የሰሜን ሸዋ ጥቃት፣ ሲኖዶስ እና የአቶ በረከት መፈታት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 27.01.2023
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሰሜን ሸዋ ጥቃት፣ ሲኖዶስ እና የአቶ በረከት መፈታት

በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት መሰናዶ፦ የሰሜን ሸዋው ጥቃት፤ የሲኖዶስ ሕገወጥ የጳጳሳት ሹመት የቀሰቀሰው ቁጣ እንዲሁም የአቶ በረከት ስምዖን መፈታት ላይ እናተኩራለን። አስተያየቶቻችሁ የተሰባሰበበትን ጥንቅር ሙሉ ዘገባ በድምፅ ማድመጥ ይቻላል።

ሣምንታዊ የማኅበራዊ መገኛ ዘዴዎች ቅኝት

መንግሥት ሸኔ በሚል የፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በሰሜን ሸዋ ውስጥ ጥቃት ሰንዝሮ በርካቶችን ገደለ፤ አፈናቀለ፤ ቤት ንብረት አቃጠለ መባሉ ዐቢይ መነጋገሪያ ሆኗል። ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የፈጸሙት የ«አማራ ታጣቂዎች» ናቸው ሲል አስተባብሏል። የተወሰኑ ጳጳሳት አዲስ ሲኖዶስ አቋቋምን ሲሉ ሹመት መስጠታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድም ሆነ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ቁጣ አጭሯል። ይህም የዛሬው ትኩረታችን ነው። በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ስድስት ዓመት የተፈረደባቸው አቶ በረከት ስሞኑን በአመክሮ ከ4 ዓመት በኋላ የመፈታታቸው ዜናም ትኩረትን ስቧል።

የሰሜን ሸዋ ጥቃት

የሰሜኑ ጦርነት እና ግጭት የደቆሰው ማኅበረሰብ ለጊዜውም ቢሆን እፎይ ባለበት ቅጽበት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች ደም አፋሳሽ ጥቃቶች፤ ግጭቶች እና ውጥረቶች ነግሰዋል። በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ሰሞኑን በነበሩ ጥቃቶች እና ግጭቶች የበርካቶች ሕይወት ሲቀጠፍ በመቶ ሺህዎች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል። እየተደጋገመ በሚከሰተው ጥቃት እና ግጭት በርካታ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ተቃጥለው አመድ ሆነዋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረትም ወድሟል። በአካባቢው ሄድ መለስ የሚለው ችግር ከስር መሰረቱ ባይፈታም በማኅበረሰቡ ጥረት ጋብ ብሎ ጥቂት ወራት እፎይታ ተፈጥሮ ነበር። ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ደግሞ ችግሩ አገርሽቶ በርካቶች ተገድለዋል። የስልክ መስመር በሚሰራባቸዉ አካባቢዎች የሚኖሩ የዓይን ምስክሮች እንዳሉት የአማራ ልዩ ኃይልና መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ግጭቱን የጀመሩት ባለፈዉ ቅዳሜ ነዉ።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየት ሰጪዎች መንግሥት ችግሩን የማስቆም ፍላጎት የለውም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። «መንግሥት ካለ ሕግ ያስከብር» የእናት አሰፋ አስተያየት ነው። «እንዴ መንግስት አለ እንዴ ይህ ጥያቄ ከታደሰ ታምሩ የተሰነዘረ ነው። ፍቃዱ አማረ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም በተመሳሳይ መልኩ፦ «መንግስት አለ እንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሉ ጠይቀዋል። «መንግስት አልሰመም የተወሰና ሰዉ ስያልቅ ጣልቃ ይገባል እስከዛ ትንሽ ይበጠበጥ» ያሉት ደግሞ ሄኒ ማን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። «እኔን ያልገባኝ ነገር» ይላሉ እዮብ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «መንግስት ችግሩን መቅረፍ ከፈለገ 1 እና 2 ወር ብቻ ነው እሚፈጅበት» ሲሉም ይቀጥላሉ። «ይህን መቆጣጠር ያቃተው መንግስት መንግስት መባል ይችላle ሲሉም ጠይቀዋል። ብሮከር ያሲኖ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ፦ በሰጡት ዘለግ ያለ አስተያየት፦ «በአማራ ክልል የኦሮሞ ማህብረሰብ ልዩ ዞኖችና ተጎራባች የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስን የአማራ ክልል የፀጥታ ክፍል በጥንቃቄ ትክክለኛ መነሾውን ነቅሶ በማውጣት የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ በዘለቄታው የሰላም ዋስትና የማረጋገጥ ሕጋዊ ኃላፊነቱን በፅናት መወጣት ይጠበቅበታል» ብለዋል።

Karte Sodo Ethiopia ENG

የኢትዮጵያ ካርታ፦ በበርካታ ቦታዎች ግጭት ተደጋግሟል

ሲኖዶስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ብርቱ አደጋ የደቀነ ክስተት ከሰሞኑ መፈጸሙ በርካቶችን አስደንግጧል አስቆጥቷልም። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የጥምቀት በዓል ከዚህ ቀደም ችግር ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች ጭምር በድምቀት መከበሩ ብዙዎችን የማስደሰቱን ያህል የቤተክርስቲያን ቀኖና መጣሱ በርካቶችን አስከፍቷል። ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐሙስ ዕለት በምእላተ ጉባኤው ውሳኔ ባስተላለፈበት ወቅት «የመፈቅንለ ሲኖዶስ ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል» ብሏል። መንግሥቱ ታደሰ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ፦ «ነውር ስራ ነው የተሰራው እቃወማለሁ» ብለዋል እንደ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች። ሙሴ የጃናሞራው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ሕገ ወጥ ነው። በቋንቋ ለመገልገል ሲኖዶስ መክፈል አያስፈልገውም» ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 14 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በአባ ሳዊሮስ አማካኝነት ኢ-ሲኖዶሳዊ በሆነ መንገድ የቀኖና ጥሰት በመፈፀም ከሕግ ውጭ የተሰጠ የተባለውን ሲመት አውግዞ ከቤተክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለውን ሙሉ ሥልጣናቸውን በመሻር ከቤተ ክርስትያን እንደለያቸውም አሳውቋል።  ከጥር 18 ቀን፣ ጀምሮም በዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ ወስኗል። የሲመት ሰጪዎቹን ድርጊት እንደ ቅዱስ ሲኖዶሱ ምልኣተ ጉባኤ፦« ጸረ ቤተክርስቲያን» «ታሪክ ይቅር የማይለው ሕገወጥ ተግባር» እንዲሁም «ሕገ ወጥ» በማለት የኮነኑት የእምነቱ ተከታዮች ብቻ አይደሉም። ሸምስ መሀመድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «ሀይማኖት ጥንታዊ ነው፤ ዘመናዊ ሊሆን አይችልም። ውስጣዊ ፍላጎት እውነትኛነት እንጂ ውጫዊ ውሸትን አያንፀባርቅም) ስለዚህ ባለዘመኖች ሀገርና ህዝብ አትበጥብጡ» የሚል አስተያየት አስተላልፈዋል።

ልጅ አለን የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፦ «ቤተክርስቲያንን በፍቅር እንጂ ታግሎ ያሸነፈ የለም።እመነኝ ይህንን ፈተናም በድል ትወጣዋለች።ጠላቶቿም ያፍራሉ» ብለዋል። ከቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና በማፈንገጥ በሕገ ወጥ መንገድ በተከናወነው «ሢመተ ጳጳሳት» ከተሳተፉት መካከል ቀደም ሲል መጋቤ ሐዲስ አባ ጸጋ ዘአብ አዱኛ በመጸጸት ይቅርታ ጠይቀዋል። መጋቤ ሐዲስ አባ ጸጋ ዘአብ የይቅርታ ደብዳቤያቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) አቅርበው በመጸጸት ይቅርታ ስለጠየቁም የይቅርታ ደብዳቤያቸውን ተቀባይነት ማግኘቱም ተጠቅሷል። ሌሎችም የሚመለሱ እና የሚጸጸቱ ከሆነ ቤተክርስቲያን ለይቅርታ በሯ ክፍት መሆኑም ተገልጧል። «የሚያፈርሳት ይፈርሳል፤ ቤተክርስቲያን ዛሬም ትሻገራለች። እናመሰግናለን በእድሜና በፀጋ ይጠብቅልን።» አስተያየቱ አንበርብር ነጋሽ በተባሉ የዩትዩብ ተጠቃሚ የተሰጠ ነው።

እሸቱ አሰፋ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «ሁሉም ነገር በስረአት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን እምነትን የገፋና የጎጥ ምርጫ መደረጉ ነው በጣም በጣም ያሳዝናል» ብለዋል። «ችግሩን እዝህ ደረጃ ሳይደረስ ቀደም ብሎ ብፈቱ መልካም ነበር ችላ ማለት ላለመግባባት ዳርጎናል።» የአዱኛ ገብሩ አስተያየት ነው። አዲስ መጅሊስ አዲስ ሲኖድ እያሉ ፓለቲከኞች አጀንዳ ሲሰጡን እኛ ደግሞ ሌባው ኪሳችን እንዳይገባ ነቄ ሆንን ላሽ እንላለን» ያሉት ሰሚር ከድር የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። ሊሊ ገብረአብ የተባሉ ሌላ የዩትዩብ ተጠቃሚ «ቅድስት ቤተክርስትያን ክብሯን አሳየችን» ብለዋል። የቅዱስ ሲኖዶሱን የሐሙስ መግለጫ በቀጥታ ሥርጭት በተከታተሉበት ወቅት በሰጡት አስተያየት።

የአቶ በረከት መፈታት

ለአራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞው መንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ በረከት ስምኦን ረቡዕ ዕለት ከእስር መፈታታቸውም ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ አውታር የመነጋገሪያ ርእስ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢሕአዴግ)ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ በረከት ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት የተፈቱት የእስር ጊዜያቸውን በአመክሮ ጨርሰው መሆኑም ተገልጧል።

Äthiopien Bahirdar Covid19

የባሕር ዳር ከተማ ገጽታ

ስለመፈታታቸው ከተሰጡ አስተያየቶች ስድቦቹን ትተን የተወሰኑትን እናሰማችሁ።  «የእነአቶ በረከት ስምዖን ትውልድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባ የታሪክ ድርሻ ማብቅያ ሊኖረው ይገባል። የዚህም ጊዜ አሁን ነው።» ዋቅሹም መይሳ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ መልእክት ነው።  እዮብ ገብሬ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የአቶ በረከት ስምዖን ከእስር መፈታትን «ደግ ነገር ነው» በማለት «ቀድሞም መታሰር አልነበረባቸውም» ብለዋል። «በረከትን ፈትቶ አብዲ ዔሌን አለመፍታት ጥያቄ ያስነሳልና ቢታሰብበት መልካም ነው» ብለዋል። «በረከት ስምኦን ከእስር ተፈታ፣ እና አብዲ ኤሌ ለምንድነው የማይፈታው ጂ ፋሲል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ጥያቄ ነው።

አቶ በረከት ስምኦን በጥረት ኮርፖሬት ላይ በደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ተጠርጥረው ጥር 15 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸው ይታወሳል።  የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስድስት ዓመት እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸውም ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

Audios and videos on the topic