የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት | ዓለም | DW | 22.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት

ቦምብ፤ሚሳዬል፤ አረር፤ ጥይቱን ያፈናዳ-የተኩሰዉ ወገን ማንነት ለነሱ ከቁብ የሚገባ አይደለም።ሰዉ ነዉ ቁም ነገራቸዉ።ሕይወት ማዳን ነዉ-ዓላማቸዉ። በየእሳት፤ጢስ፤ጠለስ፤ ዉድመቱ መሐል ዘለዉ ይገባሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት

የዘንድሮዉ የራይት ላይቭሊሁድ ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚዎች ዛሬ ስዊድን ዉስጥ በይፋ ታዉቋል።ተለዋጭ ኖቤል ተብሎ የሚጠራዉን ሽልማት ዘንድሮ ያገኙት የሶሪያ፤የግብፅ እና የሩሲያ የርዳታ ተቋማት፤ የመብት ተሟጋቾችና ጁምሁሪየት የተባለዉ የቱርክ ጋዜጣ ነዉ።ሽላሚዉ ድርጅት በየዓመቱ እንደሚያደርገዉ ሁሉ የሚሰጠዉን ሁለት መቶ ሺሕ ዩሮ አራቱ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ይጋሩታል። ከጦርነቱ በፊት ዳቦ ጋጋሪ፤ አስተማሪ፤ ልብስ ሰፊ ወይም እንደ አብዛኛዉ ሶሪያዊ በሌላ አነስተኛ ሙያ የሚተዳደሩ ነበሩ።ዛሬ ከተማ-ሐገራቸዉ በጦርነት ሲወድሙ ዜጋቸዉን ሕይወት ለማዳን በአደጋኛዉ ዉጊያ መሐል የሚራወጡ ነብስ አድን ሰራተኞች ናቸዉ።ሶስት ሺሕ ይገመታሉ።ነጭ ቆብ ያጠልቃሉ።መለዮቸዉ-የወል ስማቸዉም ነዉ።

ቦምብ፤ሚሳዬል፤ አረር፤ ጥይቱን ያፈናዳ-የተኩሰዉ ወገን ማንነት ለነሱ ከቁብ የሚገባ አይደለም።ሰዉ ነዉ ቁም ነገራቸዉ።ሕይወት ማዳን ነዉ-ዓላማቸዉ።እንዲያ ሆኖ በየእሳት፤ጢስ፤ጠለስ፤ ዉድመቱ መሐል ዘለዉ ይገባሉ።ሰዎችን ያወጣሉ።ጤነኞቹን ያሸሻሉ።ለቆሰሉት የመጀመሪያ ርዳታ ይሰጣሉ።ወደ ሆስፒታል ይወስዳሉ።የሞቱትን ይከፍናሉ።

«(መራጩ) ችሎት ባለነጭ መለዮ የሚባሉትን የሶሪያ የሲቢል ተከላካዮች፤ ሰላማዊ ሰዎችን ከጦርነቱ ጥፋት ለማዳን ላሳዩት ታላቅ ሰብአዊነት፤ፅናት፤ቁርጠኝነትና ፍቅር (ለሽልማቱ) መርጧቸዋል።»

ይላሉ የራይት ላይቭሊሆድ የበላይ ሐላፊ ኦለ ፎን የክስኩል።ሁለተኛዋ ተሸላሚ ግብፃዊት ናቸዉ።የሴቶች መብት ተሟጋች ሞዝን ሐሰን።ነዝራ የተሰኘዉ የሞዝን ድርጅት በግብፅ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትን፤በደልና መገለልን ይታገላል።እንደገና ፎን የክስኩል።

«ጥቃት፤እንግልትና በደል የሚደርስባቸዉን ሴቶች ለመከላከል፤ኑራቸዉን ለማሻሻልና መብታቸዉን ለማስከበር ላደረጉት አስተዋፅኦ---»

ተሸለሙ።ሞዝና ድርጅታቸዉ።ሥራቸዉ ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል።በቅርቡ ቤይሩት-ሊባኖስ በሚደረግ ስብሰባ ለመካፈል አስበዉ ነበር።ካገር እንዳይወጡ ታገዱ።ከዉጪ ገንዘብ ሥለሚጊያኙም ለሐገሪቱ ደሕንነት አስጊ የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሰወስተኛዋ ተሸላሚም እንደ ሞዝን ሴት፤ የመብት ተሟጋች፤ ተወቃሽ፤ ተከሳሽም ናቸዉ።ስዌትላና ጋኑሽኪና።ሩሲያዊት ናቸዉ።የዜጎች ርዳታ የተሰኘ ድርጅት አላቸዉ።

ድርጅቱ ሩሲያ ዉስጥ ባሉት ሐምሳ ቤሮዎቹ አማካይነት ታቸዉ በስደተኞና በአናሳ ጎሳ አባላት ላይ የሚደርስ በደልን ይከላከላል።ከሐገር እንዳይባረሩ ይሟገታል።ይረዳል።ያማክራል።

ከሐገር እንዳይባረሩ ይሟገታል።«ሩሲያ ዉስጥ አንድ ስደተኛን ለመጠረዝ በአማካይ ሰወስት ደቂቃ በቂ ነዉ።» አሉ በቅርቡ።የሚጠረዙትን ሲያስጥሉ እሳቸዉ ተከሰሱ።ወንጀላቸዉ ከዉጪ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸዉ ነዉ።«የዉጪ ሰላይ» አላቸዉ መንግሥታቸዉ።

ጁምሁርየት የተሰኘዉ የቱርክ ጋዜጣ ባልደረቦች ዕጣ ፈንታም የተለየ አይደለም።ጋዜጠኞቹ ቅድመ ምርመራንና የመንግሥትን ጫናን ተቋቁመዉ፤ ጭቆናን፤ ሙስናን እና የፍትሕ መጣስን በድፈርት በማጋለጣቸዉ በየጊዜዉ ተወንጅለዋል።የግድያ ዛቻና ማስፈራሪያም ደርሶባቸዋል።

«የጁሙሕሪየት ጋዜጠኞች ጭቆናና ቅድመ ምርመራን፤እስራትና የግድያ ዛቻን ተጋፍጠዉ ሳይፈሩ በምርመራ ጋዜጠኝኘት

በደሎችን በማጋለጣቸዉ ለፕሬስ ነፃነት ላደረጉት አስተዋፅኦ ሸልመናቸዋል።»

ተሸላሚዎቹ የየድርሳቸዉን በመጪዉ ታሕሳስ ይረከባሉ።ሸላሚዉ ድርጅት አራቱን ተቋማት ወይም ሰዎች ለሽልማት የመረጠዉ ከሐምሳ ሐገራት ከተጠቆሙ 125 ዕጩዎች መሐል ነዉ።ለሽልማት የሚጠቆሙ ሰዎችና ተቋማት ከዓመት ዐመት እየበዙ መምጣት ፎን የክስኩል እንደሚሉት ለሸላሚዉ ድርጅት ድስታም፤ የዚያኑ ያክል የሥራ ጫና፤ አንዱን ከሌላዉ ለማበላለጥ ፈተናም ነዉ።

ሄለ የፕሰን/ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic