የርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ የቱርክ ጉብኝት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 02.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ የቱርክ ጉብኝት

በቱርክ የሶስት ቀናት ጉብኝትን ያደረጉት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በጉብኝታቸዉ ማጠቃለያ በተደረገዉ የመሰናበቻ ዝግጅት ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተለሜዎስ ጋር የሐዋርያዉን ቅዱስ አንድርያስ ዕለተ ሞት በልዩ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት አስበዋል።

ሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በሚገኘዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ -ክርስትያን የጸሎት ሥነ-ስርዓት ላይ በጋራ መገኘት ለቤተክርስትያኒትዋ አንድ አስፈላጊና ዋንኛ ሚናን መጫወታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። የዶቼ ቬለዉ ቶማስ ቦርማን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የቱርክን ጉብኝትን በተመለከተ የዘገበዉን በዕለቱ አዉሮጳና ጀርመን መሰናዶአችን ተካቶአል።ሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች ባለፈዉ እሁድ ኢስታንቡል ከተማ በሚገኘዉ በግሪክ የቅዱስ ጊዮርጊስ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን የሐዋርያዉን ቅዱስ አንድርያስ ዕለተ ሞት በማስታወስ በሚዘጋጀዉ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዉ ነበር። በአብዛኛዉ እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መኖርያ የሆነችዉ የቱርክዋ ኢስታንቡል ከተማ፤ የምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የብፁዕ ቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ ዋና መቀመጫ በመሆንዋም ትታወቃለች። አቡነ በርተሎሜዎስ በዓለም ዙርያ የሚገኙ የ300 ሚሊዮን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የበላይ አባትም ናቸዉ። ቱርክን ለሶስት ቀናት የጎበኙት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተለሜዎስ በጋራ ባደረጉት በዚህ የጸሎት ሥነ- ስርዓት ላይ በኦርቶዶክስ እና በካቶሊካዊት ቤተክርስትያን መካከል ያለዉን ልዩነት ማጥበብ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። በሥነ- ስርዓቱ ላይ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ እንዲህ ነበር ያሉት

« በመካከላችን ጭቅጭቅ፤ ክርክርና ፉክክር ካለ እንዴት ነዉ ታድያ ከክርስቶስ የመጣን የሰላም መልክት ለሌሎች መመስከር የምንችለዉ? ይህን የርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ንግግርን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስም ተቀብለዉታል። ሁለቱ አብያተ-ክርስትያናት በዚህ ክርክርና ጭቅጭቅ ዉስጥ ሳሉ ሌላዉ ዓለም በመኖር አለመኖር ስጋትና ስለ ነገ ምን መሆን ጭንቀት ላይ ይገኛሉ ያሉት አቡነ በርተሎሜዎስ በበኩላቸዉ፤ ዛሬ ማኅበረሰቡ በተለያየ የክርስትና ሃይማኖት ምክንያት በልዩነት በግጭትና በጠላትነት የተለያይቶ የሚገኝ ከሆነ ነገ ሰብዓዊነት እንዴት ይለመልማል እንዴት ከሞት ሊዳንስ ይችላል- ሲሉ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠይቀዋል። በጸሎት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ሁለቱም የአባያተ ክርስትያን ዋና መሪዎች ጦርነት ባለባቸዉ በሶርያና ኢራቅ በሚገኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚፈፀመዉን እንግልትና ወከባን አዉግዘዋል። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ቱርክን በጎበኙ በመጨረሻዉ ዕለት ማለትም ባሳለፍነዉ እሁድ ከሰዓት በኋላ ከሶርያና ከኢራቅ ጦርነት ሸሽተዉ በኢስታንቡል መጠግያ ያገኙ ስደተኞችን ጎብኝተዋል። ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ስደተኞቹ ያላቸዉን ተስፋና ሰላም እንዳያጡም አበረታተዋቸዋል። በሌላ በኩል ቱርክ፤ ከሶርያ እና ከኢራቅ የሸሹ ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞችን በመቀበልዋ በምሳሌነት የምትቀርብ ቸር ሀገር ሲሉ ለቱርክ ምስጋናን አቅርበዋል። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስና የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ክርስቲያኖች በአስጨናቂ ሁኔታ ላይ ሆነው ለሚያቀርቡት ጥሪ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚመጥን ምላሽ እንዲሰጣቸው ይሻሉ ሲሉም ተናግረዋል።

ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ሁሉም አብያተ ክርስትያናትና የተለያየ የክርስትና እምነት ተከታዮች ያላቸዉን ኃይል ሁሉ በማስተባበር ለዓለም ሰላም መጣር እንዳለባቸዉም አመልክተዋል። ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ይህን ቃል የተገባቡት ከምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ከብፁዕ ቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ ብቻ ሳይሆን በቱርክ ከአነጋግሩዋቸዉ የሙስሊም ሃይማኖት መሪዎች ጋርም ነዉ።
ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ኢስታንቡል ዉስጥ ሰማያዊ መስጊድ የተባለዉን ቦታ ሲጎበኙ በሙስሊሞች በኩል ከፍተኛ ቦታ እንደተሰጣቸዉ ነዉ የተመልከተዉ። መስጂዱን በጎበኙበት ግዜ በመስጂዱ ዋና የሃይማኖቱ ተጠሪ ጋር ባካሄዱት የጸሎት ሥነ- ስርዓት፤ ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ለእስልምና ያላቸዉን አክብሮት ማሳየታቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። በዚህም ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በሃይማኖቶች መካከል የመገናኛ ድልድይ በማበጀት በክርስትና እና በእስልምና መካከል ለሚደረግ ዉይይት ግልጽ መሆናቸዉን ማስመስከራቸዉ አሳይተዋል። በኢስታንቡል በሚገኘዉ በአንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን የመጡ አንዲት የኢስታምቡል ነዋሪ እንደተናገሩት በሃይማኖት ብንለያየም ሁላችንም አንድ አይነት ሰዎች ነን፤

« በተለያየ ሃይማኖት ይኑረን እንጂ ሁላችንም ብንሆን ወንድምና እህት ነን። እኔ በበኩሌ ሙስሊም ነኝ በሌላ በኩል የሺዓ ዘርፍ ሙስሊም ነኝ። ሆኖም ግን ዛሬ ወደዚህ የመጣሁት ሁለቱ ሃይማኖቶች ሲገኛኙ ማየት እጅግ ስለሚያጓጓኝ ነዉ። »


የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ርዕስ ፍራንሲስ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ሪቸብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በተወያዩበት ወቅት በዓለም ዙርያ የሚገኙ የሙስሊም የፖለቲካ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ምሁራን በእስልምና ስም የሚወሰድ የኃይል ርምጃ በግልፅ ቢያወግዙ ጥሩ ነበር ሲሉ መናገራቸዉ ተዘግቦአል። ሙስሊሞች ሁሉ አሸባሪዎች ናቸዉ የሚሉ ወገኖች ትክክል አይደሉም ሲሉ ፍራንሲስ አበክረዉ ወቅሰዋል። ክርስትያኖች ሁሉ አክራሪ ናቸዉ ብሎ መደምደምም እንደማይቻል ሁሉ ሙስሊሞች ሁሉ አሸባሪ ናቸዉ ማለት ፍፁም ስህተት መሆኑን የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ተናግረዋል። በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ተዛመተ የተባለዉን ክርስትያኖችን መጥላትና መፍራት ተገቢ ያልሆነ ርምጃ በማለት አዉግዘዋል። ከትናንት በስትያ እሁድ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በቱርክ የሶስት ቀናት ጉብኝትን አጠናቀዉ ወደ ቫቲካን ከማቅናታቸዉ በፊት ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተለሜዎስ ጋር በጋራ የሃዋርያዉን ቅዱስ አንድርያስ ዕለተ ሞት በልዩ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት ለማሰብ በተገኙበት ወቅት ስለዓብያተ-ክርስትያን እርቅና አንድነት ተነጋግረዉ ነበር።

« በመንፈስ ቅዱስ ከተመራን እና ከሰራን የዓይነት ብዛትና ልዩነት ፈፅሞ አያወዛግበንም። መንፈስ ቅዱስም ዓይነቱን በቤተክርስትያን ጉባዔ እንድናኖረዉ ይገፋፋናል»


የመገናኛ ብዙኃን በርዕስ አንቀፆቻቸዉ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ርዕስ ፍራንሲስ የቱርክ ጉብኝትን በአዎንታዊ ጎኑ ነዉ የተመለከቱት። በዚህም ፍራንሲስ በዚህ ጉብኝታቸዉ ከፍተኛ ፍቅርን ከማኅበረሰቡ መግዛታቸዉ ተነግሮላቸዋል። ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በጉብኝታቸዉ ወቅት ከአንዱ የጉብኝት ቀጠሮ ወደ ሌላዉ ሲዘዋወሩ ይጠቀሙበት የነበረዉ ተሽከርካሪ ቱርክ ዉስጥ የተሠራና የቱርክ መካከለኛ ማኅበረሰብ የሚጠቀምበት ተሽከርካሪን ስለነበር፤ በበርካታ የቱርክ ነዋሪዎች ዘንድ የሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ቁጥብነት እጅግ ግርምትን መፍጠሩም ተመልክቶአል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ከዓለም ዙርያ ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ለምታስተናግደዉ ለቱርኳ ኢስታንቡል ከተማ የተለመደ አልነበረም።

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ፅንፈኝነትን፤ አክራሪነትንና ጥላቻን ለማስወገድ በተለያዩ የሃይማኖቶት ተከታዮች መካካል ዉይይት ማድረግ እንደሚጠቅም አጥብቀዉ የመከሩት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ሙስሊሞች የሚበዙባትን ሃገር ቱርክን ሲጎበኙ የመጀመርያቸዉ እንደሆነ ተመልክቶአል።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic