የሬጌ ፍቅር | ባህል | DW | 08.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የሬጌ ፍቅር

የ28 አመቱ ጀርመናዊ ጁልያን ሒልት በሬጌ ሙዚቃ ፍቅር የተነደፈው ገና ልጅ እያለ ነበር። ኑሮውን በጃማይካ ካደረገ አንድ አመት ያለፈው ጁልያን በአነስተኛ ማሳ ላይ አትክልት ያመርታል። ካገሬው ሰው ተግባብቶ የሚኖረው ጁልያን የዓለም አተያዩ በሙዚቃ ተቀይሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:57

የሬጌ ፍቅር

ጃሚንግ ጁልያን ሒልት ልጅ እያለ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደመጠው የቦብ ማርሌ ዜማ ነው። ጃማይካዊው ቦብ ማርሌ እና ዘ-ዌይለርስ የሙዚቃ ቡድን በጎርጎሮሳዊው 1977 ዓ.ም. ኤክሶዶስ በተሰኘ አልበማቸው ውስጥ ያካተቱትን ጃሚንግ ጁልያን ለመጀመሪያ ጊዜ ያደመጠበትን ወቅት ባያስታውስም ይኸው ዛሬ ድረስ በፍቅር ወድቆለታል።

«የሰማሁበትን ጊዜ ባላስታውሰውም ልጅ ሆኜ እናቴ ስታደምጠው ትዝ ይለኛል። ዛሬም ሳደምጠው የሙዚቃ ንዝረቱ በሰውነቴ ይሰማኛል። የቦብ ራስታ ማርሌ እጅግ የምወደው የሬጌ ሙዚቃ ነው።»

በጃማይካውያን አብዮት፤ኹከት እና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የተወለደው ሬጌ ባህር ተሻግሮ ውጥንቅጡ ባልነበረባቸው አገሮች ዘንድም ተቀባይነትን ተወዳጅነትን አትርፏል። ጁልያን ሒልት የአስራ አንድ አመት ልጅ እያለ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን መቀመጫውን ያደረገው ሲድ የተሰኘ የሬጌ፣ሒፕሆፕ እና ዳንስሆል ባንድ ተሰሚ ነበር ። የቦብ ማርሌ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ዳሚያን ማርሌ የሙዚቃ ሥራዎች ጁልያን በሬጌ ፍቅር ጭልጥ እንዲል አድርገውታል።

«የሙዚቃ ምቱ፤ ቅላጼው እና የሙዚቃ ቅንብሩ በቀጥታ ለልቤ ይናገራል። ሙዚቃውን ለመረዳት ቋንቋውን ማወቅ አይጠበቅብህም።ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው። የሬጌ ሙዚቃ በሌሎች ሰዎች ላይ እንዳለው አይነት ተፅዕኖ በእኔም ላይ አለው። አንድ አይነት ቋንቋ እንረዳለን። የሬጌ ሙዚቃንም እናዳምጣለን።»

ሬጌ የለውጥ ፈላጊዎች የትግል ጥሪ ተደርጎ ይቆጠራል። የቦብ ማርሌ ሙዚቃዎች የእኩልነት እና ፍትኅ ፍለጋ ጥሪም ናቸው። ማርከስ ጋርቬይ፣ሊዎናርድ ሖዌል እና ሳም ብራውንን የመሰሉ የጃማይካ የለውጥ ፋኖዎች የሬጌ ሙዚቃን መልዕክታቸውን ለማድረስ ሕዝቡንም ለማስተባበር አግዟቸዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ግን ለ28 አመቱ ጀርመናዊ ጁልያን ሩቅ ናቸው።

«ሬጌ ስለ ፍቅርም የተቀነቀነ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። አዎ አንዳንድ ጊዜ መታገል ይኖርብሃል። ይህ የህይወት አንድ ክፍል ነው። ትግል እና ፍቅር የህይወት ገጽታዎች ናቸው። ሁሉም ሙዚቀኞችም ስለዚህ ያዜማሉ። በፍቅር ስለ መኖር እና ፍቅርን ስለማጣት፤ ስለክፉ እና ደግ ጊዜ-»

ጁልያን ሙዚቀኛ ሳይሆን የምግብ አብሳይ ነው። ተወልዶ ባደገበት የጀርመን ቦን ከተማ ያሉት ጥቂት የሬጌ ሙዚቃ አድናቂዎች ቢሆኑም ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር አላቸው። ጁልያን «ወዳጅነታችን እንደ ቤተሰብ ነው» ሲል ይናገራል። በሙዚቃ ብቻ ወደ ሚያውቃት ጃማይካ ለማቅናት ሲያሰላስል አስር አመታት ፈጅቶበታል። በስተመጨረሻ ወደ ካሪቢያን ደሴቷ አገር አመራ።

«ወደ ደሴቷ ስሄድ በፍቅር ወደኩ። በቀጥታ ወደ አንድ ሆቴል አመራሁና ስራ ብሰራላችሁ የተወሰነ ገንዘብ ትከፍሉኛላችሁ ስል ጠየኳቸው። እናም ስራ ጀመርኩ። ወደ ጃማይካ ስጓዝ ጠቅልዬ እዛው ለመኖር አስቤ አልነበረም። አሁን ምን አልባት ህይወቴን ሙሉ በዛው ለመኖር እያሰብኩ ነው። ከፈለኩ ላደርገው እችላለሁ።»

ጁልያን ተወልዶ ያደገባት ጀርመን ሰላም እና ጸጥታዋ የተጠበቀ አገር ናት። የተሻለ የትምህርት እና የሥራ እድልም ለዜጎቿ ታቀርባለች። የጁልያን አዲስ መኖሪያ ጃይማይካ በአንጻሩ የጸጥታ ችግር ይተዋልባታል። ኑሮም በጃማይካ ውድ ነው። ጁልያን በጃማይካ የፈለገውን ሁሉ እንዳገኘ ያምናል።


«ወደ ጃማይካ ስጓዝ ብዙ ነገር ነበር የጠበኩት። የጠበኩትንም አግኝቻለሁ። ስለ መጥፎ ነገሮች ፍርሐት ተሰምቶኝ የነበረ ቢሆንም ያን ያክል አስከፊ አይደለም። ጠንቃቃ እና አካባቢህን የምታስተውል ከሆንክ ጥሩ ግዜ ልታሳልፍ ትችላለህ። በጃማይካ ብዙ ወንጀል ይፈጸማል። ሊያጭበረብሩህ እና ገንዘብህን ሊወስዱ የሚሹ ሰዎች አሉ። ሰዎች እርስ በርስ ይገዳደላሉ። እንደ እኔ በገጠር ከኖርክ ደግሞ ይህን በደምብ ታስተውለዋለህ።»

ጁልያን በጃማይካ ሬጌን እያደመጠ ከአገሬው ሰው ጋር ተግባብቶ ገበሬ ሆኗል። ሽንኩርት፤ቲማቲም እና ለምለሙ የካሪቢያን አፈር የሚያበቅለውን ያመርታል። ግን መሬቱ ትንሽ እንደሆነች ነግሮኛል። በጀርመን አድርጎት የማያውቀውን ቁፋሮ እና ማረም የተማረው የአካባቢው ነዋሪዎች እየሳቁበት ነበር።

«በከተማ አንድ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ተከራይቼ የጀርመን ቴሌቭዥንን እያየሁ መዝናናት እችል ነበር። ለዚህ ደግሞ ወደ ጃማይካ መሔድ አይጠበቅብኝም። እኔ አገር ጎብኚ አይደለሁም። እናም በጠዋት ተነስቼ ቆንጨራዬን ይዤ ወደ ጫካ በመሄድ የእርሻ ሥራዬን አሰራለሁ። ይህን ህይወት እወደዋለሁ። እውነተኛ ህይወት ነው። ወደ ተፈጥሮ መመለስ ነው። በዝናብ በፀሃይ ላይ ጥገኛ ነኝ። ይኼኔ ወደ ተፈጥሮ እጅግ እንደቀረብኩ ይሰማኛል። እና እዚህ ካለው ህይወት የበለጠ እውነተኛ እንደሆነ ይሰማኛል።»
ጃማይካ ሲነሳ ሬጌ ከሬጌ ጋር ደግሞ የራስ ተፈሪያን እምነት እና ጋንጃ አብረው ይነሳሉ። ከዓመታት በፊት ለማህበራዊ ለውጥ እንቅስቃሴ አካል ሆኖ የተጀመረው የራስ ተፈሪያን እምነት ከኢትዮጵያ በተለይም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው። ጁልያን የእምነቱ ተከታይ አይደለም። ጠጉሩንም አልተጎነጎነም። ለእርሱ ቀዳሚው ነገር «መልካም ነገር ማድረግ» እንደሆነ አጫውቶኛል። ሬጌ ሲነሳ ማሪዋና፤ፖት፤ዊድ እና ሜሪ ጄን በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ካናቢስ እብሮ ይታወሳል። ቅጠሉ፤አባና ግንዱ እየተጠቀለለ የሚጨሰው ካናቢስ ጃማይካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በህግ ገደብ የተጣለበት ቢሆንም የዛኑ ያክል በርካቶች ይጠቀሙታል። በብዙ አገራት በአደንዛዥ እጽነት ተፈርጆ በህግ በተከለከለው የካናቢስ ቅጠል ላይ የተለየ አቋም አለው።

«የህክምና ዶክተሮች እና ሆስፒታሎች እንዳሉ ሁሉ ባህላዊ ሐኪምም አለ። በደሴቷ ላይ ስለሚበቅሉ እጽዋት ጠንቅቆ ያውቃል። በአንድ ሰው ላይ ያሉ ችግሮችን ሁሉ ያድናል። የተቆረጠ እጅ መልሶ መቀጠል አይችልም። ነገር ግን የራስ ምታት፤የጀርባ ህመም የሚሆኑ እጽዋት ያውቃል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ጋንጃ ነው። እጹ እንደ መድሐኒት ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ግልጋሎትም ይውላል።»

የህክምና ባለሙያዎች ማሪዋና ተብሎ የሚታወቀው የካናቢስ ቅጠል በተጠቃሚዎቹ ላይ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ጉዳት እንደሚያስከትል ይገልጣሉ። እይታን መቀየር፤የጊዜ ዑደትን ማዛባት የሰውነት እንቅስቃሴን ማስተጓጎል ለማሰብ እና ችግሮችን ለመፍታት መቸገር እና የማስታወስ ችሎታን ማዛባት በተጠቃሚዎቹ ላይ በአጭር ጊዜ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ተብለው ተዘርዝረዋል። በረጅም ጊዜ ደግሞ የአዕምሮ እድገት እንደሚያስተጓጉል የህክምና ባለሙያዎች የሰሯቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ጁልያን ከዚህ ቀደም በተጓዘባቸው ካናዳና እስራኤልን በመሰሉ አገሮች የአገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሯቸውን ቦታዎች በመተው የአገራቱ ነዋሪዎች የለት ተለት ህይወትን ለመኖር እንደሞከረ አጫውቶኛል። ከአንድ ሳምንት በኋላ የሬጌ ሙዚቃን እያደመጠ ለእረፍት ከመጣባት የትውልድ አገሩ ጀርመን ወደ ጃማይካ የሚያቀናው ጁልያን አንድ ቀን ወደ ኢትዮጵያ መጓዝም ይፈልጋል።


እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic