የሰላም ዉልና የሽብር ጥቃት በማሊ | አፍሪቃ | DW | 11.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሰላም ዉልና የሽብር ጥቃት በማሊ

በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ የደረሰዉ ጥቃት በሀገሪቱ መንግሥትና በቱአሬግ አማፅያን መካከል የተጀመረዉን የሰላም ድርድር ለማደናቀፍ ያለመ ነዉ በማለት መንግሥትና ፈረንሳይ አዉግዘዋል። በጥቃቱ አንድ የቤልጅና አንድ የፈረንሳይ ዜጎችን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።

ዛሬ ደግሞ በመንግሥትና በአማፂዎቹ መካከል የሚካሄደዉን የሰላም ድርድር የሚቃወሙ ወገኖች በሰሜን ማሊ በምትገኘዉ ኪዳል ከተማ ለሰልፍ ጎዳና ላይ መዉጣታቸዉ ተነግሯል። ስለማሊ ሰላም የተደረገዉ ዉይይት ጥቃት አድራሾቹን ፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች አለማካከቱ ተጨማሪ ቀጣይ የሽብር ጥቃቶችን ሊያስቀር እንደማይችል ተንታኞች እየጠቆሙ ነዉ።

መትረየስና ጓዳሠራሽ ተቀጣጣይ ፈንጂ ይዞ ነዉ ባለፈዉ ቅዳሜ ባማኮ ዉስጥ በዉጭ ዜጎች ወደሚዘወተረዉ የምሽት ክለብ ጥቃት አድራሹ ታጣቂ ዘዉ ያለዉ። «አላህ ታላቅ ነዉ» እያለ በመጮህም ዉስጥ ገብቶ ተኩስ ከፈተ። እማኞች እንደሚሉት ሰዉየዉ አልሞ የመጣዉ አንድ ፈረንሳዊን ለመግደል ሲሆን አንድ የቤልጅግ ዜጋንና ፈረንሳዊዉን እንዲሁም ሾፌሩን ጨምሮ የአምስት ሰዎችን ሕይወትን አጠፋ። ከአንድ ቀን በኋላ የአልጀሪያዉ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አል ሙራቢቱን ማለትም በግርድፍ ትርጉሙ «ተከላካዮቹ» የሚሰኘዉ ባለፈዉ ታህሳስ ሰሜን ማሊ ዉስጥ በፈረንሳይ ወታደሮች የተገደለ መሪያቸዉን ደም ለመበቀል የፈፀሙት ጥቃት መሆኑ ተገለጸ።

Mali UN in Kidal

ኪዳል የተመድ ጦር ሠፈር

የቡድኑ ጥቃት በዚህ አላበቃም እሁድ ዕለትም ሰሜን ማሊ ኪዳል የሚገኘዉ የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ MINUSMA የጦር ሠፈር በአዳፍኔ ተደበደበ። አንድ የቻድ ሰላም አስከባሪ ወታደርና ሁለት ሕፃናት በድምሩ ሶስት ሰዎችንም ገደለ። ለዚህ ጥቃት እስካሁን ማንም ኃላፊነቱን አልወሰደም። ሎንዶን የሚገኘዉ ቻተም ሃዉስ የተሰኘዉ ተቋም የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ ፖል ሜሊ የጥቃት አድራሹ ማንነት ለጊዜዉ ባይታወቅም ድርጊቱ ግን በጅሃዳዊዎቹ መፈፀሙ ግልፅ ነዉ ይላሉ።

«በሁለቱም ጥቃት አድራሾች መካከል በስሜትም ቢሆን የተገኛነ ነገር መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ከዚያ ባለፈ ግን በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ የድርጅት ግንኙነት መኖር አለመኖሩን በዚህ ደረጃ ማወቅ አንችልም።»

ማሊ የሚገኘዉ የተመድ ወታደራዊ ተልዕኮ በተለየ መልኩ በተደጋጋሚ የጥቃት ዒላማ መሆኑ ይታያል። ባለፈዉ ጥር ወርም ማሊ ከሞሪታኒያ በምትዋስነበት ድንበር አካባቢ የሚገኘዉ የድርጅቱ የጦር ሰፈር ጥቃት ደርሶበታል። ለያኔዉ ጥቃትም በማግሬብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰዉ የአልቃይዳ ክንፍ ኃላፊነቱን ወስዷል። እንዲህ ያለዉ የጥቃት ርምጃም በወታደራዊዉ ተልዕኮና በሲቪሉ ኗሪ መካከል ያለመተማመን ዉጥረትን ያነገሰ ሆኗል። በመሠረቱ እዚያ የሚገኙት ሲቪሉን ማኅበረሰብ ከጥቃት ለመከላከል ነበር። ያም ሆኖ ያልተገመተ ግድያ እንዳይደርስ በመስጋትም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ቁጥር እየቀነሰ ነዉ። ባለፈዉ የሳምንት መጨረሻ የደረሱት ጥቃቶችም ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸዉ የማይቀር ይመስላል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ገደማ በአልጀሪያ ሸምጋይነት የማሊ መንግሥትና የቱአሬግ አማፅያን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር አካሂደዋል። በድርድሩም የአዛዋድ ብሄራዊ የነፃነት ንቅናቄ እና የአዛዋድ የአረብ ንቅናቄ የተሰኙት ቡድኖች ተሳትፈዋል። አዛዋድ ነፃ ግዛት እንዲሆን የሚጠይቁትን የሰሜኑን የማሊ አካባቢ የሚወክል ነዉ። እንዲያም ሆኖ የሰላም ድርድሩ ከተካሄደ ከቀናት በኋላ ዋና ከተማዋ በተከታታይ ጥቃቶች ተናጠች። የሰላም ድርድሩ ፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎቹን አለማሳተፉን የጠቆሙት የቻተም ሃዉሱ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ ፖል ሜሊ፤ በእስላማዊ ፅንፈኞቹና ሰሜን ማሊ ራስ ገዝ ይህን በማለት በሚዋጉት አማፅያኑ መካከል ግልፅ ልዩነት መኖሩ መታወቅ እንዳለበት ያመለክታሉ።

«የማሊ ሰሜናዊ ክፍል ከማዕከላዊ መንግሥት እንዲላቀቅ ወይም ራስ ገዝ እንዲሆን የሚፈልጉት አብዛኛዉ የቱአሬግ ቡድኖች የተሳተፉበት የሰላም ሂደት አለ። ይህ ግን በየትኛዉም ዓይነት የሰላም ሂደት ወይም ፖለቲካዊ ድርድር ካልተሳተፉት በዓለም ደረጃ ጂሃድና ፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂነትን የማስፋፋት ዓላማ ካነገቡት ጅሃዳዊ ቡድኖች እንቅስቃሴ ፍፁም የተለየ ነዉ። እናም የሰላም ስምምነት ፈጽሞ የእነሱ ፍላጎት አይደለም።»

ፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎቹ ብዙ ሕዝብ ባልሰፈረበትና መንግሥታዊ አስተዳደር በሌለበት የሳልህ ዞን በስፋት ይንቀሳቀሳሉ። አደንዛዥ እፅ እና የጦር መሣሪያ በሕገ ወጥ በማዘዋወርና በመነገድም ገንዘብ ያካብታሉ።

Algerien Mali Friedensabkommen Unterzeichnung in Algier

የሰላም ድርድር በአልጀሪያ

ፖለቲካ መረጋጋትና ስርዓት የያዘ አስተዳደራዊ መዋቅር አያሳስባቸዉም። ለዓመታት በምዕራብ ማሊ አካባቢ ሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ብዙም አልታየም ነበር። ፕሪቶሪያ የሚገኘዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ዴቪድ ዙንሜኑ ግን እንዲሆን የመቀጠሉ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን በማስረዳት አስቀድሞ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት ያስረዳሉ።

«ስለላዉንና የፀጥታ ጥበቃዉን በተለይም ዒላማ ሊሆኑ በሚችሉ አካባቢዎች ማጠናከር ያስፈልጋል። ከምንም በላይ በዉጭ ዜጎችና በአዉሮጳዉያን ይጎበኛሉ በሚባሉ ስፍራዎችን የሚመለከቱ መረጃዎች አሉ። እነዚህ ቡድኖች የመገናኝ ብዙሃንን ከፍተኛ ትኩረት ማግኘት ይፈልጋሉ። በተለይም አንድ አዉሮጳዊ ላይ ጥቃት ሲደርስ ትኩረት እናገኛለን ብለዉ ይተማመናሉ።»

ከማሊ መንግሥት ጋ ድርድር ያደረጉት የቱአሬግ አማጽያን የሰላም ስምምነቱን መቼ እንደሚፈራረሙት እስካሁን ግልፅ የተሰማ ነገር የለም። ያም ቢሆን ግን በእነሱና በመንግሥት መካከል የሚኖረዉ የሰላም ስምምነት ጅሃዳዊ ጥቃት አድራሾቹን ሌላ ጥፋት ከመፈፀም ያስቀራቸዋል ማለት ግን አይቻልም።

ማደሊነ ማየር/ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic