የሰባት ዓመትዋን ሄቨንን አስገድዶ ደፍሮ የገደላት ሰው ላይ የተላለፈው ብይን ያስነሳው ጥያቄ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት በአስገድዶ መድፈርና አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ህይወቷ ያለፈው የሰባት ዓመት ታዳጊ ጉዳይ በተበዳይ እናት በኩል ለመገናኛ ብዙሃን ከቀረበ በኋላ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡ ሰሞኑን በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር መነጋገሪያ የሆነው አሰቃቂው ወንጀል ከህብረተሰቡ እሴት በእጅጉ የተቃረነ ነው በሚልም ማኅበረሰቡን አስቆጥቷልም፡፡
በተለይም በወንጀሉ ፈጻሚ ላይ በፍርድ ቤት የተላለፈው የ25 ኣመት ጽኑ እስራት እጅጉን የሚያንስና አስተማሪ ያልሆነ ነው በማለት ምሬታቸውን የገለጹ የማህበረሰብ አካላት ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የሕግ ባለሙያ መሰል የህብረተሰቡ አለመርካትን በዋነኝነት የፈጠረው በአገሪቱ ያለው የወንጀል ሕጉ ክፍተት ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞኖች ግጭቶች በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የተፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች
በሕግ ብያነው ያልረኩ ተበዳይ እናት አንድ ዓመት ከፈጀው የሕግ ሂደትና ብርቱ ፈተናዎች በኋላ የልጃቸው ፍትህ በተመጣጣን ሁኔታ የተረጋገጠ አልመስል ስላቸው ፈተናውን ተጋፍጠው ወደ ሚዲያ ወጡ፡፡ ያሳለፉት ሰውኛ መከራቸውም ከዐዕምሮ በላይ ነውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ አካላት ስሜታቸውን ተጋሩ፡፡
በርካቶችም የአገሪቱን ሕግ አስተማሪነት ከወንጀሉ ከፍተኛነት አንጻር እየወቀሱ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ እና የህግ አማካሪው የሕግ ባለሙያ አንዱኣለም በእውቀቱ ግን የችግሩ ዋነኛው መነሻ በአገሪቱ ያለው የሕግ ክፍተት ነው ይላሉ፡፡
“በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አስገድዶ መድፈር የ15 ዓመት እድሜ እስራትን ነው የሚያስቀጣው” ያሉት ባለሙያው ምናልባት እንደወንጀሉ ክብደት ይህ እስከ 25 ዓመት የእድሜ ልክ እስራት ከፍ የሚልበት የክስ ሂደት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ዋነኛው ሰሞነኛውን ጉዳይ በተመለከተ ከፍተኛ የሆነው እስከ ሞት ቅጣት መበየን ነበረበት ለሚለው የህብረተሰቡ ቁጣ የሕግ ከፍተት መኖሩን አስረድተዋል።
እንወያይ፤ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ
በሞት የሚስቀጣው ከፍተኛ ፍርድ እንዴት ይተላለፋል
የሕግ ባለሙያው በህጻን ሄቨን ላይ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት በተመለከተም የሕግ ሂደቱን በተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት አስፈላጊ ቢሆንም በፍርድ ቤት የተሰጠው ፍርድ ግን በህግ ከተቀመጠው ቅልቁ ነው ብለዋልም፡፡ መሰል ኅብረተሰቡን የማያረካ ውሳኔ የማስቀረት እልባቱ ያለውም በሕግ አውጪው አካል ላይ እንደ ህብረተሰብ ጫና በማሳደር ነው ይላሉ፡፡ “ዋናው መፍትሔ ሕግ አውጪዎች ላይ ጫና ማሳደርና ሕግ ማሻሻል ነው፡፡
ዳኞች ሊፈርዱ የሚችሉት ፊትለፊታቸው በተቀመጠው የሕግ አንቀጽ ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ሊቀርብ የሚችለው አስተያየት ክሱን ያቀረበው አቃቤሕግ ከዚህ በተሻለ መንገድ ወንጀሉን ማቅረብ አይችልም ወይ የሚል ነው” ያሉት ባለሙያው ከአስገድዶ መድፈርም ባሻገር የግድያው አፈጻጸምና ግድያውን ለመደበቅ የተሄደው መንገድ ቢጎላና ክሱ በዚያ መንገድ ቢቀርብ ከዚህ የጠነከረ ፍርድ ማስፈረድ ይቻል ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ሊደረግ የሚገባው ግፊት
የወንጅል ድርጊቱ ከህብረተሰቡ እሴት ያፈነገጠ ከመሆኑም በላይ እጅጉን አሰቃቂ ነው፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ ከመሳቀቅም አልፎ ተቆጥቷል፡፡ ይህንንስ የማካካሻ ጠጋኝ መንገድ ይኖር ይሆን? የተባሉት ባለሙያው፤ “ሕግ ማንጸባረቅ ያለበት የህብረተሰቡን ስሜት ነው” ብለዋል፡፡ መሰል ወንጀሎች ከመደጋገማቸውም ባለፈ እጅጉን አሰቃቂና ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር በቂ ፍርድ አለመተላለፉ ህብረተሰቡ ከፍተኛውን ግፊት በሕግ አውጪ ላይ ሊደርግ ይገባል የሚል ግንዛቤ የሚሰጥ ነውም ተብሏል፡፡ ሕጉ ከህብረተሰቡ መቅደምም ነበረበት ያሉት ባለሙያው ሌሎች እንዳይጠቁ አስተማሪ ፍርድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ ግፊት ማድረግን ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡
የህጻኗ የፍትህ ጉዳይ እጅጉን መነጋገሪያ በመሆን በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሽፋንን በማግኘት ላይ ነው፡፡ የወንጀሉ በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መሆንን ተከትሎ የአገሪቱ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እከታተላለሁ ብሏል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመበት ባህርዳር ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ነው የሰጠው፡፡ የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ግን በተለይም የሴትችና ማህበራዊ ጉዳይ የሰጠውን መግለጫ ነቅፏል፡፡ የሕግ ባለሙያው አንዱዓለም በእውቀቱ ለዚህም ማብራሪያ ሲሰጡ፤ “ዳኞች ፍርድ መስጠት የሚችሉት በተቀመጠላቸው ሕግ መሰረት ብቻ ነው፤ ምናልባት ለውሳኔው መነሻ የሚሆነው በአቃቤ ሕግ የቀረበው ክስ ሊሆን ስለሚችል ያንንም በአግባቡ ማየት ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር