የሪያድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን መጻዒ ጊዜ | ዓለም | DW | 24.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሪያድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን መጻዒ ጊዜ

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በግዛቱ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የጣለው የቤተሰብ የነፍስ ወከፍ ወርሃዊ ክፍያ እና የዋጋ ጭማሪ በዚያ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው ብዙዎች ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01

የሳዑዲ ኢትዮጵያውያን ትኩረት የሳበው የዋትስ አፕ ገጽ

አብዛኞቹ እንደሚሉትም፣ ከነ ቤተሰቦቻቸው ጠቅልለው ሀገር መግባትም ሆነ ሳዑዲ ዓረቢያ መኖር ፈተና ሆኖባቸዋል። ሪያድ ውስጥ የተጀመረ አንድ የዋትስ አፕ ቡድን ለኢትዮጵያዊያኑ የመወያያ፣ የመማሪያና አንዳንዴም የንትርክ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ከነቤተሰባቸው ጠቅለው ወደ ሀገራቸው ለመግባት የሚሹ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እየጠየቁ ነው።                                                     
    
በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵዊን በዋትስ አፕ አማካኝነት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የድምጽ የጽሁፍ የፎቶግራፍም ሆነ የተንቀሳቃሽ ፊልሞችን ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የሚተላለፉ ወቅታዊ ዘለቄታዊም ሆነ አጣዳፊ መመሪያ እና ደንቦችን የሰማ ላልሰማ ይዳረሱበታል። በአቶ አህመድ መሀመድ ጠንሳሽነት የተመሰረተው በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ የዋትስ አፕ ግሩፕ  የዋትስ አፕ ኩባንያ የሚፈቅደውን ከፍተኛውን የአባላት ብዛት ይዟል 250 አባላት ይዞም በተለይ ወቅታዊ እና አጣዳፊ በሚባለው በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያዊያን እጣ ፈንታ ላይ ማህበረሰቡን እያወያየ መረጃዎች እንዲንሸራሸሩ እያደረገ ይገኛል። በሳዑዲ ዓረቢያ በአንጻራዊነት የኢንተርኔት አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘቱ ማኛውም ነዋሪም ለኢንተርኔት መገልገያነት የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በቀላሉ ማግኘቱ ዋትስ አፕን ተመራጭ የመገናኛ መንገድ አድርጎታል፡፡
አቶ አህመድ መሀመድ እና አቶ አልአሚን ጀማል የዋትስ አፕ ግሩፑን በመመስረት፣ አባላትን በመጋበዝ እና ገጹን በማስተዳደር ባለፉት አራት ወራት ሰፊ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

Äthiopier WhatsApp Gruppe in Riad

አቶ አልአሚን ጀማል እና አቶ አህመድ መሀመድ

በሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ሀገር ዜጎችን በተመለከተ የሚወጡ ተከታታይ ህጎች እነሱን ተከትለው የመጡም ሆነ የሚመጡ ከፍተኛ ክፍያዎች ቅጣቶች እንዲሁም የዋጋ ጭማሬዎች መካከለኛ ገቢ ላላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ከፍተኛ ፈተና ፈጥረዋል፡፡ በአንጻራዊነት በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በተለይ በየአመቱ አንድ መቶ  የሳዑዲ ሪያል እየጨመረ የሚመጣው ወርሃዊ የቤተሰብ የነፍስ ወከፍ ክፍያ ሳዑዲን የሩቅ ህልም እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል። ዘንድሮ በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ መሆን ያውም ከነ ቤተሰብ እጅግ ውድ መሆኑን አቶ አላሚን እና አቶ አህመድ ይያረጋግጣሉ።
የሳዑዲን ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ትኩረት የሳበው የዋትስ አፕ ገጽ በበዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚቀባበሉ እና የሚጋሩ ሀሳቦችንም አንስቷል ከዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት የአውሮፓ አሚሪካንም ሆነ የመካከለኛውን ምስራቅ ዲያስፖራዎች በአንድ ሚዛን መስፈር እንደማይገባው በተደጋጋሚ የሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ረጅም ዘመን በመኖርም ሆነ በመወለድ ዜግነትም ሆነ ቋሚ የመኖሪያፍ ቃድ በማይገኝበት ሀገር አሁን ደግሞ ለመኖርም ከፍተኛ ክፍያ በተጠየቀበት ሁኔታ መንግስት የዜጎቹን ድምጽ ሊሰማ ይገባል የሚሉ በርካቶች ናቸው። አብዛኞቹም በመንግስት ተስፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትን ወክለው በሳዑዲ ለጉብኝት የሚመጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም ሆኑ  የኤምባሲው ዲፕሎማቶች በሳዑዲ የኢትዮጵያ ዲስፖራ ግሩፕ ለሚነሱ ወቅታዊ ጥያቄዎች በጥናት የተደገፈ በጽሁፍ የተቀመጠ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሀሳብ አቅርቡ ማለቱን የግሩፑ መስራቾችም እና አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል። ይህንን ለማድረግም እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ስለሺ ሽብሩ

አርያም ተክሌ


 

Audios and videos on the topic