የሩስያ ወታደሮች በክሬሚያ ተኩስ ከፈቱ | ዓለም | DW | 22.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሩስያ ወታደሮች በክሬሚያ ተኩስ ከፈቱ

ሩስያ ክሪሚያን ይፋ የግዛትዋ አካል አድርጋ ከተቀበለች በኋላ ሩስያ በዚያ በይፋ የጦሩ ቁጥጥሯን አጠናከረች። ከዩክሬይን በተገነጠለችው ክሪሚያ ውስጥ ባሉት 147 የዩክሬይን የጦር ሰፈሮች የሩስያ ባንዴራ መውለብለብ መጀመሩን የሩስያ መከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል።

ከ67 የዩክሬይን መርከቦችም 54ቱ በሩስያ ቁጥጥር መዋላቸውን ሚንስቴሩ አክለው አመልክቶዋል። የሰርጓጅ መርከቦች ኃይላት ዋና አዛዥ አናቶሊ ቫሮችኪን እንዳስታወቁት፣ ብቸኛው እና በሰቫስቶፖል የሚገኘው የዩክሬይን የባህር ሰርጓጅ መርከብ «ሳፖሮሾዬ» አሁን በሩሲያ ቁጥጥር ይገኛል። ግማሹ የመርከቡ ሰራተኞች በሩስያ ባህር ኃይል ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸው ተያይዞ የወጣው ዜና አመልክቶዋል። በሩስያ መከላከያ ዘገባ መሰረት፣ ከ18,000 የዩክሬይን ወታደሮች መካከል ክሪሚያን ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉት 2,000 እንኳን አይደርሱም። በመጨረሻ በወጡ ዘጋባዎች መሰረት፣ የሩስያ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች በያዙት የዩክሬይን የቤልቤክ ጦር ሰፈር ተኩስ መሰማቱ ተገልጾዋል። በተያያዘ ዜና ጀርመን ለዩክሬይን የሽግግር መንግሥት ተጨማሪ ርዳታ እንደምትሰጥ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬ መዲናይቱን ኪየቭ በጎበኙበት ጊዜ ቃል ገቡ። ሽታይንማየር ሩስያ ከፊል ደሴት ክሪሚያን ወደ ግዛትዋ የቀላቀለችበትን ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ ሲሉ አውግዘውታል። በክሪሚያ ሰበብ አሁን የተፈጠረው ውዝግብ አውሮጳን ሊከፋፍል እንደማይገባ ሽታይንማየር አስጠንቅቀዋል። ጀርመናዊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከኪየቭ ቀጥለው ወደ ዶኔስክ በመጓዝ ከከተማይቱ ዋና አስተዳዳሪ ጋ ለመነጋገር አቅደዋል። የአንድ ምዕራባዊት ሀገር ከፍተኛ ባለሥልጣን በዚችው ከተማ የክሪሚያን ዓይነት ውዝግብ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወደዚያ ሲጓዝ ሽታይንማየር የመጀመሪያው ናቸው።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ