የ«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» ወቀሳ | ኢትዮጵያ | DW | 03.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የ«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» ወቀሳ

«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» በመባል የሚታወቀው፣ በዓለም ዙሪያ ለነባር ህዝቦች ኅልውና የሚታገለው ድርጅት የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስለኦሞ ሸለቆ ጉዳይ እንዲያነሱ አሳሰበ። ድርጅቱ በኦሞ ሸለቆ «የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተከሰተ ነው፤ ጀርመንም ሆነች ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት የመብት ጥሰቱን አይተው እንዳላዩ ሆነዋል» ብሏል።

«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» በመባል የሚታወቀው፣ በዓለም ዙሪያ ለነባር ሕዝቦች ኅልውና የሚታገለው ድርጅትበኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል፣ ታችኛው የኦሞ ሸለቆ ተከሰተ ላለው የሠብዓዊ መብት ጥሰት ጀርመን ትኩረት ትስጥ ሲል አሳሰበ። የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ እዚህ ጀርመን በርሊን ከተማ ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ሲያነጋግሩም በኢትዮጵያ የኦሞ ሸለቆ አካባቢ በሚኖሩ ተወላጆች ላይ ስለሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያነሱ ጥሪ አስተላልፈዋል። የ«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል»የጀርመን ቅርንጫፍ አስተባባሪ ሊንዳ ፖፔ ከበርሊን ከተማ።

«አንጌላ ሜርክል በእዚህ ስብሰባ ኦሞ ሸለቆ ውስጥ ስለሚኖሩ ሕዝቦች መብቶች እንዲያነሱ ጥሪያችንን አስተላልፈናል። ጀርመን ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ የልማት እና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግ ሀገር ናት። በኢትዮጵያ የኦሞ ሸለቆ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተከሰተ ነው። እናም እስካሁን ባለን ግንዛቤ መሠረት ጀርመንም ሆነች ሌሎች የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ የአውሮጳ ሃገራት ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳላየ ያልፉታል»

«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» ባለፈው ሳምንት አርብ (ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓም ) ለመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በላከው ግልፅ ደብዳቤ በደቡብ ኢትዮጵያ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ ውስጥ ያለው ሁናቴ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጧል። በኦሞ ሸለቆ በመልሶ ሰፈራና በግዳጅ መባረር የተነሳ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከሰተዋል ሲል ድርጅቱ አያይዞ ጠቅሷል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ፤ ከቀዬ በግዳጅ መፈናቀል፣ መደብደብ እንዲሁም መደፈርን የመሳሰሉትን እንደሚያካትቱ «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል»ተናግሯል።

የኦሞ ወንዝ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ

የኦሞ ወንዝ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ

«አንጌላ ሜርክል በኦሞ ሸለቆ እየሆነ ስላለው ነገር ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲናገሩ አጥብቀን እንሻለን። ጀርመን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ላላማከረ ማንኛውም ፕሮጀክት አንዳችም አይነት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደማትችል ግልጽ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን። እናም ይኽ ነጥብ የሚነሳ ከሆነ፥ በፖለቲከኞች እና በመንግሥት ባለሥልጣናት፥ ለምሳሌ በልማት ሚንሥትር በኩል በእርግጥም ተግባራዊ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።»

ሰፊ ልማት ሲከናወን ወደፊት ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነገሮች የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲያውቅ እና እንዲስማማበት ሊደረግ ይገባል፤ ይኽ በኦሞ ሸለቆ ሲሆን አልታየም ሲል «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» ወቀሳውን አቅርቧል። ድርጅቱ ዋነኛ ትኩረቱ በኦሞ ሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቢሆኑም፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግር መከሰቱን የ«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» የጀርመን ቅርንጫፍ አስተባባሪ ሊንዳ ፖፔ ተናግረዋል።

«በተለይ የምናተኩረው በኦሞ ሸለቆ ዙሪያ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለምሳሌ በጋምቤላም የሆነው እንደእዛው ነው። በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ነገሮች ተከስተው ውጤታቸው እጅግ የከፋ ነበር። ለምሳሌ፦ «የመንደር ምሥረታ» መርሐ-ግብር ወደ ተግባር ሲቀየር፥ ማለት በየመንደሮች መልሶ የማስፈር እንቅስቃሴ ሲፈጸም በወቅቱ ቃል ተግብተው የነበሩ ቀና ነገሮች በእውነቱ ተግባራዊ አልሆኑም።»

በኦሞ ወንዝ ላይ የሚገነባው የ«ጊቤ 3» ግድብ በታቀደለት መሠረት በመጪው የጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት ሥራ ከጀመረ የአካባቢው ነዋሪዎች የምግብ ምንጭ የሆነው ተፍጥሯዊ ሙላቱ ይቋረጣል ሲል «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል»ስጋቱን ገልጧል። ጀርመን ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ወሳኝ ሃገራት እንዷ በመሆኗ በኦሞ ሸለቆ የሚከሰተው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሬት ነጠቃ ትኩረት ሊያሻው ይገባል ሲል ድርጅቱ አስገንዝቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች