የሮሽቶኩ ጥቃት 20ኛ አመት መታሰቢያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የሮሽቶኩ ጥቃት 20ኛ አመት መታሰቢያ

በጀርመንዋ የወደብ ከተማ ሮሽቶክ የዛሬ 20 አመት በስደተኞች ላይ የተፈፀመው ዘረኛ ጥቃት በትናንትናው እለት በመላ ጀርመን ታስቧል ። በወቅቱ ሆ ብለው የተነሱ ወጣት አመፀኞችና ቀኝ አክራሪዎች፣ የተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ህንፃን በእሳት በማቃጠል ያደረሱት ጥቃት

በጀርመንዋ የወደብ ከተማ ሮሽቶክ የዛሬ 20 አመት በስደተኞች ላይ የተፈፀመው ዘረኛ ጥቃት በትናንትናው እለት በመላ ጀርመን ታስቧል ። በወቅቱ ሆ ብለው የተነሱ ወጣት አመፀኞችና ቀኝ አክራሪዎች፣ የተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ህንፃን በእሳት በማቃጠል ያደረሱት ጥቃት ከ2ተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ጀርመን ውስጥ ከተፈፀሙት መሰል ጥቃቶች የከፋው ነበር ። ይህ እርምጃም በጀርመን ከባድ መዘዞችን አስከትሏል ።

ሮሽቶክ በተባለው በሰሜን ምሥራቅ ጀርመንዋ የወደብ ከተማ የሚገኝ የስደተኞች መኖሪያ ህንፃ ላይ ቀኝ ፅንፈኞችና የአካባቢ ነዋሪዎች ዘግናኝ ጥቃት የፈፀሙት እጎአ ነሐሴ 22 1992 ነበር ። ጥቃቱ የደረሰበት ህንፃ  በሰሜን ጀርመኑ የሜክለንቡርግ ቮርፖመርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር በስደተኞች መቀበያ ማዕከልነት የሚያገለግል ስፍራ ነበር ። በወቅቱ ቀኝ ፅንፈኞች መፈክሮችን እያሰሙ ከህንፃው ሰው እንዳይወጣና እንዳይገባ በመከልከል ድንጋይ ና በነዳጅ የተሞሉ በእሳት የተያያዙ ጠርሙሶችን ወደ ህንፃው በመወርወር ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ። ወጣቶቹ ህንፃውን ሲያቃጥሉም በአካባቢው ይተላለፉ የነበሩ ሰዎች አድናቆታቸውን ይገልፁላቸው ነበር ። በሮሽቶክ የውጭ ዜጎች ጉዳይ ሃላፊ ቮልፍጋንግ ሪሽተር ጥቃቱ በተባባሰበት ወቅት ህንፃው ውስጥ ነበሩ ። 

« የመኖሪያውን ህንፃ ከውጭ ሆነን ስንመለከተው በዛ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ያገኙትን ያለ ምህረት በማጥፋት ስሜት ተነሳስተው ነበር የሚያጠቁት ። እኛም በወቅቱ ጥቃት ደርሶብናል ምንም አዙሮ ማየት ማመዘን የሌለበት ጥቃት ነበር የተሰነዘረው ። መቶ ሰው በዚያ ቤት ውስጥ ኖረ አልኖረ ጉዳያቸው አልነበረም ። እኛም በዚያ ውስጥ ልንገደል እንችል ነበር ። » 

በሚያስገርም ሁኔታ በእሳት ቃጠሎ የተጎዳ ሰው አልነበረም ። ነዋሪዎቹ ወደ ህንፃው ጣሪያ በመሸሽ ከእሳቱ ማምለጥ ችለዋል ። ጥቃቱ ቀጥሎ ከ 2 ቀንና ለሊት በኋላ ነበር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ስደተኞቹን ወደ ሌላ ስፍራ ለማጓጓዝ የበቁት ። ከዚያ በኋላም ቢሆን አመፀኞቹ ህንፃው ውስጥ በቀሩት ቬይትናማውያንና በፖሊስ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አላቆሙም ። ዘግይቶ በስፍራው የደረሰው ፖሊስ አመፀኞችን በመያዝ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ቢሞክርም ከአቅሙ በላይ ነበር የሆነው ። ከሁለቱ ጀመኖች ውህደት በኋላ ሥራ አጥነት በተስፋፋበት በምሥራቅ ጀርመን ሆድ ለባሰው ህዝብ ፖለቲከኞች ሁኔታዎችን ከማርገብ ይልቅ ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን ገቡ በማለት የተጋነኑ መልእክቶችን ማስተላለፋቸው ወጣቶቹ ጥቃቱን እንዲፈጽሙ በማነሳሳት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ ሪሽተር ። 

« ራድዮውም ቴሌቪዥን መመልከት በቂ ነበር ። ስደተኞች ይጎርፋሉ መርከቡ ጢም ብሎ, ሞልቷል እየተባለ ና ተገን ጠያቂዎችም ወንጀለኛ መሆናቸው ይነገር ነበር ። ይህም ለእነርሱ የጥቃት እርምጃ አስተዋጽኦ አድርጓል ። በግልፅ የሚስተዋል ነበር የቀኝ ኃይሎች ከ 2ተኛው ቀን አንስቶ ጉዳዩን የመነጋገሪያ ርዕስ ከማድረጋቸውም በላይ ጥቃት ወደ ሚፈፀምበት  ሮሽቶክ እንደ ቱሪስት ይሄዱ ነበር ። ለዚህ እርምጃም ዘረኝነትና የውጭ ዜጎች ጥላቻ እንደገፋፋቸው በሚያቀርቡት የመከራከሪያ ሃሳብ ሁሉ ይናገሩ ነበር »

ጥቃቱ ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለበት ምክንያት አሁንም ያጠያይቃል ። በበርሊኑ ነፃ ዩኒቨርስቲ ዘረኝነትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ሃዮ ፉንከ አመጹ ርስ በርስ የተያያዙ ድክመቶች ውጤት ነው ይላሉ ።

« እንደ እኔ ትዝብት ወሳኙ ጉዳይ የከተማዋ አስተዳደር የፊደራል ክፍለ ሃገር እንዲሁም በከፊልም ቢሆን የፌደራሉ መንግሥት በሊሽተንሃገን ጥቃቱ እንዲባባስ አድርገዋል ። ማድረግ የሚገባቸውን በቂ እርምጃ አልወሰዱም። ስለዚህ ጥቃቱን ለ ለማስቆም የፖለቲካ ፈቃደኝነት ባለመታየቲ ስህተት ተሰርቷል ስለዚህ ባለሥልናቱ እያወቁ አንዲህ አይነት የማጥፋት ሙከራ ሲደረግ ተመልክተዋል »  

ለአመጹ ፖለቲካዊ ምላሽ የተሰጠው ዘግይቶ ነው ። በአመፁ ተጠያቂ የተባሉ 44 ሰዎች ከ 1 እስከ 3 አመት የሚደርስ እስራት ተበይኖባቸውል ። የዚያን ጊዜው የሮሽቶክ ከንቲባና የሜክለንቡርግ ቮርፖመርን ፊደራዊ ክፍለ ሃገር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ከሥልጣናቸው ለመውረድ ተገደዋል ። እስካሁን ግን በተመሰቃቀለው የፖሊስ የወቅቱ ዘመቻ ተጠያቂው የማን እንደሆነ ግልፅ አይደለም ። የመኖሪያ ህንፃ ውን ከጥቃት እንዲከላከል የተሠማራው የፖሊስ ኃይል ከስፍራው ሲለቅ በምትኩ ሌላ ሳይተካ ከቀረ በኋላ ነበር አመጹ ተባብሶ ብዙ ጉዳት የደረሰው ።   

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 23.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15veb
 • ቀን 23.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15veb