የሰሞኑ የህወሐት ስብሰባና የተቃዋሚዎች አስተያየት | ኢትዮጵያ | DW | 23.01.2023
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሰሞኑ የህወሐት ስብሰባና የተቃዋሚዎች አስተያየት

``ከመጀመሪያው እኛ ያለን አቋም TPLF በሕግ የማይገዛ፣ በውይይት የማያምን፣ ለብቻው ብቻ በስልጣን መኖር የሚፈልግ የጥቅምና የቤተሰብ ስብስብ ነው ብለን ነው የምናምነው። እና ይህ የስልጣን ነጋዴ በሃይል በስልጣን ላይ ሊቀጥል እንጂ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ዝግጁ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡልን ብዙ ነገሮች አሉ። ``

የሰሞኑ የህወሐት ስብሰባና የተቃዋሚዎች አስተያየት

ህወሓት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሳታፊ በሆነ መልኩ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ቁርጠኛነት የለውም ሲሉ የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ አራማጆች ለDW ተናገሩ። ድርጅቱ ለሳምንት የዘለቀ ስብሰባ ላይ ቢቀመጥም የትግራይ የወደፊት እጣ ፈንታ በሚወስን ፖለቲካዊ ውይይት አንድም የፖለቲካ ፓርቲ በስብሰባው አላሳተፈም ብለዋል። ከዚህ አንጻር እንደበፊቱ ጥልቅ ተሃድሶ አካሂጃለሁ ብሎ የሚመጣ ከሆነ ተቀባይነት የለውም ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል። 
የህወሓት ፖለቲካዊ አመራርና የትግራይ ወታደራዊ አመራር ስብሰባ ከተቀመጡ ሳምንት ደፍነዋል። በእስከዛሬ ውይይት ስለተደረሰበት ስምምነት ግን ይፋዊ መረጃ አልተሰጠም። ትላንት አመሻሽ ላይ በአንድ የግል ጋዜጠኛ ማሕበራዊ ድረገጽ የወጣው ሰበር መረጃ ግን ብዙዎችን እያወዛገበ ነው።
ሰበር ዜናው ህወሐት በስብሰባው 23 የካቢኔ አባላት ያሉት የሽግግር መንግስት ማቋቋሙንና ከነዚህ 14ቱ ከህወሐት መሆናቸውን ይገልጻል። ዜናው ከተሰራጨ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ጌታቸው ረዳና ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሂወት ``የትግራይ ሕዝብ ደህንነት በተመለከተ ለውጥ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ቢደረስም የተደረገ ሹምሽር የለም`` በማለት አስተባብለዋል።

ይህን መሰረት አድርገን የተለያዩ የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አንድ የፖለቲካ አራማጅ አነጋግረናል። አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ የዓረና ትግራይ የሕዝብ ግኑኝነት ሐላፊ።
`` በአሁኑ ሰዓት ህወሓት የራሱ ስብሰባ እያካሄደ ነው። እንዲሁም የወታደራዊ መሪዎች የሚሳተፉበት ነው ተብሏል። ይህ የራሳቸው ጉዳይ እንጂ የሽግግር መንግስት የሚመለከት አይደለም። እንደዛ ከሆነ የሚመለከታቸው ሕጋዊ የሆኑ ፓርቲዎች መሳተፍ ነበረባቸው። የሽግግር መንግስት የሚቋቋም ከሆነ የፌደራል መንግስትና የፕሪቶሪያው ውል የፈረመው አካል በተስማሙበት መሰረት ሌሎች ፓርቲዎችም ስብሰባ አካሂደው አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግስት ይመሰረታል ነው የሚለው ስምምነቱ። ህወሓት ግን ቤት ዘግታ ነው እየተነጋገረች ያለችውና ይሄ ትርጉም ያለው ስብሰባ አይደለም።``

ዋና ጽሕፈት ቤቱ ጀኔቫ ያደረገው የአግአዝያን ሐበሻ ሕብረት አስተባባሪ ዶክተር አረጋዊ መብራህቶም ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
`` ከመጀመሪያው እኛ ያለን አቋም TPLF በሕግ የማይገዛ፣ በውይይት የማያምን፣ ለብቻው ብቻ በስልጣን መኖር የሚፈልግ የጥቅምና የቤተሰብ ስብስብ ነው ብለን ነው የምናምነው። እና ይህ ሕጋዊ ያልሆነ፣ በሕግ የማይገዛ፣ ለራሱና ለቡድኑ ጥቅም የሚሯሯጥ የስልጣን ነጋዴ ሃይል በስልጣን ላይ ሊቀጥል እንጂ ሌላ ሰላማዊ ሕጋዊ አካሄድ ፤ ለሐገርና ለሕዝብ የሚጠቅም የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ዝግጁ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡልን ብዙ ብዙ ነገሮች አሉ። ታሪኩም የሚያሳየን እንደዛ ነው። በውይይት የሚያምን በሕግ የሚያምን ሃይል አይደለም። አሁንም እያደረገ ያለው ሕዝብን የማጭበርበር እና ቀስ በቀስ ደግሞ ተቃራኒ የሆኑ ሃይሎችን የማስወገድ አሁንም ወደዛ ነው እየሄደ ያለው እንጂ የሽግግር መንግስት ያቋቁማል በፕሪቶሪያው ስምምነት ይገዛል የሚል ተስፋም እምነትም የለንም በኛ አመለካከት።``

የትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ይቋቋም ጥያቄ
በፕሪቶሪያ ውል መሰረት የፌደራል መንግስትና ህወሓት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያካተተ ጊዚያዊ መንግስት ማቋቋም ሲገባው ህወሓት ብቻውን ተሰብስቦ የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ የገለጹት የታላቋ ትግራይ ባይቶና የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ ሃይለስላሴ ተከታዩን አክሏል።
`` የፕሪቶሪያ ውሉ ምንድነው የሚለው የፌደራል መንግስት፣ ህወሐትና ተቃዋሚዎች ያሉበት የሽግግር መንግስት ያቋቁማሉ ነው የሚለው። አሁን ምን እየተደረገ እንደሆነ ግን ግራ ገብቶናል። አሁን ስብሰባ ላይ ነው ያሉት፤ አቶ ጌታቸው የጻፉትም አይቸው ነበረ። የለውጥ ስብሰባ እየተደረገ ነው፤ ቢሆንም ግን የተለወጠ ነገር የለም እያሉ ነው። 14 ከህወሐት፣ 6 ከዲያስፖራ፣ 3 ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚል አይቻለሁ። ይሄ ግን ድብብቆሽ ነው። ሕዝቡ ከመከራ እንዳይወጣ እያደረጉት ያለ ነው። ስለዚህ ትክክል አይደለም። ሕወሓት በለመደው መንገድ እየሄደ ነው።``

በመቐለ ዩኒቨርስቲ አስተማሪና በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ አራማጅነታቸው የሚታወቁት አቶ ሸዊት በበኩላቸው ።
`` ትልቁ ስጋት የሚያድርብህ እንደ አንድ ትግራዋይ ሆነህ ስታስበው አሁን ቤት ዘግቶ እየመከረ ያለው ህወሓት ብቻ ነው። ይሄ ማለት ሊያሸጋግሩን የሚፈልጉት እነሱ ተወያይተው በሚያመጡት መፍትሄ ነው ማለት ነው። አሁን ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙዎቹን አውቃቸዋለሁ ስለውይይቱ ምንም አይድያ የላቸውም። ስለዚህ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሩን ዘግቶ የሚያመጣው መፍትሔ እንዴት ነው ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው ብለህ ስትጠይቅ የፈለገው ተአምረኛ መፍትሔ ይዘው ቢመጡም ሊሰራ አይችልም። ምክንያቱም አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሁኔታ አደለምና የፖለቲካ ፓርቲዎች ማሕበረሰቡም አሳትፈህ ሁሉንም የሚገዛ የሚያስማማ መፍትሔ ነው መሆን ያለበት። ስለዚህ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን አካሄዱም የተሳሳተና ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው።``
ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ህወሐት እንደከዚህ ቀደሙ ``ጥልቅ ተሃድሶ አካሂጃለሁ`` በሚል አሁንም የሽግግር ሂደቱን በበላይነት ለመምራት ከሞከረ አደጋው የከፋ ነው ብለዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ
 

Audios and videos on the topic