የሰብል ምርት ከፍ ማለትና ፋይዳዉ | ዓለም | DW | 12.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሰብል ምርት ከፍ ማለትና ፋይዳዉ

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 ከፍተኛ የሰብል ምርት መገኘቱን አመለከተ። እንደFAO ዘንድሮ ከ2,5 ቢሊዮን ቶን በላይ የሰብል ምርት በመመረቱ በዓለም የምርት ታሪክ አዲስ ሪከርድ ተመዝግቧል።

እንዲያም ሆኖን ግን አሁንም በርካታ ሃገራት የእህል እርዳታ እንደሚፈልጉ ድርጅቱ አስታዉቋል። ከእነዚህ መካከል 29ኙ ደግሞ የሚገኙት አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ። እንደFAO ዘገባ በተለይ በዩናይትድ ስቴትስና በአዉሮጳ የሚካሄደዉ እርሻ ዉጤታማ አስተዋፅኦ ነዉ የዘንድሮዉን የሰብል ምርት ከፍ እንዲል ያደገዉ። መቀመጫዉ ሮም የሚገኘዉ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት እንደሚለዉም ምርቱ 2,53 ቢሊዮን ቶን እንደሚደርስ ይህም ካለፈዉ ዓመት ጋ ሲነፃፀር በ0,3 በመቶ ከፍ እንደሚል ያመለክታል። ስለምግብ ዋጋ መናርና የምርት እጥረት በሚወራባት ዓለም የተሻለና በአዲስ ሪከርድ ደረጃ የሚመዘገብ ምርት ማፈስ መቻሉ ለቀሪዉ ዓለም ምን ማለት ይሆን? አብዱረዛ አባሲያን የFAO ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያ እንዲህ ይላሉ፤

«የሰበል ምርት እጅግ በጣም አስፈላጊ የምግብ ምርት ነዉ። ይህም ሩዝን፣ ስንዴን እንዲሁም በቆሎ፣ እና ገብስን ሁሉ ያጠቃልላል። እነዚህ የሰብል ምርቶች በቀጥታ ለሰዎችም ሆነ ለከብቶች አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸዉ። እናም የምርቱ መጠን መከታተል እጅግ በጣም ወሳኝ ነዉ። ያለንን የምርት መጠን ስናዉቅ ነዉ በዓለም ገበያ ዋጋዉ ከፍና ዝቅ ሊል የሚችለዉ። ይህ ደግሞ ምርቱን በስፋት ለሚጠቀሙ ሃገራት ትልቅ ትርጉም አለዉ።»

FAO ከሚያከናዉናቸዉ ተግባራት አንዱ እያንዳንዱ ሀገር ምን ያህል ምርት አምርቶ እንደሆነ መከታተል ነዉ። በዚህ መረጃ ተመስርቶም ያለፈዉ ዓመት ከዘንድሮዉ በምን ሁኔታ እንደሚለይ በማወዳደር የአጭር ጊዜ ትንበያዎችን ይፋ ያደርጋል አብዱረዛ አባሲያን እንደሚሉት።

«የሰብል ምርት ሲጨምር አብዛኛዉን ጊዜ የተሻለ የአቅርቦት ሁኔታ አለ ማለት ነዉ። በተቃራኒዉ ምርት ቀነሰ ማለት አቅርቦቱ ያንሳል ዋጋዉም ከፍ ይላል ማለት ነዉ። ለዚህ ነዉ FAO የዓለምን የሰብል ምርት የሚከታተለዉ፤ ይህን ብቻም አይደለም ንግዱን፣ ፍጆታና ክምችቱን ሁሉ እንከታተላለን። FAO ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ይህንን የሚያከናወኑ ድርጅቶች አሉ፤ ምክንያቱም ለዓለም የምግብ ዋስትና አስፈላጊ ነዉ።»

የዓለም የምግብ የእርሻ ድርጅት ይፋ ባደረገዉ ዘገባ መሠረት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ወዲህ በዘንድሮ የአዉሮፓዉያን ዓመት የተገኘዉ ምርት እጅግ ከፍተኛ ነዉ። ምርቱ ከፍ እንዲል ምክንያቱ የሆኑ ነገሮች የትኞቹ ይሆኑ፤ አሁንም አብዱረዛ አባሲያን፤

«በጣም በርካታ ምክንያቶች ናቸዉ። ምክንያቱም እንደገለፅኩልሽ ይህ የዓለም ምርት ነዉ፤ ወደ180 የሚሆኑ ሃገራት በጋራ ማለት ነዉ። እናም የእያንዳንዱ ሀገር ምክንያት ይለያያል በጥቅሉ ማስቀመጥ ያዳግታል። እንዲያም ሆኖ ግን በአጠቃላይ መልኩ የሰብል ምርቶች በአየር ንብረት ይዞታ ላይ መሠረት የሚያደርጉ ናቸዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ አርሶ አደሮች ምንያህል የተስፋፋ መሬት ላይ አመረቱ የሚለዉ ነዉ። አርሶአደሮች የማምረቻ ቦታቸዉን የሚያስፋፉት የገበያዉ ዋጋ የሚስብ ሲሆን ነዉ። ባጠቃላይ ግን በዚህ ዓመት በሪኮርድ የሚመዘገብ ምርት ማግኘት የተቻለዉ ምርቱ ከፍ ብሎ በታየባቸዉ አካባቢዎች በጣም ጥሩ የአየር ሁኔታ ስለነበረ ነዉ።»

የተሻለ ምርት ዘንድሮ ተገኝቷል የሚለዉ አዎንታዊ ዜና በአንድ ወገን ቢኖርም በሌላ በኩል አሁን በርካታ ሃገራት የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉም FAO ግልፅ አድርጓል። በጦርነት የሚታመሱት ሶርያ፣ ኢራቅ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ኮት ዴቬዋር፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በአንድ ወገን፣ በርካታ ስደኞች የሚገኙባቸዉ ቻድ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሞሪታኒያ፣ ካሜሮንና ኮንጎ በሌላ ወገን የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ናቸዉ። ባጠቃላይ 29ኙ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት ናቸዉ። በአንድ ወገን የተገኘዉ በርካታ ምርት ምናልባት ሚዛኑን ያስተካክለዉ ይሆን፦

«ይህ አዲስ ችግር አይደለም፤ ይህ ለዘላለም አብሮን ያለ ችግር ነዉ። ይም ማለት በዓለም ደረጃ ያለዉ የአቅርቦትና የምርት ሁኔታ እያንዳንዱ ሀገር የግድ ከዚህ ከፍተኛ ምርት ተጠቃሚ ነዉ ማለት አይደለም። አብዛኞቹ ድሀ ሃገራት በተለይም በአፍሪቃ፣ እንዲሁም በላቲን አሜሪካና እስያ የሚገኙት በየዉስጣቸዉ አስከፊ የአየር ሁኔታ፣ ድርቅ፣ ሕዝባዊ ተቃዉሞም ሆነ ጦርነት እና የመሳሰሉትን የተለያዩ ችግሮችን የሚጋፈጡ ናቸዉ። እንደዘንድሮዉ ከፍተኛ ምርት በሚገኝበት ጊዜ የምግብ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ይገመታል። እናም አንዳንዶቹ ሃገራት ከዓለም ገበያዉ ወይም ከለጋሽ አገሮች ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ ብሎ መገመት ይቻላል።»

ጋሚቢያ፣ ጊኒቢሳዉ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ማሊ፣ ኒዠር፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሌሴቶ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ እና ዩጋንዳ ደግሞ የምግብ አቅርቦታቸዉ አስተማማኝ ያልሆኑ ሃገራት መሆናቸዉን FAO ግልፅ አድርጓል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic