የርዕሰ ዓዉደ ዓመት ድግስና ወጉ | ባህል | DW | 03.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የርዕሰ ዓዉደ ዓመት ድግስና ወጉ

አዲሱ የጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ም እንደ ሀገራችን ርዕሰ ዓዉደ ዓመት፤ በመስከረም ወር አጥብያ በሚያብበዉ በአደይ አበባ ታጅቦ፤ ችቦ አቀጣጥሎ ባይጠባም፤ ይህንኑ የቀን ቀመር የሚከተሉ በዓለም ዙርያ በሚገኙ ሀገራት የሚኖር በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በርችት ችቦ ተኩስ አላፊዉን የ 2012 ዓ,ም ሸኝቶ አዲሱን አመት ተቀብሎታል።

አብዛኛዉ ዓለም ዘመኑን የሚያሰላበት የጎርጎሮሳዉያኑ ቀመር የዘመን ፤ መለወጫ በዓልን ደግሶ ከትናንት ጀምሮ ቀስ እያለ ወደ ዕለታዊዉ ስራዉ መግባት ጀምሮአል። ከዓለም አገራት ቀደም ብላ አዲሱን ዓመት ጀመረችዉ የሳሞአ ደሴት ስትሆን፤ የአዉስትራልያዋ መዲና ሲድኒ ደግሞ በመለጠቅ የመጀመርያዉ ደማቅ እና በሰፊዉ የዘመን መለወጫ ድግስን ማድረግዋም ተዘግቦላትል።

Silvester 2012 Neujahr 2013 Düsseldorf

አዲስ ዓመት በዱስልዶርፍ

በዚሁ የአዲስ አመት መቀበያ ድግስ በአዉስትራልያዋ ሲድኒ ከተማ ከሰባት መቶ ቶን የሚበልጥ ርችት ተኩስ በዓሉን አድማቂ ነበር። የጀርመንን ትልቁ የዘመን መለወጫ ድግስን ያስተናገደችዉ ርዕሠ-ከተማ በርሊን ናት። በዓሉን ለማክበር የብራንደንቡርግ ቱር በተሰኘዉ ታሪካዊ ሥፍራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ታድሞ እንደነ ነበር። ህዝቡ እኩለ ለሊት ላይ የባተዉን አዲስ ዓመት ለመቀበል ወደ ስፋራዉ መጉረፍ የጀመረዉ ከምሽቱ 12 ሰአት ጀምሮ እንደነበር በአካባቢዉ የተገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃኖች ዘግበዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ዕለቱ ሞቃታማ ስለነበር ነዉ። እንደ አየር ንብረት ምርምር ጉዳይ ቢሮ ዘገባ በዚህ በሰሜን ንፍቀ ክበብ አካባቢ በሚገኙ በርካታ ሀገሮች የአየር ሁኔታዉ ተለዋዉጦ በክረምቱ ወራት እንደሚሆነዉ በረዶ እንብዛም አልጣለም ዝናብ ብቻ የሚጥልባቸዉ ቦታዎች በዝተዉ ታይተዋል። ሞቃታማ ሲባል ከሚታየዉ የክረምት ወራት አንፃራዊ ሆኖ ተነገረ እንጂ፤ ብርዱ አንዘፋዛፊ መሆኑ አሁንም የማይታበል ነዉ። ወደ ተነሳሁበት ወደ አዲሱ አመት የበርሊኑ ድግስ ልመለስ፤ እና በበርሊኑ የብራንድን ቡርገር ቱር አዲሱን ዓመት መቀበያ ስድስት ሽህ ርችቶች ተተኩሰዉ የጠቆረዉን ሰማይ ማድምቀዉ የድግሱን ታዳሚ አስቦርቀዋል። ይኸዉ በመዲናዋ የነበረዉ ዝግጅት በርግጥ በቀጥታ በቴሌቭዥን ተሰራጭቶአል በተለያዩ የቴሌቭዥን ካናሎችም በየፌደራል ክፍለ ሃገራቱ የአዲስ አመት መቀበያ ድግስ በቀጥታ ስርጭት ለሃገሪዉ ተመልካች ተላልፎአል። ተሰናባቹ ዓመት ለመጠናቀቅ ጥቂት ሰዓታት እንደቀሩት፤ የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል፤ ለህዝባቸዉ በብዙሃን መገናኛ ባስተላለፉት የእንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ መልክታት፤ ህዝባቸዉ በአዉሮጳ ስለ ተከሰተዉ የፋይናንስ ቀዉስ ታጋሽነትን እንዲያሳይ ጠይቀዉም ነበር

Berlin Silvester Feuerwerk Brandenburger Tor Quadriga Neujahr

የአዲስ ዓመት ድግስ በበርሊን

«ከትልቅ ሃሳብና ችግር ጋር አዲሱን ዓመት የሚቀበሉት በርካቶች እንደሆኑ በርግጥ አዉቃለሁ። በርግጥም በመጭዉ ዓመት በኤኮኖሚዉ ይዞታ አኳያ ቀላል ሳይሆን ከባድ ነገር ነዉ የሚገጥመን። ታድያ ይህ ሁኔታ ሊያበረታን እንጂ፤ እምነት ሊያሳጣዉንና ሊያዘናጋን አይገባም። እዚህ ላይ ሁለት አስደናቂ የህክምና ዉጤቶችን ልነግራችሁ እወዳለሁ። ከጥቂት ቀናት በፊት ሲወለድ ጀምሮ የመስማት ችግር የነበረበት አንድ የ10 ዓመት ልጅ ተዋዉቄ ነበር፤ ይህ ልጅ በቀዶ ህክምና ሰዉነቱ ዉስጥ እጅግ የረቀቀ መሳርያ ተገጥሞለት ከበሽታዉ ተፈዉሶአል። ዛሪ ታድያ ይህ ህጻን ያለም ምንም ችግር ሙዚቃ ማዳመጥ ይችላል ትምህርት ቤት ይሄዳል። ሌላም አንዲት በልብ ቀዶ ጥገና ተመሳሳይ መሳርያ የተገጠመላት ሴት ተዋዉቄ ነበር፤ ይህች ልጅ አሁን ስፖርት መስራት ትችላለች፤ እንደማንኛዉም ጤነኛ ሰዉ ህይወትዋን ትመራለች። ታድያ እነኝህ የኛ የህክምና ምሁራን በህክምና ዘርፍ ካስኙዋቸዉ እፁብ ድንቅ ነገሮች በጥቂቱ ኛቸዉ ።» ስለዚህም አሉ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወደ ሰባት ደቂቃ ያህል ባሰሙት ዓመታዊ የአዲስ ዓመት መግለጫቸዉ መጨረሻ «ስለዚህም አዲሱን ዓመት ጥንካርያችንን በጋራ የበልጥ የምናሳይበት፤ በአንድነታችን ፤ ሁልግዜ አዲስ ነገር የመፍጠር ችሎታችን የምናሳይበት እና የኤኮኖሜያችን ጥንካሪ የሚያግኝበት ይሆናል። ይህ ከሆነ ጀርመን ወደፊትም ሰብዓዊ እና ስኬታማ እንደሆነች ትቀጥላለጭ።»

በአገራችን በመስከረም ስፍራዉ ሁሉ ለምለም ፤እዮሃ ብለን 2005 ከተቀበል እነሆ አራተኛ ወራችንን ልናጠናቅቅ ነዉ። የጎርጎረሳዉያኑን የቀን ቀመር በሚከተሉ አገራት የሚኖሩ አብዛኞች ኢትዮጵያዉያን ከባልንጀሮቻቸዉ ጋር የጎርጎረሳዉያኑና የኢትዮጳያን አዲስ አመት እንደሚያከብሩ ይታወቃል ታድያ ሁለት ርዕስ አዉዳመትን በስድስት ወር ግዜ ዉስጥ ሁለት ግዜ ይሆናል የሚያከብሩት ።

Silvester 2012 Neujahr 2013 Russland

የአዲስ ዓመት ድግስ በሞስኮ

በአ,አ ዩንቨርስቲ በቋንቋ ተቋም ዉስጥ የግዕዝ ቋንቋ መምህር የሆኑት ዶክተር ሰርገዉ ገላዉ በአዲስ አመትሰፊ ባህል እንዳለን አጫዉተዉናል።

ሌላዉ በኤሊባቡር ነዋሪ የሆኑት መምህር በቀለ ለሙ በአካባቢያቸዉ ርዕሰ ዓዉዳመት በድምቀት እንደሚከበር እና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል እንደሆና፤ አዲስ አመትን የሚያከብር እድለኛ ነዉ የሚል አነጋገርም እንዳለ ነግረዉናል። በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓል ከሞላ ጎደል፤ ተመሳሳይ ነዉ ማለት ይቻላል ። የጎርጎረሳዉያኑን ቀመር በምትከተለዉ በደቡብ አፍሪቃ የአዲስ ዓመት አቀባበል ባህል እንዴት ይሆን?

በሩስያ የዘመን መለወጫ በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል። በርካታ ኢትዮጳያዉያን በሩስያ የተለያዩ ግዛቶች ይኖራሉ። በሩስያዋ ሁለተኛ ከተማ በሆነጭዉ ሳንት ፔተርስበርግ ከተማ ከ 25 ዓመት በላይ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገብረ ወልድ በሰፊዉ አወያይተዉናል። ቻይናዉያን የዘመን መለወጫ በዓላቸዉን የሚያከብሩት በየካቲት መጨረሻ ላይ ቢሆንም በርካታ ቻይናዉያን የጎርጎሮሳዉያኑን ዘመን መለወጫ ርችት በመተኮስ ተቀብለዋል። በነገራችን ላይ በቻይናዉያኑ የጨረቃ የቀን ቀመር መሰረት ዘንድሮ የድራኩላ ዓመት ሲሆን፤ በመጭዉ ፀደይ ላይ የሚቀበሉት ዓመት የእባብ አመት ይባላል።

Silvester 2012 Neujahr 2013 Dubai

የአዲስ ዓመት ድግስ በዲባይ

825 ሜትር ርዝመት ካለዉ ከዱባዩ ከቡርጃ ኸሊፋ ህንፃ ዙሪያ በተተኮሰዉ የዘመን መለወጫ ርችት በርካታ ሀገር ጎብኝዎች ተማርከዉ እንደ ነበር በዓለም የተሰራጨዉ የምስል ዘገባ አሳይቶአል። ሕንድ በአስገድዶ መድፈር ጥቃት ህይወትዋ ላለፈዉ ባለፈዉ ወጣት ምክንያት በአብዛኞቹ ከተሞቿ የአደባባይ የዘመን መለወጫ ድግስ ተሰርዞ ነበር። በአፍሪቃችን በኮት ዲቯር እና በአንጎላ በዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት በነበረ ስነ-ስርዓት ላይ በተከሰተ አደጋ በርካቶች መሞታቸዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ም የዘመን መለወጫ በዓል የሃዘን ድባብ እንዲያጠልበት ያደረጉ ክስተቶችም ነበሩ። አድማጮች የጎርጎረሳዉያኑን የዘመን ቀመር በማስመልከት የያዝኩትን ቅንብሪን እዚህ ላይ አጠናከኩ፤ በጎርጎረሳዉያኑ የዘመን ቀመር አዲሱን ዓመት ለተቀበላችሁ መልካም አዲስ አመት እያልኩ እሰናበታለሁ። ሙሉዉን ቅንብር ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 03.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17D5m
 • ቀን 03.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17D5m