የርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ እና የፈረንሳይ ሚና | አፍሪቃ | DW | 13.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ እና የፈረንሳይ ሚና

ርዋንዳ በሀገርዋ እአአ ሚያዝያ ሰባት፣ 1994 ዓም የጎሳ ጭፍጨፋ የተካሄደበትን 21ኛ ዓመት ባሰበችበት በዚህ ሳምንት የፈረንሳይ መንግሥት ጭፍጨፋውን በተመለከተ እስከዛሬ በድብቅ ይዞት የቆየውን መረጃ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

እአአ ከ1990 እስከ 1995 ዓም ድረስ በነበሩት ዓመታት የተሰበሰቡ መረጃዎችን የያዙት ሰነዶች ፈረንሳይ በርዋንዳ ታሪክ ውስጥ ዘግናኝ በሆነው የጎሳ ጭፍጨፋ ላይ የተጫወተችውን ትክክለኛ ሚና ሊያሳይ ይችል ይሆናል ተብሎ ነው የሚገመተው።

የታሪክ ጠበብት እና የሰለባዎች ተሟጋቾች ድርጅቶች ካለፈው ረቡዕ ወዲህ እነዚህን ሰነዶች የመመልከት ዕድል አግንተዋል። ዕድሉ ካጋጠማቸው መካከል አንዱ የሆኑት «ኢቡካ» የተሰኘው የሰለባዎች ጉዳይ ተመልካች ድርጅት የቤልጅየም ቅርንጫፍ ቃል አቀባይ ኤሪክ ሩታይሲሬ እንዳመለከቱት፣ የጎሳው ጭፍጨፋ በተካሄደባቸው ጊዚያት የፈረንሳይ መንግሥት በርዋንዳ ይገኙ ከነበሩት ተወካዮቹ ጋ ያካሄደውን የሀሳብ ልውውጥ የመሳሰሉ መረጃዎች እንደሚያገኙ ተስፋ ተደርጓል። በመሆኑም፣ ፈረንሳይ በጎሳው ጭፍጨፋ ላይ ሳትጫወተው አልቀረችም በሚል የሚሰማው ጥርጣሬ ተጣርቶ ሀቁ ሊታወቅ ይገባል ባዮች መሆናቸውን ነው ሩታይሲሬ የገለጹት።

« ብዙ መረጃ ይገኛል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የፈረንሳይ የጦር ተልዕኮ እና ፈረንሳውያን ታዛቢዎች የጎሳው ጭፍጨፋ ከመካሄዱ በፊት፣ በተካሄደበት እና ከተካሄደም በኋላ በርዋንዳ ይገኙ እንደነበር ይታወቃል። እና በዚያ በነበሩት የፈረንሳይ ጦር አባላት መካከል፣ እንዲሁም፣ በኤሊዜ ቤተመንግሥት እና ርዋንዳ በነበሩት ተወካዮቹ መካከል ብዙ የመረጃ ልውውጥ እንደነበረ እንገምታለን። »

የርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ የተጀመረው ከብዙኃኑ የሁቱ ጎሳ የተወለዱት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጁቨናል ሀቢያሪማና ከቡሩንዲው አቻቸው ሲፕሪየን ንታሪያሚራ ጋ እአአ ሚያዝያ ስድስት፣ 1994 ዓም ይበሩበት በነበረው አይሮፕላን ላይ በተጣለ ጥቃት ተሳፋሪዎቹ በጠቅላላ ሕይወታቸውን ባጡበት ጊዜ ነበር። ይህንን ጥቃት በተከተሉት ሶስት ወራት ቢያንስ 800,000 የውሁዳኑ የቱትሲ ጎሳ እና ለዘብተኛ የሁቱ ጎሳ አባላት ተገድለዋል። ሀቢያሪማና እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ ከርዋንዳ መንግሥት ጋ የጠበቀ ግንኙነት የነበራት ፈረንሳይ በ1994 ዓም የጎሳ ጭፍጨፋ ላይ ቀጥተኛ ሚና እንደነበራት የርዋንዳን ታሪክ በቅርብ የሚከታተል ሁሉ እንደማይጠራጠረው ነው በለንደን የአፍሪቃ እና የዐረቡ ዓለም ጥናት ተቋም ተንታኝ ፊል ክላርክ የሚናገሩት።

« ፈረንሳይ ለጎሳው ጭፍጨፋ ተጠያቂ የነበሩትን የርዋንዳ መንግሥት የኢንተራሀምዌ ሚሊሺያዎችን በማሰልጠኑ ላይ ተሳትፋለች። ከ1992 እስከ 1994 ዓምም ለሀቢያሪማና መንግሥት የጦር መሳሪያ በቀጥታ አቅርባለች። ጋዜጠኞች እና የታሪክ ምሁራን ይህን መረጃ ባለፉት 20 ዓመታት በሚገባ መዝገበው አስቀምጠውታል። »

በሀቢያሪማና መንግሥት አንፃር ይዋጋ የነበረው የርዋንዳ አርበኞች ግንባር ለጎሳ ጭፍጨፋው ተጠያቂ በነበሩት የኢተራሀማዌ ሚሊሺያዎች ላይ ድል በተቀዳጀበት በሰኔ ወር ነበር ግድያው ያቆመው። እስከዚያን ጊዜ ድረስ ድምጿ ብዙም ያልተሰማው ፈረንሳይ ያኔ የርዋንዳን ሲቭል ሕዝብ ለመከላከል በሚል «ቱርኳዝ» የተባለ ተልዕኮ አነቃቃች። ይሁንና፣ ፈረንሳይ ሲቭሉን ለመከላከል በደቡብ ምዕራብ ርዋንዳ ያቋቋመችው የተከለለ አካባቢ ከርዋንዳ አርበኞች ግንባር በመሸሽ ላይ የነበሩት ነፍሰ ገዳዮቹ የኢንራሀማዌ ሚሊሺያዎች ያኔ ዛይር ተብላ ትጠራ ወደነበረችው ጎረቤት ዴሞክራቲክ ኮንጎ እንዲሸሹ መንገዱን ነበር ያመቻቸላቸው።

ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደነበር በዚሁ የፈረንሳይ «ቱርኳዝ» ተልዕኮ የተሳተፉ ጊዮም ኦንሴልን የመሳሰሉ ወታደሮች ሳይቀሩ አረጋግጠዋል። በዚሁ ተልዕኮ ፈረንሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ የርዋንዳ ዜጎችን ማዳኗን ብታስታውቅም፣ ያኔ ሻምበል የነበሩት ኦንሴል አባባሉ እውነታውን የማያንፀባርቅ መሆኑን ነው የገለጹት። እርግጥ፣ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የፈረንሳይ ወታደሮች በሽሽት ላይ ከነበሩት የሀቢያሪማና ሁቱ ሚሊሺያዎች በአስር ሺህ የሚቆጠር የጦር መሳሪያ እና ፈንጂዎችን ቢወርሱም፣ በሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ በተላለፈ አንድ ትዕዛዝ መሰረት የሰበሰቡትን የጦር መሳሪያውን በአንድ የጎረቤት ዛይር መጠለያ ለነበሩት የሁቱ ሚሊሺያዎች በመመለስ፣ የስደተኛውን ጣቢያ ወደ ጦር ሰፈር እንደቀየሩ ነው ኤንሴል ለፈረንሳውያን ሳምንታዊ መጽሔት «ዠን አፍሪክ» ያስታወቁት።

እንደ ፊል ክላርክ ግምት፣ ፈረንሳይ እስከዛሬ በድብቅ ይዛቸው የቆየችውን ሰነዶቹን ባሁኑ ጊዜ ይፋ ለማድረግ ላቀደችበት ውሳኔዋ ዩኤስ አሜሪካ የርዋንዳን የጎሳ ጭፍጨፋ የሚመለከት መረጃ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይፋ ያወጣችበት ርምጃዋ ምክንያት ሊሆን ችሏል።

« ፈረንሳይ ሰነዶቹን በዚህ ሳምንት በይፋ ለማውጣት የወሰነችው ዩኤስ አሜሪካ ስለጭፍጨፋው ብዙ መረጃዎችን በማውጣቷ ምክንያት ነው። እነዚሀ ያሜሪካውያኑ መረጃዎች ፈረንሳይ በጎሳው ጭፍጨፋ ላይ ሚና ስለመጫወት አለመጫወቷ ያወሳሉ። በሌላ አነጋገር መረጃዎቹ ለፈረንሳይ የማይመቹ ናቸው። ስለዚህ ፈረንሳይ ሰነዶቹን በዚህ ሳምንት ይፋ ለማድረግ የወሰነችው ስለ 1994 ዓም ጭፍጨፋ የራሷን መረጃ ለማቅረብ ይመስለኛል። »

Frankreich Nicolas Sarkozy und Paul Kagame

ፈረንሳይ የጎሳውን ጭፍጨፋ በተመለከተ ለብዙ ዓመታት ዝምታን መምረጧ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ አልቀረም። ከዚህ በተጨማሪ አንድ የፈረንሳይ ዳኛ የሀቢያሪማና አይሮፕላን ተመቶ የወደቀበትን ጉዳይ በተመለከተ እአአ በ2006 ዓም የማጣራት ስራ ባካሄዱበት ወቅት በርዋንዳ አርበኞች ግንባር መሪ እና በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ባስታወቁበት ጊዜ ኪጋሊ ከፈረንሳይ ጋ የነበራትን ዲፕሎማቲካዊ ግንኙነት ለጥቂት ዓመታት ማቋረጧ የሚታወስ ነው።

ግንኙነቱ በቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኒኮላ ሳርኮዚ አመራር ዘመን እንደገና ቢታደስም፣ አሁንም እክል እንዳላጣው ፊል ክላርክ ገልጸዋል። ለምሳሌ፣ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ፈረንሳይ በጎሳው ጭፍጨፋ ላይ ከሀቢያሪማና መንግሥት ጎን ተጠያቂ ናት ሲሉ ወቀሳ ከሰነዘሩ በኋላ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ርዋንዳ አምና 20ኛውን የጎሳ ጭፍጨፋ ባሰበችበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሳይሳተፉ መቅረታቸው ይጠቀሳል።

የፈረንሳይ መንግሥት የጎሳውን ጭፍጨፋ በተመለከተ እስከዛሬ በድብቅ ይዞዟቸው የቆዩትን ሰነዶች አሁን ይፋ የሚያደርግበት ርምጃው ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል ወሳኝ ድርሻ ሊያበረክት እንደሚችል ተስፋ ቢደረግም፣ የርዋንዳ መንግሥት ባለሥልጣናት ከፈረንሳይ የሚጠብቁት ይፋ የይቅርታ መጠየቂያ እስካሁን አልቀረበም።

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic