህግ ማዕቀፍ አካትቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ እና ሁለተኛ ደግሞ የደረሰባቸውን ጉዳት ላይ ካሳም ጭምር የሚያገኙበት የህግ ስርዓት ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ቃል ተገብቶ ለመስራት እየተሄደ ያለው” ይላሉ፡፡    

በስህተት ለታሰሩ ሰዎች ስለሚሰጥ ካሳ የተጠቀሰው አይነት ጥቂት አዲስ ነገሮችን መርሃ ግብሩ እንደያዘ የሚስማሙት አቶ ቁምላቸው አዲስ ከተካቱት ውስጥ ከህገ መንግስቱም ሆነ ከዓለም አቀፍ ህግ ጋር የሚጣረስ ይዘት ያለው አንቀጽ ማግኘታቸውን በገረሜታ ይገልጻሉ፡፡

“ባለፈው ያልነበረ ትንሽ አስገራሚም አስደንጋጭም የሆነው አንድ አንቀጽ በፖሊስ ጣቢያ በጥበቃ እና በምርመራ ላይ ሰዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በአዲሱ መርሃ ግብር ላይ ምን ይላል? ለወንጀል ምርመራ ውጤታማነት ሲባል አንድ ተጠርጣሪ ከቤተሰቦቹ፣ ከጠበቃው እና ከሃይማኖት አባቱ ሳይገናኝ የሚቆይበትን ስርዓት የሚወስን ህግ ይወጣል ይላል፡፡ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ በነበረው ስብሰባ ላይ ሲነገር የነበረው ምንድነው?  ‘ይህንን ስርዓት የምናደርግበት ምክንያት አሁን በልምድ አለ፤ ግን በልምድ ፖሊሶችና የምርመራ አካላት ይሄን ነገር አላግባብ እንዳይጠቀሙበት መቆጣጠር እና መከታተል ያስፈልጋል፤ ያንን ለማደርግ ነው፤ ለተጠርጣሪው ጥበቃ ነው’ የሚል ማሳመኛ ነው የነበረው፡፡”

“አንድ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ጠበቃ የማግኘት መብቱ መሰረታዊ  ሰብዓዊ እና ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ለወንጀል ምርመራ ሲባል ሊገደብ የሚችልም፣ የሚገባውም መብት አይደለም፡፡ በህገ መንግስቱ ሰብዓዊ መብቶችን ለመገደብ በተቀመጠው ምክንያቶች ዝርዝር የወንጀል ምርመራ ውጤታማነት ተዘርዝሮ አይገኝም፡፡ ስለዚህ ይሄ የህግ ማዕቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ህጋዊ መሰረት የሚሰጥ ነው እንጂ ሰብዓዊ መብትን የሚያስከብር ሆኖ አይታይም፡፡ ለዚህ ነው አስገራሚ የሆነው” ይላሉ፡፡    

አቶ ጴጥሮስ ግን ትችት ያስነሳው እና በረቂቁ ላይ ተጠቅሶ የነበረው አንቀጽ አልጸደቀም ባይ ናቸው፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic