1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሞንኛ አበይት ርዕሶች እና ከማኅበራዊ መገናኛ የተሰበሰቡ አስተያየቶች

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2016

በዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዝግታችን„የአማራ ክልል የፀጥታ ቀዉስ በውይይትና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ ማቅረቡ፤ ከጠበቆቻቸው ጋር ለመገናኘት የተቸገሩት ታዬ ደንደኣ፤ እንዲሁም የኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ እና ያስከተለዉ ቀዉስ„ በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል፤

https://p.dw.com/p/4hcqk
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ምስል Thomas Trutschel/photothek/picture alliance

ሰሞንኛ አበይት ርዕሶች እና ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተሰበሰቡ አስተያየቶች

በዚህ ዝግጅታችን „የአማራ ክልል የፀጥታ ቀዉስ በውይይትና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ ማቅረቡ፤ ከጠበቆቻቸው ጋር ለመገናኘት የተቸገሩት ታዬ ደንደኣ፤ እንዲሁም  የኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ እና ያስከተለዉ ቀዉስ„  በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል፤  

ለአማራ ክልል የሰላም እና የድርድር ጥሪ  

በአማራ ክልል የሚታየዉን የሰላም እጦት "በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስችላል" የተባለለት የሰላም ዉይይት በያዝነዉ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ፤ "ሁሉም ነገሮች  ከብረት፤  በመለስ በውይይት፣ በድርድር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ህዝብና አገርን በሚያሳድግ አቅጣጫ መነጋገር አለብን፣ መወያየት አለብን የሚል አቋም መያዝ አለበት፤ መንግስት ጭምር ይህን አቅጣጫ እንዲከተል፣ በተጨባጭ ውጊያ እያደረገ ያለውም ኃይል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማድረግ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ውይይት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ " ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ተፋላሚ ሃይላትን ያላሳተፈ የሰላም ውይይት ውጤት ይኖረው ይሁን? በክልሉ ሰላም እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት?

አበበ ጌታነህ፤ እውነት መንግስት ከፋኖ ጋር መደራደር ፈልጎ ከሆነ፤ በብዙ አማራጮችን ማባከን ወይም ዙሪያ ጥምጥም መሄድም አያስፈልግም ነበር። እንደ አይጥ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ አይነት ድርድር ነው መንግስት የሚፈልገው፤ አቅሜን አሳይቸ ዳግም ተመልሰው እንዳይመጡ፤ ከጥቅም ውጭ ከአደረግን በኃላ ለመደራደር እችላለሁ፤ አይነት ነገር ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ወፍ የለም የሚል የፌስቡክ መለያ ያላቸዉ አስተያየት ሰጭ በአስተያየታቸዉ፤ መንግሥት የሰላም ፈላጎት ቢኖረው ኑሮ ገዥው ፓርቲ በመረጣቸው ከሰፈር ሽማግሎች ጋር ውይይት አያደርግም ነበር ። የአማራ ህዝብ ጥያቄ በጣም ግልፅ ነው።  ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጽያ ውስጥ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ነፃነት ከብሄርተኝነት ሰፈር ወጥቶ ኢትዮጽያዊነትን መገንባት በብሔራቸውና በማንነታቸው ምክንያት የተሰሩትን ፖለቲከኞችና ንፁሃንን መፍታት እና የመሳሰሉት ናቸው ። ነገር ግን ብልፅግና ካለፉት ስርዓተ መንግስታት ድክመቶች ሳይማር በብሔር ስም ራሱን በባሰ መልኩ አደራጅቶ፤ የመጣ ቢሆንም ግን፤ ከኪሳራ ውጭ ለውጥ አያመጣም ሲሉ በአራት ነጥብ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

በአማራ ክልል ባህር ዳር የባለስልጣናት ስብሰባ
በአማራ ክልል ባህር ዳር የባለስልጣናት ስብሰባ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ኢትዮጵያ፤ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ፤ ክልሉ ከወያኔ ወረራ ጀምሮ በአሁኑም ጭምር እየወደመ ይገኛል። ይሄ ጦርነት መነሻዉ ምንም ይሁን ምን፤ እንዲቆም ተደርጎ ወደ ድርድር መግባት ያስፈልጋል። መንግስትን የሚታገሉ ሃይሎች ጥያቄያቸዉን በሚገባና በተደራጀ መንገድ ያቅርቡ፣ መንግስትም ለጥያቄዎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚመልስ ቃል ገብቶና ተፈራርሞ ሀገራችን ወደ ሰላም መመለስ አለበት ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ሰላማዊ ድርድሩ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከተፈለገ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት አብደላ አብደላ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ አንደኛ ተፋላሚ ሀይሎችን ጨምሮ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶችን ያለ ስጋት ማሳተፍ አለበት።  ሁለተኛ  በአገሪቱ ውስጥ በጠመንጃ የሚፋለሙት አካላት ሁሉ(መንግስትን ጨምሮ) ጦርነት ሟቆም አለባቸው።  ሦስተኛ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው።  በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኙ የውጭም ሆነ የውስጥ አደራዳሪዎች መመረጥ አለባቸው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ጉዳይ 

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ የቀድሞዉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደአ፤ ጠበቆቻቸው ላይ ከመንግስት የሰላ ማስፈራሪያ በመድረሱ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው መግለፃቸዉ ተሰምቷል። አቶ ታዬ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፤ ቀርበው እንዳስረዱት «አቃቤ ሕግ እና ሰዎቻቸው» ባሏቸው አንድም ጠበቃ እንዳይቆምላቸው በጠበቆቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሷል። አቶ ታዬ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የሰጠዉ የንብረት ማስመለስ ትዕዛዝም አለመከበሩን አንስተው ቅሬታቸውን ማሰማታቸዉ ተሰምቷል።  

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ታየ ደንደአ
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ታየ ደንደአ ምስል Million Haileselasi/DW

ሸኘዉ ዋለ፤ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ፤  የሰላም ሚኒሰትርን አስሮ ሰላም የሚፈልግ መንግሥት ጉድ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ አጠቃለዋል።

ድሮና ዘንድሮ የተባለ የማኅበራዊ መገናኛ መለያ ያላቸዉ የፊስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ እኔ እንደሚመስለኝ አቶ ታዬ ከመንግሥት ጥበቃ ዉጪ ከሆነ ጥቃት እንደምደርስበት በማመን ሆን ብሎ የታሰረ ሰው ነው የሚመስለኝ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።  

ዮናስ ሺፈራዉ፤ ፍትህ ሀገር ያፀናል። ማንም መዳኘት ያለበት በትክክለኛው የፍትህ ሚዛን ነው። መንግስት የህዝብን አመኔታ ማትረፍ አለበት ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

የኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ ያስነሳዉ ቀዉስ

የኬንያው ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቶ በሐገሪቱ ግብር ለመጨመር የያዙትን እቅድ በመቃወም መዲናዋ ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተቀሰቀሰዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ቢያንስ 23 ሰዎች መሞታቸዉ ተዘግቧል። ተቃዋሚዎች  ወደ ምክር ቤቱ መትመማቸዉን ተከትሎ ነዉ፤ በርካታ ሰዎች ፖሊስ በተተኮሰባቸዉ ጥይት የተገደሉት እና በርካቶች የቆሰሉት። የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ህዝባቸውን ያስቆጣው የታክስ ጭማሪ ሕግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ቢያሳውቁም ተቃውሞው ዛሬም እንደቀጠለ እየተነገረ ነዉ።  የኬንያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው የባሕር ዳርቻዋ ሞምባሳ ከተማ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች ሩቶ ከሥልጣን እንዲወርዱ በጩኸት ሲጠይቁ ነበር። በተቃዋሚዎቹ በሚወረወሩ ድንጋዮች እና ዘረፋዎች ምክንያትም የንግድ ተቋማት ተዘግተው ነበር።

ኑማን ሁንዳ ዱሩሳ ፤ ተቃውሞን ማሰማት መብት ሆኖ ሳለ ወደ ፓርላማ ጥሶ ገብቷል የተባሉት የፓርላማ አባል ሳይሆኑ ድምፀ ታአቅቦ ልያደርጉ ነው ወይስ ምን ፍለጋ ነው? በሰፊው ሜዳ መቃወም ትተው ሌላ ነገር መፈለግን ምን አመጣው? ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ምልክት ደምድመዋል።   

በኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ እና የቀሰቀሰዉ ቁጣ
በኬንያ የግብር ጭማሪ እቅድ እና የቀሰቀሰዉ ቁጣ ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

እዚህ የግብር ዶፍ እየወረደብን ዝም ጭጭ ብለናል ያሉት ታምሩ አበበ፤ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።

የትነበርክ አሻግሬ የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ ፤ የኬንያን ሁኔታ በአፅንኦት እየተመለከትነው ነው ,,,መኮረጅ ሚያስፈልገን ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ጃራ ቦሩ የተባሉ የፌስቡክ ተከታይ ፤ እብድ በለዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። እብድ በለዉ፤ የሚቀምሰው አጥቶ በዋጋ ንረት እየተጨነቀ ባለ ህዝብ ላይ ዳቦ እና ዘይት ላይ ተጨማሪ ግብር ለመጣል መሞከሩ ለዚህ እንደሚያበቃው አለመጠበቁ ነው የሚገርመው። የኬንያም ሆነ የኛ ሃገር መሪዎች ከእውነታው የተፋቱ፣ በፈንተዚ ዓለም የሚኖሩ፣ በመለኮት እየተመሩ እንደሆኑ የሚየምኑ መሪዎች ናቸው።  

በሦስት ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ያየንበት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት እስከዚሁ ነበር። ሙሉዉን ጥnqeር የድምጽ ማድመጫ ማዕቀዱን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ