የራድኮ ምላዲች የክስ ሒደት | ዓለም | DW | 03.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የራድኮ ምላዲች የክስ ሒደት

«እኔ ጄኔራል ራድኮ ምላዲች ነኝ። የክሱ ጭብጥ አንድም ቃል እንዲነበብልኝ አልፈልግም።»

default

ምላዲች ዛሬ

03 06 11 የቀድሞዉ የቦስኒያ ሠርብ ጦር አዛዥ ጄኔራል ራድኮ ምላዲች የተመሠረተባቸዉን የዘር ማጥፋት ክስ መስማት አልፈልግም አሉ።ዛሬ ዘሔግ-ኔዘርላንድስ ካስቻለዉ አለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ችሎት ፊት የቀረቡት ሚላዲች እንደሚሉት የተያዘባቸዉን የወንጀል ጭብጥ ለመስማት ጤናቸዉ አይፈቅድም።ጡረተኛዉ ጄኔራል በቦስኒያዉ ጦርነት ወቅት ስምንት ሺሕ ያሕል ሰላማዊ ሰዎችን በማስገደል፥ ሌሎች በሺሕ የሚቆጠሩትን በማሰቃየት፥ በማስደፈርና በማገት ወንጀል ተከሰዉ ለአስራ-ስድስት አመታት ሲታደኑ ነበር።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ። «እኔ ጄኔራል ራድኮ ምላዲች ነኝ። የክሱ ጭብጥ አንድም ቃል እንዲነበብልኝ አልፈልግም።» በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት በቀድሞዋ ይጎዝላቪያ የተፈፀመዉን የጦር ወንጀል የሚመረምረዉ ችሎት ግን የተከሳሹን ጥያቄ አልተቀበለዉም።የመሐል ዳኛ አልፎንስ ኦሬ ክሱን ያነቡ ገቡ። «በክሱ መሠረት እርሶዎ፥ ራድኮ ሚላዲች፥ በዘር ማጥፋት፥በሰዉ ልጅ ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና የጦር ሕግና ደንብን በጋራ ወንጀል መፈፀመን ጨምሮ፥ በተለያየ ሁኔታ በመጣስ ወንጀል ተከሰዋል።»
NO FLASH Ratko Mladic Festnahme

ምላዲች 1985

ዳኛ ኦሬ የክሱን ጭብጥ ሲዘረዝሩ የቀድሞዉ አስፈሪ ጄኔራል የጆሮ ማድመጫ ቀበቶ እሁለት የገመሰዉ የሚመስለዉን ትልቅ፥ መላጣ ጭንቅላታቸዉን ግራ-ቀኝ እያወዛወዙ የሚባለዉን ሁሉ ይቃወሙ ነበር።ዕምነት ክሕደታቸዉ ተጠየቁ። «ሥለ ጤንነቴ ሁኔታ በዝግ ችሎት ማስረዳት እፈልጋለሁ።» ፍርድ ቤቱ፥ ተከሳሹ የክሱን ጭብጥ በሰላሳ ቀናት ዉስጥ አጥንተዉ መልስ እንዲሰጡ ቀጥሮ አበቃ።ሰዉዬዉም ወደ ማረፊያ ቤት ተላኩ።አስራ-አምስት ኳድራት ሜትር የሚሰፋዉ ማረፊያቸዉ ብዙዎቹ የሴሬብሬንትሳ ነዋሪዎች «ቤት» ከሚሉት ብዙ ይሻላል።የተሟላ መፀዳጃ፥ ባኞ ቤት አለዉ።ያሻቸዉን ጣቢያ የሚመለከቱበት ቴሌቪዥ ተገጥሞለታል። መስኮቱን ከፈት አድርገዉ ከባሕር የሚነሳዉን ንፁሕ አየር መማግ ነዉ።ሰዉነታቸዉን ማፍታት ቢፈልጉ ከክፍላቸዉ ጎን ካለዉ ሌላ ክፍል ጂምናስቲክ መስራት፥ የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወት ይችላሉ።ከስፖርት ክፍሉ ጎን ደግሞ እንግዳ መቀበያ ክፍል አላቸዉ።እዚያ ሲፈልጉ እጎናቸዉ ከታሰሩት ከጓደኛቸዉና ከቀድሞዉ የቦስኒያ ሰርቦች መሪ ከራዶቫን ካራዲች ጋር የድሮዉን እያነሱ ማዉጋት ይችላሉ።ሲያሰኛቸዉ ደግሞ ጠያቂ ዘመድ ወዳጆቻቸዉን ያስተናግዱበታል። ራድኮ ምላዲች እንደ ጦር ጄኔራል ባዘዙት የቦስኒያ ሔርሶ ጎቪናዉ ጦርነት የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ዘመድ ወዳጆች፥ የተገረፉ፥የተሰቃዩ፥ የተደፈሩት፥ ገሚሶቹ አሁንም መጠለያ ጣቢያ ናቸዉ።ሌሎቹ ስደት።የተቀሩት አንድም መንግሥት በሰጣቸዉ አሮጌ መኖሪያ፥ አለያም ዘመድ ተጠግተዉ «ኑሮ» ይሉታል።እና ብዙዎቹ «እስር ቤት» የሚባለዉን የምላዲችን ማረፊያ የመሰለ ቤትን በተሌቪዥን ነዉ-የሚያዉቁት። ጄኔራል ምላዲች የተከሰሱበት ወንጀል ብዙ ነዉ።ሴሬብሬንትሳ በተባለችዉ ከተማና አካባቢዋ ብቻ ስምንት ሺሕ ሰላማዊ ሰዎችን አስጨፍጭፈዋል፥ሳርዬቮን ለአርባ ሰወስት ሳምንታት አስከብበዉ የከተማይቱን ነዋሪ በምግብ፥ ዉሐ፥ ሕክምና እጦት አሰቃይተዋል።ልጃገረዶችን ከወላጆቻቸዉ፥ ሴቶችን ከቤሎቻቸዉ እያስነጠሉ አስደፍረዋል-የሚለዉ ይገኝበታል። አስራ-ስድት አመት ሲታደኑ ቆይተዉ ባለፈዉ ሳምንት መያዛቸዉ፥ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸዉም ከስሬብሬንሲሳ እልቂት የተረፉት ሴአድ ቤክሪች እንደሚሉት አለም ለፍትሕ መቆሙን ጠቋሚ ነዉ።ግፍ ለተዋለባቸዉ ግን ልባቸዉን አይጠግም።«እኛ ያለፍንበትን ግፍ የቀመሰ እና ዘመድ-ወዳጁን ያን በመሰለ አሰቃቂ ወንጀል ያጣ ሐዘኑ ፍፃሜ አያገኝም።አለም ተጠያቂዎቹን መከታተሉን ማወቅ ጥሩ ነዉ።ግፍ ለተዋለባቸዉ ግን የሚያበቃ ነገር የለም።»

Jahrestag Srebrenica 2010

የአፅም ቀብር-ስሬብሬኒሳ

የምላዲች ጦር እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1995 በተለይ ሴሬብሬንሳ ላይ ወጣትና ጎልማሳ ወንዶችን እየመረጠ ሲረሽን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዕዝ የዘመተዉ የኔዘርላንድስ ጦር በቅርብ ርቀት ይመለከት ነበር። ነጋሽ መሐመድ ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic