1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአማራ ክልል ይካሄዳል ያሉት «የዘፈቀደ የጅምላ እሥር»

እሑድ፣ ጥቅምት 3 2017

ኢሰመኮና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያሉት «የዘፈቀደና የጅምላ» ያሏቸው እስሮች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች በክልሉ ጽንፈኛ ባሏቸው ኃይላት ላይ የተወሰደው «ሕግ የማስከበር ተግባር ነው» ሲሉ እርምጃው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4lhuv
ስለአማራ ክልል ጦርነት በቀረበ የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ የአማራ ክልል እናቶች ሲያለቅሱ የሚያሳይ ፎቶ
ስለአማራ ክልል ጦርነት በቀረበ የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ የአማራ ክልል እናቶች ሲያለቅሱ የሚያሳይ ፎቶምስል Alemnew Mekonnen

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአማራ ክልል ይካሄዳል ያሉት «የዘፈቀደ የጅምላ እሥር»

የአማራው ክልል ጦርነት ከዓመት በላይ ባስቆጠረበት በአሁኑ ጊዜ  በክልሉ በመካሄድ ላይ መሆኑ የሚነገረው «የዘፈቀደ የጅምላ እሥር» የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ትኩረት ስቧል።በጉዳዩ ላይ መግለጫዎችን ያወጡት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል  ከሳምንታት ወዲህ በርካታ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየታሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።  ኢሰመኮ የጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን ገልጿል።

በአማራ ክልል ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና የሚዲያ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ወደ ጊዜያዊ ማቆያዎች እየተወሰዱ ነው ሲል ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል። ኢሰመኮና አምነስቲ ኢንተርናሽናል «የዘፈቀደ የጅምላ እስሮች »ያሏቸው እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል  የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ስለእስሩና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ባሏቸው ኃይላት ላይ በመወሰድ ላይ ስላሉ እርምጃዎች በሰጡት መግለጫ ፣የተወሰደው «ሕግ የማስከበር ተግባር ነው» ሲሉ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግጭት፤ የጅምላ እስር እና የመገናኛ አውታሮች ሽፋን

በቅርቡ የተቋቋመው የክልሉ የሰላም ምክር ቤት በበኩሉ መፍትሔው ድርድር ነው ብሏል። የዛሬውን እንወያይ ከሳምንታት ወዲህ በክልሉ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረውን እስርና ሌሎች እርምጃዎችን መነሻ ያደረገ ነው።እርምጃዎቹ ሊያሳድሩ የሚችሉት ተጽእኖዎችና ሊያስከትሉ የሚችሉት መዘዞች ፣እንዲሁም በክልሉ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ከኃይል ውጭ ያሉ ሌሎች አማራጮች፣ ውይይቱ የሚያተኩርባቸው ናቸው።

በአማራ ክልል ጦርነት የተቃጠለ አምቡላንስ
በአማራ ክልል ጦርነት የተቃጠለ አምቡላንስምስል Solomon Muchie /DW

 በአሮሚያ ይፈጸማል የተባለው የጅምላ እስር

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወያዩ አራት እንግዶችን ጋብዘናል እነርሱም ፣አቶ ባይሳ ዋቅዎያ  የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሞያ ፣አቶ ያየህይራድ በለጠ የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ አቶ ሲሳይ አሳምሬ የፖለቲካና ፍልስፍና ምሁር እንዲሁም አቶ ሽብሩ በለጠ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው።  በውይይቱ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት እንዲያሳተፉልን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጥያቄ ብናቀርብም መልስ አልሰጡንም። የአማራ ክልል ባለሥልጣናትንም በስልክ ልናገኛቸው አልቻልንም።

ሙሉውን ውይይት ለመከታተል ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ