የራብ-ልምና ዑደት | ኢትዮጵያ | DW | 25.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የራብ-ልምና ዑደት

ኢትዮጵያን የረሐብና የረሐብቶች አብነት ላደረገዉ የረሐብ ዑደት፥ ኬንያን ከኢትዮጵያ ተርታ ላሠለፈዉ ረሐብ ፖለቲካዊዉ ምክንያት ዛሬም እንደ ረሐቡ ዑደት ከጉጭ አልፋነት ንግግር አለማለፉ ነዉ ሌላዉ ድቀት።

default

ሶማሊያ

25 07 11

እንደገና ድርቅ፥ እንደገና ረሐብ፥ እንደገና ዋይታ።የጠኔ-ጩኸት፥አዝጋሚሞት።የራብ-ልምና ዑደት።ምሥራቅ አፍሪቃ።የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።«ሐገራችን ከብቶች ነበሩን።መሬት-እርሻም ነበረን።ከብቶቻችን በሙሉ ግመሎቻችን፥ ላሞቻችን፥ ፍየሎቻችን ሁሉም አለቁብን።መሬቱም ደረቀ።ከገበያ ምንም ነገር መግዛት አልቻልንም።(ገንዘብ ላለዉም) ዋጋዉ የሚቻል አይደለም።»

ይላሉ ፋጡማ።እሳቸዉና ልጆቻቸዉም ደረቁ።ግን ከሚሊዮን ብጤዎቻቸዉ ብዙ ይሻላሉ።ተራቡ ተሰደዱ እንጂ አልሞቱም።ደግሞም ዳዳዓብ-ኬንያ መጠለያ ጣቢያ ደርሰዋል።ያዉ ለልመና።ሶማሊያን፥ ኢትዮጵያን፥ ኬንያን፥ ጀቡቲና ዩጋንዳን የመታዉ ድርቅ ከአስራ-አንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አስርቧል።

የሶማሊያዉ የከፋ ነዉ።የረሐቡ ጥናት ምሳሌዋ ግን ፀረ-ረሐብ ንቅናቄ የተሰኘዉ የጀርመን ግብረ-ሠናይ ድርጅት ባልደረባ የንስ ኦፐርማን እንደሚሉት ኢትዮጵያ ናት።

«ድርቁ ያስከተለዉ ሰብአዊ ድቀት እኛ እንዳየነዉ እጅግ ከፍተኛ ነዉ።በንፅፅር ሲያታይ አሁን የደረሰዉ ድቀት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካየነዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ።ሁኔታዉ እንደ ሰብአዊ ድርጅት ለኛና ለሰራተኞቻችንም ሲበዛ ከባድ ነዉ።እዉነቱን መናገር አለብኝ።ሕዝቡ የሚያየዉን ፍዳ ማመን ያስቸግራል።ፍፁም ሊቋቋመዉ ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል።»

ኦፐርማን እና ባልደረቦቻቸዉ እርዳታ ለመሥጠት የሚፍገመገሙበት የዳዳዓብ የስደተኞች ሠፈር ከዓለም ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነዉ።እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሶማሊያዉ ጦርነት እና የምሥራቅ ኢትዮጵያዉ ግጭት ያሰደደዉ ከሰወስት መቶ ሰማንያ ሺሕ በላይ ሕዝብ ታጭቆበታል። በቅርቡ ደግሞ ለረሐብ የተጋለጠዉ የደቡባዊ ሶማሊያ፥የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የራስዋ የሰሜናዊ ኬንያ ሕዝብ እየሠፈረበት ነዉ።

Superteaser NO FLASH Hunger in Dadaab Kind

ኬንያ

በየመንገዱ ረሐብ የሚጥለዉን ደካማ ለሞት ጥለዉ ከየአቅጣጫዉ ወደዚያ መጣሊያ ጣቢያ በየዕለቱ ሁለት ሺሕ ሰዎች ይጎርፉበታል።መንገድ ላይ የሚሞተዉን የቆጠረዉ የለም።መጠለያ ጣቢያዉም መቀበሪያቸዉ የሚሆንባቸዉ ብዙ ናቸዉ።በተለይ ሕፃናቱ።የመጠለያ ጣቢያዉ ሐኪም አሊሰን ኦማን እንደሚሉት መጠለያ ጣቢያ ከደረሱ በሕዋላ የሚመቱት ሰዎች በተለይ የሕፃናቱ ቁጥር በፊት ከነበረዉ ብዙ እጥፍ ጨምሯል።
«እንዳለ መታደል ሆኖ ሕፃናት እየሞቱ ነዉ።አብዛኞቹ የሚሞቱት እዚሕ በደረሱ በመጀመሪያዉ ሃያ-አራት ሠዓታት ዉስጥ ነዉ።ከቤታቸዉ ለመሰደድ ከመወሰናቸዉ በፊት ብዙ እንደሚያቅማሙ እናዉቃለን።ከወሰኑ በሕዋላ ደግሞ ከሁለት እስከ ሰወስት ሳምንት በእግራቸዉ ይጓዛሉ።እና ሕፃናቱ እዚሕ የሚደርሱት እንደምታይዋቸዉ በጣም ደክመዉ ነዉ።የሟቾቹ ቁጥር በፊት ከነበርንበት በስድስት እጥፍ አሻቅቧል።»

ከኬንያ ሰሜናዊ ድንበር ማዶ፥ ከደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ጠረፍ ባሻገር ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ጠረፍም ረሐብ ያቆራመደዉ ሰዉ የሰቆቃ ጩሐት ይሰማል።አፅም አስከሬን ይቆጠራል።ፋጢማ ከደቡብ ሶማሊያ ልጆቿን አንጠልጥላ ወደ ምዕራብ-ስትጓዝ፥ ደሐቤ እና ባለቤቷ ኢብራሒም ዘጠኝ ልጆቻቸዉን አስከትለዉ ወደ ሰሜን አቀኑ።መድረሻ ዶሎ ኦዶ-ኮቤ መጠለያ ጣቢያ።ከቤታቸዉ በወጡ በስድስተኛዉ ቀን ካሰቡን ደረሱ።

«የቀረን ነገር ልጆቻችን ብቻ ናቸዉ» አለች ደሔቤ።እርሻችን ደረቀ።ከብቶቻችን አለቁ።»ደሐቤ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ ያሰበችዉ ከምትጦራቸዉ እናትዋ እና ከምትረዳት እሕቷ ጋር ነበር።«ግን---» ያነጋገራት ጋዜጠኛ እንደ እንደሚለዉ አልቀጠለችም፥ ከጥልቅ ጉርጓዳቸዉ ጭል-ጭል የሚሉት አይኖቿ ደክመዋል።እንባ ማፍልቀ ግን አላቃታቸዉም።«ግን» የገጠጠ ጉንጮችዋን እየገመሠ የሚወርደዉን እንባ ጅማት ብቻ በቀራቸዉ እጆችዋ እያበሰች ቀጠለች።«ሁለቱም ሞቱ።»

ፋጢማ፥ ደሐቤ እና ብጤዎቻቸዉ በየቀያቸዉ አስከሬን ጥለዉ፥ በየመንገዳቸዉ አስከሬን ተዘናግረዉ ከየመጠላያ ጣቢያዉ ደርሰዋል።«አሁን የምንታገለዉ ለእነሱ ነዉ» አለች ደሐቤ ወደ ልጆችዋ እያመለከተች።ዶሎ ኦዶ የሚገኙት ሰወስት መጠለያ ጣቢያዎች ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ የሶማሊያ ስደተኛ እና እዚያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሐብ የተጋለጡ ሰዎች ሠፍረዉበታል።ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተሰኘዉ ግብረ ሠናድ ድርጅት እንደሚለዉ መጠለያ ጣቢያ ከደረሱት መሐል በየቀኑ ባማካይ ሁለት ሕፃናት ይሞታሉ።

ባለፈዉ ሳምንት ዶሎ ኦዶን ጨምሮ ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን የጎበኙት የዓለም ምግብ ድርጅት የበላይ ጆሲተ ሺራን በበኩላቸዉ ረሐቡ የጠናዉ በሶማሊያ ዉስጥ ወይም መጠለያ ጣቢያ በገቡት ሰዎች ላይ ብቻ አይደለም።
«በኢትዮጵያ ያለዉ ሁኔታ በተለይ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ በርካታ አካባቢዎች በድርቅ ክፉኛ መመታቱን እናዉቃለን።በተለይ ከብት አርቢዎቹ አስከፊ ችግር ዉስጥ ናቸዉ።ችግሩ የቆየ ነዉ።ባለፉት ጥቂት አመታት ከብቶቻቸዉ ሞተዉባቸዋል።ባለፉት ስምንት ወራት ዉስጥ ደግሞ ያላቸዉን ነገር በሙሉ አጥተዋል።በተለይ በከብት አርቢዎቹ የደረሰዉ ጉዳት በጣም አሳሳቢ ነዉ።»

«በጣም አሳሳቢ» ።ግን ዓለምና የአካባቢዉ መንግሥታት ሥለ ረሐብተኛዉና ረሐብተኞቻቸዉ በጣም ለማሰብ ዓመታት፥ ይሕ ቢቀር ስምንት ወራት ዘግይተዋል።ወይም ሕዝብ እንዳይራብ ለመርዳታ አልፈለጉም። ወይም በቅጡ ያልተቀበረ አስከሬን፥ የገጠጠ-ፊት፥የሚቆጠር አጥንት ጅማት የየቴሌቪዥኑን መስኮት እስኪሞላ ድረስ የረሐቡን ጥናት ከቁብ አልቆጠሩትም።

እርግጥ ነዉ ተለያዩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ችግሩ እንዲሕ ጠንክሮ ሕይወት ማጥፋት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ለጋሾች የተለመደ የእርዳታ እጃቸዉን እንዲዘረጉ ተማፅ ነዉ ነበር።ለጋሹ ዓለም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አንድም ተሰላችቷል፥ አለያም በግሪክ የምጣኔ ሐብት ቀዉስ፥ በአፍቃኒስታንና በሊቢያ ጦርነት ተወጥሯል።ብቻ ኬንያም ሆነ ኢትዮጵያ በሚገኙት ስደተኛ ጣቢያዎች የሠፈረዉ ሕዝብ ከሞቱት ወይም እዚያ መድረስ ካቃታቸዉ ጋር ሲነፃፀር እድለኛ ነዉ።

ቢያንስ እርዳታ አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለዉ።እስካሁን በቂ እርዳታ ያገኙት ግን ጥቂቶች ናቸዉ።አብዱል መሐመድ በቅርቡ ዳደዓብ ስደተኞች ጣቢያ መድረስ ከቻሉት አራት-መቶ ሺሕ ያሕል ስደተኞች አንዱ ናቸዉ።ሽማግሌ ናቸዉ።ታድለዋል።ግን፥-«ከሐገሬ ያሰደደኝ ረሐብ ነዉ።ርዳታ እየጠበቅሁ ነዉ።እስካሁን ግን ማንም ማደሪያ አልሰጠኝም።የማድረዉ ዉጪ ነዉ።»

የረሐብተኛዉ በተለይ የሶማሊያ ችግረኞች ሰወስተኛ የመሰደጂያ አቅጣጫ ሞቃዲሾ ናት።ባንድ በኩል የአ-ሸባብ ዉጊያ፥ በሌላ በኩል የሶማሊያ ጎረቤቶችና የሐያሉ ዓለም ጫና ግራ ቀኝ አቃርጦ ሾባ ያደረገዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወደ ርዕሠ-ከተማይቱ የሚጎርፈዉ ስደተኛ ድንኳን ተክሎ ከመቀበል ባለፍ የሚያደርገዉ፥ ሊያደርገዉ የሚችለዉም የለም።ይሕን ሞክሯል።ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲ ኑር እንደነገረን ሞቃዲሾ መዳረሻ ለፈሰሰዉ ሕዝብ እስካለፈዉ አርብ ድረስ ከዉጪ የደረሰለት የኩዌት እርዳታ ብቻ ነዉ።

«ሰሞኑን ሠፈራ ጣቢያ ከደረሱት መካካል ቢያንስ ዘጠኝ ልጆች በረሐብ መሞታቸዉን ባለሥልጣናቱ ነግረዉናል።ሠብአዊ ርዳታ በጣም ባጣዳፊ ካልደረሳቸዉ በሕይወት ያሉትም ይሞታሉ ብለዉ ይሰጋሉ።የኩዌት መንግሥት የሰጠዉን እርዳታ የጫኑ ሁለት አዉሮፕላኖች ዛሬ ሞቃዲሾ አዉሮፕላን ጣቢያ ማረፋቸዉን ሰምቻለሁ።የኩዌት መንግሥት እርዳታ መላኩን አረጋግጪያለሁ።ከዚሕ ዉጪ ግን እስካሁን ድረስ ለተራበዉ ሕዝብ የደረሰ ሠብአዊ ርዳታ የለም።»

ለጋሽ ሐገራት ገና የሚሠጡትን ርዳታ ለመወሰን ዛሬ ሮም ሲመክሩ ነዉ የዋሉት።መክረዉ-ዘክረዉ ወስነዉ፥ እርዳታዉ ለተረጂዉ እስኪደርስ የሚሞተዉን ሕዝብ ቁጥር ማስላት አሁን አይችልም። እርዳታዉ ቢገኝ እንኳን እንደ ሞቃዲሾ፥ ኬንያ ወይም ኢትዮጵያ ከሚገኘዉ ስደተኛ ዉጪ ለሚገኘዉ ረሐብተኛ በተለይ አሸባብ በሚቆጣጠረዉ አካባቢ ላለዉ ሕዝብ ርዳታ የሚደርስበትም መንገድ ላሁኑ ግልፅ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፥ አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ወደ ሚቆጣጠራት ወደ ባይደዋ ባለፈዉ ሳምንት በአዉሮፕላን የላከዉ ምግብና መድሐኒት በሠላም መድረሱ ተዘግቧል።የድርቅ-ረሐቡ ሥጋት እንደተሰማ አ-ሸባብ በዉጪ የእርዳታ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረዉን ማዕቀብ ማንሳቱ እርዳታዉ ከተገኘ ተረጂዉ ወዳለበት ማድረሱ አይገድም የሚል ተስፋ አጭሮ ነበር።

ዩኒሴፍ የላከዉን እርዳታ የጫኑት አዉሮፕላኖች ጭነታቸዉ ባይደዋ አራግፈዉ በሰላም የመመለሳቸዉ ዜና ደግሞ ለተረጂዎቹ ደስታ፥ ለርዳታ አቀባዮቹም መልካም ዜና ነበር።ሐሙስ ግን አሸባብ በፊት የገባዉን ቃል አጠፈ።እንደገና ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር።

NO FLASH Hunger und Dürre in Äthiopien

ኢትዮጵያ

«የአሸባብ ቃል አቀባይ ካንድ ሳምንቱ በፊት በሰጡት መግለጫ ማንኛዉም የርዳታ ድርጅት ቡድኑ በሚቆጣጠረዉ አካባቢ ለሚገኘዉ ችግረኛ እርዳታ መስጠት እንደሚችሉ አስታዉቀዉ ነበር።ትናንት ጠሩት ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ ግን ባለፈዉ ሳምንት ያሉትን አጥፈዉ አሸባብ በሚቆጣጠረዉ አካባቢ እንዳይንቀሳቀሱ ከዚሕ ቀደም በከለከላቸዉ የእርዳታ ድርጅቶች ላይ የጣለዉን ዕገዳ እንዳላነሳ አስታዉቀዋል።ማዕቀቡ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት፥ የአለም የልማት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የርዳታ ድርጅቶችን የሚያጠቃልል ነዉ።»

ባለፈዉ አርብ መቃዲሾን የጎበኙት የአለም ምግብ ድርጅት የበላይ ወይዘሮ ጆሲተ ሺረን አ-ሸባብ በድርጅታቸዉ ላይ የጣለዉ ማዕቀብ ለተራበዉ ሕዝብ ርዳታ ለማቅረብ የሚደረገዉን ጥረት እንደሚያዉከዉ አልሸሸጉም።ይሁንና ሽራን አደጋዉ ከባድ ቢሆንም ለሕዝቡ መድረስ አለብን ባይ ናቸዉ።

ብዙዎች እንደሚሉት ሚሊዮኖችን ያስራበዉ ድርቅ ወይም ተፈጥራዊ መቅሰፍት ብቻ አይደለም።እንዲያዉም ከተፈጥሮዉ ይልቅ ሰዉ ሠራሹ ችግር የጥፋት ሁሉ ዋነኛ መሠረት ነዉ። አሸባብ በተለይ ለሶማሊያዉ ችግር መባባስ አንዱ ሰበብ መሆኑ አያጠያይቅም።ኢትዮጵያን የረሐብና የረሐብቶች አብነት ላደረገዉ የረሐብ ዑደት፥ ኬንያን ከኢትዮጵያ ተርታ ላሠለፈዉ ረሐብ ፖለቲካዊዉ ምክንያት ዛሬም እንደ ረሐቡ ዑደት ከጉጭ አልፋነት ንግግር አለማለፉ ነዉ ሌላዉ ድቀት።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic