የራሱን ህዝብ ከጨለማ ያላወጣው የብርሃን ምንጭ ክፍለ-ዓለም ፣ አፍሪቃ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 17.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የራሱን ህዝብ ከጨለማ ያላወጣው የብርሃን ምንጭ ክፍለ-ዓለም ፣ አፍሪቃ፣

በ 19 ኛው ክፍል ዘመን ፣ አፍሪቃን በቅኝ ግዛት ለመቀረማመት የበቁት ወገኖች ይህን ክፍለ-ዓለም «ጨለማው ክፍል ዓለም» የሚል ተቀጥላ ስም ሰጥተው እስከ ቅርብ ጊዜም ቢሆን አልፎ- አልፎ ይህንኑ አገላለጽ የሚጠቅሱበት ሁኔታ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም ።

default

ከአየር ላይ የተነሣ፣ በምድረ በዳ የተተከሉ፣ የፀሐይ ኃይል አጠራቃሚ አውታሮች ፎቶግራፍ ፣

አባባሉ በሥነ-ቴከኒክ፣ እንደነርሱ በአፋጣኝ አለመምጠቁን ለማመላከት ካልሆነ በስተቀር፣ አፍሪቃ፣ የሰው ዘር መገኛ ፣ የሥልጣኔም ምንጭ መሆኑን አሌ ማለት አይቻልም። የአያሌ ሺ ዓመታት የሥልጣኔውን ክምችት ፣ ሌሎች መነሻ አድርገው ሲገሠግሡ፣ አፍሪቃ እንዳጀማመሩ ፊት ቀድሞ አለመገኘቱ እሙን ነው።

አፍሪቃ፣ የደለበ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረውም፣ በአሁኑ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን ፣ ከሌሎች ክፍለ-ዓለማት ሁሉ በኤኮኖሚ ተዳክሞ እንደሚገኝ ይታወቃል። ለሥልጣኔ መስፋፋት ማስመስከሪያው ፣ በሥነ-ቴክኒክ ውጤቶች፣ ህዝብ፣ በሰፊው እንዲገለገል ማብቃት ነው። በተለይም በኃይል ምንጮች!

የዓለም የሥልጣኔ ምንጭነቱን አሻራ ያላጣው፣ የተፈጥሮ ውበትም ያልተጓደለበት አፍሪቃ፣ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ፣ከአሜሪካና ከአውሮፓ ጋር በማነጻጸር ለማመላከት የሚሹ ጠበብት እንደሚሉት፣ ድቅድቅ ባለ ሌሊት በሳቴላይት የተነሱ ፎቶግራፎችን የሚመለከት ማንም ሰው፣ አብዛኛው የአፍሪቃ ክፍል፣ የመብራት ማመንጫ አውታሮች ተግባር ተቋርጦበትም ሆነ ሳይተከልለት በመቅረቱ፣ ከተሞችና መንደሮች ጨለማ ውጦአቸው ነው የሚታዩት። እርግጥ ነው፣ አብዛኛው የአፍሪቃ ክፍል፣ የተተከሉ የኃይል ማ መንጫ አውታሮች ተግባር እየተቋረጠበት ሳይሆን፣ ከእነአካቴው ባለመዳረሳቸው ፣ 77% የክፍለ-ዓለሙ ህዝብ የኤሌክትሪክ መብራት ባለማግኘት ጨለማ እንደዋጠው ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ ወደ 350 ሚልዮን የሚጠጉ አፍሪቃውያን የኤልክትሪክ አገልግሎት አያገኙም። ሁኔታዎች ሳይለወጡ በአንዲህ ከቀጠለ ደግሞ ፣ በ20 ዓመታት ውስጥ፣ የኤልክትሪክ አግልግሎት የ,ማያገኙት አፍሪቃውያን መጠን ፣ ወደ 600 ሚልዮን ከፍ ሊል ይችላል። ከሁሉም እጅግ አሳሳቢው የገጠሩ ህዝብ አኗኗር ነው። 95% ያህሉ፣ የኤልክትሪክ አግልግሎት ላያገኝ ይችላል። በቅርቡ በፓሪስ ፈረንሳይ ተካሂዶ በነበረ አንድ ዓለም አቀፍ የኅይል ምንጭ ነክ ጉባዔ ላይ እንደተገለጠው፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ረገድ፣ አማካይ የኑሮ ደረጃ ያለው አንድ አሜሪካዊ ፣ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋር ሲነጻጸር 350 እጥፍ ተጠቃሚ ነው።

አፍሪቃ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በተፈጥሮ ፣ አያሌ የኃይል ምንጮችን የታደለ ክፍለ-ዓለም ነው። ውሃ፤ ፀሐይ ፤ ነፋስ፣ በትኅተ- ምድር የሚገኝ የእንፋሎት ኃይልና የመሳሰሉ የታዳሽ ኃይል ምንጮች አልተሠራባቸውም እንጂ ሰፊ ጠቀሜታ እንደሚሰጡ ከቶ የሚያጠራጥር አይደለም። የኃይል ምንጭን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ፣ ድኅነትን መቋቋም የሚያስችል መሠረተ-ልማት ለመዘርጋት፣ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ያዳግታል።

አፍሪቃ፣ ቀደም ሲል እንዳልነው በኅይል ምንጭ ረገድም የተፈጥሮ ፀጋ በሰፊው የታደለ ክፍለ-ዓለም እንደመሆኑ መጠን፣ ሲሳዩ ለሌላም እንደሚተርፍ የተገነዘቡት የአፍሪቃ ሰሜናዊ አዋሳኝ ክፍለ-ዓለም፣ የአውሮፓ 15 የኃይል ምንጭ ኩባንያዎች ፣ ታላላቆቹ የጀርመን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጭምር ማለት ነው፣ በሰሃራ ምድረ በዳ ሊጠቀሙ የአጭርና የረጅም ጊዜ አቅድ አውጥተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ዋና መ/ቤቱ ፣ በሙዩኒክ፣ ደቡብ ጀርመን የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኢንዱስትሪ ኩብንያ ዚመንስ፣ አንዳንድ ታዋቂ የገንዘብ ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ 15 ኩብንያዎች ፣ ሐምሌ 6 ቀን 2001 ዓ ም፣ በመሰብሰብ፣ ሰሜን አፍሪቃ ውስጥ በሰሃራ ምድረ-በዳ፣ የፀሐይን ኃይል የሚያጠራቅሙ አውታሮችን ለመትከል 400 ቢሊዮን ዩውሮ ያህል ገንዘብ ሊመደቡ ተስማምተዋል። የበረሃ ሥነ-ቴክኒክ (Desertec)በተሰኘው መርኅ-ግብር መሠረት ፣ በሰሃራ ምድረ-በዳ ከሚተከሉ አውታሮች ፣ የሚጠራቀመው፣ ወደ ኤልክትሪክ ኃይል የሚለወጠው፣ የፀሐይ የሙቀት ኅይል ፣ ለመሃል አውሮፓ ጥቅም እንዲሰጥ ይደረጋል። በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ ከሆነ ፣ፕሮጀክቱ፣ አዲስ አይደለም ማለት ይቻላል። ከአንጸባራቂው የፀሐይ ብርሃን፣ ሙቀቷን በአውታሮች አጠራቅሞ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመለወጥ፣ መጠቀም ከተጀመረ ፣ 24 ዓመት ሆኗል። የፀሐይ ኀይል ጠቀሜታው፣ ራሷ ፀሐይ በደመና ብትሸፍንም ፣ ደም ሲል የተራቀመውን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻል መሆኑ ነው። በጀርመን የአየርና የኅዋ ጉዞ ምርምር-ነክ መ/ቤት፣ ፣ የፀሐይ ሙቀት ጉዳይ የሥነ-ቴክኒክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር Robert Pitz-Paal እንዲህ ይላሉ።

«በሰሜን አፍሪቃ ና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የፀሐይ ሙቀት ኃይል፣ በዚህ በመካከለኛው አውሮፓ ካለው ጋር ሲነጻጸር እጅግ በሰፊው ይበልጣል። የሰሜን አፍሪቃው፣ ከደቡብ አውሮፓውም ቢሆን የላቀ መሆኑ እሙን ነው። በእስፓኝም ቢሆን የፀሐይ ሙቀት መጠን እንደ የሰ ሜን አፍሪቃውን ያህል የሚያይል አይደለም። በሰሜን አፍሪቃ ሰፋ ያለ ነጻ ቦታ አለ። በመሠረቱ፣ በዚያ እጅግ ሰፊ በረሃ ፣ ለሰሜን አፍሪቃ አገሮችና ለአውሮፓ አግልግሎት የሚሰጡ የፀሐይ ሙቀት አጠራቃሚ አውታሮችን ለመትከል ከ 2-3% የሚሆነው ቦታ ብቻ በቂ ነው። »

ኤል ካውቲ ኻሌድ/ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ