የሰሜን እና የደቡብ ሱዳን ስምምነት | ኢትዮጵያ | DW | 19.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሰሜን እና የደቡብ ሱዳን ስምምነት

የሱዳን መንግስት እና የደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ጦር በምህጻሩ ኤስ ፒ ኤል ኤም በሰሜን ሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል ለብዙ ዓመታት የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት ያበቃውን የሰላም ውል ከተፈራረሙ ከአምስት ዓመታት ገደማ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ዴሞክራሲያዊ ተሀድሶ ለማድረግ በዚህ ሳምንት አዲስ ስምምነት ደርሰዋል።

default

የሱዳን ገዢው ብሄራዊ ኮንግረስ ምክትል ፕሬዚደንት ናፍዕ አሊ ናፍዕ

የሱዳን ገዢው ብሄራዊ ኮንግረስ ምክትል ፕሬዚደንት ናፍዕ አሊ ናፍዕ ባለፈው እሁድ እንዳስታወቁት፡ ስምምነቱ በመላይቱ ሱዳን በሚቀጥለው 2010 ዓም ከሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ እና የደቡብ ሱዳን ዕጣ ፈንታን በተመለከተ እአአ በ 2011 ዓም የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ የሚደረግበትን ሁኔታ ግልጽ የሚያደርግ ይሆናል። በህዝበ ውሳኔው የደቡብ ሱዳን ህዝብ አካባቢው ከሱዳን ጋር ተጠቃሎ በመቆየቱ ወይም ተገንጥሎ ነጻ መንግስት በመመስረቱ ጥያቄ ላይ ድምጹን ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪ በብሄራዊ አንድነት መንግስት የተጠቃለሉት ሁለቱ ወገኖች በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደለው የአብየ ግዛት ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደገና በሚቀላቀልበት ጉዳይ ላይ ለመደራደር ተስማምተዋል፤ የደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ንቅናቄ ቃል አቀባይ ፓጋን ራሞን እንዳስረዱትም፡ ሁለቱ ወገኖች የጸጥታውን ጥበቃ ሁኔታ ለማሻሻል አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተስማምተዋል።
« የብሄራዊ ጸጥታ ጥበቃ ህግ ተግባራዊ እንዲሆን እንፈልጋለን። የህዝቡን ጸጥታ ጥበቃ የሚከለከል እና ነጻነታቸውንም የሚያረጋግጥ፡ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በነጻ መሳተፍ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ህግ እንዲተረጎም ነው የምንፈልገው። »
አዲሱ ስምምነት ሊፈረም ጥቂት ቀናት ሲቀረው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ንቅናቄ መሪዎችና ደጋፊዎች የሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች እአአ በ 2005 ዓም በናይቫሻ ኬንያ በተፈራረሙት የሰላም ውል ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆኑ በመዲናይቱ ካርቱም በሚገኘው በምክር ቤቱ ደጃፍ ሰላማዊ ተቃውሞ ሰልፍ ባካሄዱ ጊዜ ወደ ሰላሳ የሚሆኑ በመንግስቱ ጸጥታ ኃይላት የታሰሩበትንና በርካቶችም የተጉላሉበትን ድርጊት በተመለከተም የኤስ ፒ ኤል ኤም ቃል አቀባይ ፓጋን ራሞን ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
« ዴሞክራሲያዊው የሽግግር ሂደት ተግባራዊ እንዲሆን በመጠየቅ በሰላማዊ ዘዴ ተቃውሞ ያካሄዱት መሪዎቻችን እና የደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ንቅናቄ አባላት የታሰሩበትንና የተጉላሉበትን ድርጊት እናወግዛለን። ይህ የጭቆና ተግባር የብሄራዊው ኮንግረስ ፓርቲ አምባገነናዊውን መንግስት በማቋቋም ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። »
የብሄራዊውን ኮንግረስ ፓርቲ እና ደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ንቅናቄን ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ሲያወዛግብ የቆየውን እና ከአምስት ዓመት በፊት የተፈረመውን የሰላም ውል ሊያከሽፍ ቃትቶ የነበረው ጥያቄ በዚሁ አዲሱ ስምምነት መፈረም ሊወገድ መቻሉን የኤስ ፒ ኤል ኤም ገልጾዋል።

Darfur, Flüchtlinge, Sudan

የሱዳን ተፈናቃዮች


ቀደም ባሉ ጊዚያት የምርጫውን ሂደት በተመለከተ የተፈጠረው ውዝግብ ሊወገድ ባለመቻሉ ምክር ቤታዊው ምርጫ በሁለት ወራት ወደፊት ተገፍቶ የፊታችን ሚያዝያ እንዲካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው። እአአ ከ1986 ዓም ወዲህ አሁን ሱዳን ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በምክር ቤታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ተፈቅዶዋል። ይህ አበረታቺ ዜና ቢሆንም፡ የአውሮጳውያኑ 2009ዓመት የሰላሙ ውል ከአምስት ዓመት በፊት ከተፈረመ ወዲህ የኃይሉ ተግባር የተስፋፋበት ዓመት መሆኑን ድንበር የማይገድበው ግብረ ሰናዩ የሀኪሞች ድርጅት፡ ሜድሰ ሶን ፍሮንትየር በምህጻሩ ኤም ኤስ ኤፍ አስታውቋል። ድርጅቱ በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው ዘገባው፡ በተለይ ባንዳንድ ክፍላተ ሀገር የሚፈጸመው ጥቃት እና ውጊያው ጨምሮዋል። ለምሳሌ በምስራቃዊ ኢኳቶርያ በቀንድ ከብት የተነሳ ግጭት መኖሩ፡ እንዲሁም፡ ህጻናት የሚታገቱበት ሁኔታ ባካባቢው ህዝብ ዘንድ ውጥረቱን እያካረረው መጥቶዋል። ብዙዎቹ የግጭቶቹ ሰለባዎችም ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸው ተሰምቶዋል።
በተመድ ዘገባ መሰረት፡ በቀጠለው ግጭት 250,000 የሚሆኑ ሰዎች በሀገራቸው ውስጥ ከቤት ንብረት ተፈናቅለዋል። በቂ ምግብ የማያገኙትና አዘውትረውም በበበሽታ የሚሰቃዩት ተፈናቃዮች በእጅግ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሀኪሞቹ ድርጅት ገልጾዋል። በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ የቀውሱን አሳሳቢነት ተረድቶ ባስቸኳይ ርዳታ እንዲያስተባብር ጠይቆዋል።

አርያም ተክሌ
DW