የርዋንዳና የኮንጎ የጋራ የጥቃት ዘመቻ | ኢትዮጵያ | DW | 24.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የርዋንዳና የኮንጎ የጋራ የጥቃት ዘመቻ

የርዋንዳ መንግስት ጦር ኃይላት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት አሁን ኮንጎ ገባ።

አሁን የተያዙትጀነራል ሎውሮ ንኩንዳ

አሁን የተያዙትጀነራል ሎውሮ ንኩንዳ

የርዋንዳና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በደረሱት ስምምነት መሰረት፡ የርዋንዳ ጦር አሁን በይፋ ኮንጎ በሀገር ዋሩ ምስራቃዊ ከፊል በሚንቀሳቀሱት የርዋንዳ ሁቱ ዓማጽያን አንጻር ለምታካሂደው ትግል የጦር ርዳታ ይሰጣሉ። በርዋንዳ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ለተካሄደውና የስምንት መቶ ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ህይወት ላጠፋው የጎሳ ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑትና ለርዋንዳ ነጻነት የሚታገለው በምህጻሩ ኤፍ ዲ ኤል አር በመባል የሚታወቀው ቡድን ሁቱ ዓማጽያን እአአ በ 1994 ዓም ነበር ከርዋንዳ በመሸሽ ምስራቅ ኮንጎ የሰፈሩት። እነዚሁ የሁቱ ዓማጽያን በርዋንዳ መንግስት አንጻር ከጀመሩት ጥቃታቸው ጎን በምስራቃዊ ኮንጎ በሚኖረውም ህዝብ አንጻር የኃይል ርምጃ የወሰዱበት ድርጊት ነው የኮንጎ መንግስት በአንጻራቸው እንዲታገል ምክንያት የሆነው። በዚሁ አካባቢ የሚኖሩት የኮንጎ ቱትሲዎችም ከነዚሁ የሁቱ ዓማጽያን ስጋት ስለተደቀነባቸው እስከጥቂት ቀናት በፊት ድረስ በጀነራል ሎውሮ ንኩንዳ የተመራው ለኮንጎ ቱትሲዎች ደህንነት የሚታገለው በምህጻሩ ሲ ኤን ዲ ፒም በኤፍ ዲ ኤል አር ዓማጽያን አንጻር ውጊያ ሲያካሂድ ቆይተዋል። ይኸው ከርዋንዳ ድጋፍ ሲያገኝ በቆየው በሲ ኤን ዲ ፒ መካከል ልዩነት ተፈጥሮ መሪው ንኩንዳ ከመሪነቱ ስልጣናቸው ከተወገዱ በኋላ ተቀናቃኞቻቸው ከኮንጎ መንግስት ሰላም በመፍጠር በመንግስቱ ጦር ውስጥ ተዋህደው ለመስራት፡ በዚህም በሁቱ ዓማጽያን አንጻር ባንድነት ለመታገል ስምምነት ደርሰዋል።

የርዋንዳና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ጦር ኃይላት አሁን በሁቱ ዓማጽያን አንጻር በተጀመረው የጋራ የጥቃት ዘመቻ ላይ አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል። የሁለቱ ሀገሮች የጋራ ጦር በሁቱ ዓማጽያን አንጻር ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኪቩ አካባቢ በቡናጋና በሚገኘው የሎውሮ ንኩንዳ ቡድንም ላይ ጥቃት በመሰንዘር ንኩንዳ ትናንት ቀድሞ ይረዱዋቸው በነበሩት በርዋንዳ ወታደሮች መያዛቸውን በኮንጎ የተሰማራው የተመ ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ በምህጻሩ ሞንዩክ ቃል አቀባይ ዦን ፖል ዲትሪኽ አስታውቀዋል።

«በመጀመሪያ ባለፈው ሌሊት ተባራሪ ወሬ ከሰማን በኋላ፡ዛሬ ጧት በተረጋገጠ ሁኔታ፡ የመያዛቸው ዜና ደርሶናል። ንኩንዳ ትናንት ማታ ከምሽቱ ዐራት ሰዓት ተኩል ላይ ከሩዋናዳና ኮንጎ የተውጣጣ የተባበረ ጦር ቡናጋና ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን ምሽጋቸውን ሲያጠቃባቸው የመከላከል ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ነው እጃቸውን የሰጡት። የተያዙትም፣ ወደ ሩዋንዳ ለመሻገር ሲሞክሩ ነው። ንኩንዳ፣ በተያዙበት ወቅት ፣ 3 ባታሊዮን የሚሆን ታማኝ ጦር ነበራቸው። »

ርዋንዳና ኮንጎ ካሁን ቀደምም የጋራ ጠላታቸው በሆኑት በሁቱ ዓማጽያን አንጻር ባንድነት ለመታገል ብዙ ጊዜ ቢስማሙም፡ ስርዓት አልባ የሆኑት የኮንጎ ወታደሮች ከኤፍ ዲ ኤል አር ጋር ተባብረዋል በሚል ርዋንዳ ባሰማችው ወቀሳ የተነሳ ሁለቱ ሀገሮች ስምምነታቸውን በተግባር መተርጎም ሳይችሉ መቅረታቸው አይዘነጋም። ርዋንዳና ኮንጎ ካለፈው ማክሰኞ ወዲህ በጀመሩት ጥቃታቸው በሰሜን ኪቩ ያሉ የሁቱ ኤፍ ዲ ኤል አር ዓማጽያን ሰፈሮችን በተዋጊ አይሮፕላኖች መደብደባቸውን ያይን ምስክሮች ገልጸዋል። የኮንጎ ማስታወቂያ ሚንስትር ላምቤ አሜንዴ ኦማላንጋም ዘገባውን አረጋግጠውታል።

« የጥቃቱን ዘመቻ ጀምረናል። እና በዚሁ ጥቃት የኤፍ ኤዲ ኤል አር ዓማጽያንን የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የማስፈታቱን ሂደት አነቃቅተናል። »

ማስታወቂያ ሚንስትሩ ኦማላንጋ አክለው እንዳስረዱት፡ ዘመቻው የኤፍ ዲ ኤል አር ዓማጽያን በውዴታ ወይም በግዴታ ወደ ትውልድ ሀገራቸው የሚመለሱበትን፡ ይህን ካላደረጉ ግን በኮንጎ እንደ ስደተኛ ብቻ የሚኖሩበትን አማራጭ የያዘ ነው።

በግምት ሁለት ሺህ የርዋንዳ ወታደሮች ኮንጎ መግባታቸውን የተመ ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ በምህጻሩ ሞንዩክ እና ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል። የጦሩን መጠን በተመለከተ ኦማላንጋ ዘገባ ከመረጋገጥም ሆነ ከማስተባበል ተቆጥበዋል።

« የኛን ጦርም ሆነ የርዋንዳን የስለላ ጦር ቁጥር፡ ለነርዱ ደህንነት ዋስትና በማሰብ፡ ልናገር አልችልም፡ ልል የምችለው ጦራችን በኤፍ ዲ ኤል አር ን ለመታገል በቂ አቅም አለው። »

የርዋንዳና የኮንጎ ጦር ኃይላት በሰሜንና በደቡብ ኪቩ ስድስት ሺህ ተዋጊዎች ባሉት የሁቱ ዓማጽያን የጀመሩት የጥቃት ዘመቻ ከአስር እስከ አስራ አምስት ቀን እንደሚቆይም ኦማላንጋ አክለው ገልጸዋል። የተመድ ባወጣው ዘገባ መሰረት ርዋንዳ የኮንጎ ቱትሲዎችን፡ ኮንጎ ደግሞ የርዋንዳ ሁቱ ዓማጽያንን እንደምትረዳ ቢያመለክትም፡ ሁለቱ ሀገሮች ዘገባውን አስተባብለዋል።

የርዋንዳ ጦር አሁን በኮንጎ ጣልቃ የገባበት ድርጊት ግን በሀገሪቱ ስጋት መፍጠሩን ለኮንጎ ነጻነት የሚታገለው የኤም ኤል ሲ ቡድን ዋና ጸሀፊና ቃል አቀባይ ቶማስ ሉራካ አስታውቀዋል።

« ይህ የመንግስት ዕቅድ በመሰረቱ ጥሩ ነው። ባካባቢው ሰላም ለማስፈን ግን ዘዴው ጥሩ አይደለም። የርዋንዳ ጦር አሁን ኮንጎ ጣልቃ በገባበት ድርጊት ምን ያህል የኮንጎ ተወላጆች ችግር እንደሚደርስባቸው አይታወቅም። የውሉን ዝርዝር አናውቅም። ከመንግስታችን በኩል ግልጽነት ተጓድሎዋል። እንደሚታወቀው፡ የርዋንዳ ጦር ከ 1996 እስከ 2002 ድርስ ምስራቅ ኮንጎን ይዞ ነበር። እና በዚሁ ጊዜ የ ኤፍ ዲ ኤል አር ን ጉዳይ እልባት ለማስያዝ አልቻለም። »

የኮንጎ ብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ቪታል ካሜሬም ቢሆኑ የኮንጎ መንግስት ከርዋንዳ ጋር ስለደረሰው ስምምነት ማብራሪያ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

« የኛ መንግስት ከርዋንዳ መንግስት ጋር ግንኙነቱን እንደገና ለማደስ በውይይት ላይ እያለ አሁን የርዋንዳን ጦር መጋበዙ ትክክለኛ ርምጃ መሆኑ አጠያያቂ ነው። ይህ ጋሪውን ከፈረሱ በፊት እንደማስቀደም ይቆጠራል። እና ይህ ሁኔታ በኋላ ጸጸት ውስት ሊያስገባን ወደሚችል ሁኔታ ከመቀየሩ በፊት መንግስት ማብራሪያ ቢያቀርብበት መልካም ይመስለኛል። »

የምስራቅ ኮንጎ ሲቭል ማህበረሰቦች መሪ ኖርቤር ኩቢየም የርዋንዳ ጦር ወደ ኮንጎ መግባቱ ሁኔታዎችን ሊያባብስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። በምስራቅ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱት የሁቱ ዓማጽያን ግን ርዋንዳና ኮንጎ አሁን በአንጻራቸው የጀመሩትን ጥቃት በቡድኑ ዋና ጸሀፊ ካሊክስቴ አማካይነት በጥብቅ አውግዘታል።

« በኤፍ ዲ ኤል አር አንጻር የጥቃት ዘመቻ ማካሄዱ በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ይህ በዚያ ለሚኖረው ሲቭል ህዝብ መጥፎ መዘዝ ሊያስከትል ይእላልና፡፡ለዚህ ዓይነቱ መዘዝ ርዋንዳ ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርባታል። »

በአሁኑ ጊዜ ብዙ የውጭ ኃይላት ወደ ኮንጎ ተመልሰው በመግባት ላይ ናቸው። የዩጋንዳና የደቡብ ሱዳን ጦር ኃይላት ከዩጋንዳና ከደቡብ ሱዳን ሸሽተው ወደ ምስራቅ ኮንጎ የሸሹትንና በዦሴፍ ኮኒ የሚመሩትን የሎርድ ሬዚስተንሰ ዓማጽያንን ለማደን በዚያ እየተንቀሳቀሱ ያሉበት ሁኔታ የኮንጎን ህዝብ ሳያሳስበው አልቀረም።

የርዋንዳና የኮንጎ ጦር በሰሜን ኪቩ ጥቃት ከጀመሩ ወዲህ የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችና ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ወደዚያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። ይህም ርዳታ ለሚያስፈልገው ህዝብ ርዳታ የማቅረቡን ተግባር በማሰናከሉ የተመ ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ በምህጻሩ ሞንዩክ ቃል አቀባይ ዦን ፖል ዲትሪኽ ማስጠንቀቂያ ከማሰማት ወደ ኋላ አላሉም።

« የኮንጎ ወታደሮች ለተመ ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ በምህጻሩ ሞንዩክ እና ለቀይ መስቀል እና ለሌሎች ድርጅቶች ከጎማ በስተሰሜን ወዳለው ወደ ኪቩ የሚወስዱ ኬላዎችን እንዳይልፉ ከልክለዋል። እና ጥረታችን በዚሁ የጥቃት ዘመቻ ወደተጀመረበት አካባቢ ያሉ ተፈናቃዮችን መርዳት የምንችልበትን ፈቃድ ለማግኘት ነው። እስካሁን ዕገዳው አልተነሳም። ይህን አጥብቀን እንቃወማለን። በፍጹም ልንቀበለው የማንችለው አሰራር ነው። »

AT,HM

Quelle: RTR, DW