የሩስያ እና አፍሪቃ ወዳጅነት ማንሰራራት | ኢትዮጵያ | DW | 08.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሩስያ እና አፍሪቃ ወዳጅነት ማንሰራራት

የአፍሪቃ ኅብረት ዋና መቀመጫ የሆነችዉ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኙት የኃያላኑ መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስለምትገኘዉ ስለኢትዮጵያ፤ ሰላም፤ ስለሕዝቧ የመናገር ነጻነትና ዴሞክራሲስ ይወያዩ ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:28

ስለኢትዮጵያ፤ ወቅታዊ ሁኔታ ይወያዩ ይሆን?

በሳምንቱ መጀመርያ ሰኞ አምስት የአፍሪቃ ሃገራት ጉብኝታቸዉን በአንጎላ የጀመሩት የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ነዉ ። የላቭሮቭ ይህ ጉብኝት ከቀድሞዎቹ የሶቭየት ኅብረት ወዳጅ አፍሪቃ ሃገራት ጋር የነበራቸዉን ወዳጅነት በማደስ ኤኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር መሆኑ ተነግሮል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩስያ ለጉብኝት የመረጠቻቸዉ በደቡባዊ አህጉሩ የሚገኙት አራቱ የአፍሪቃ ሃገሮች አንጎላ ናሚቢያ ሞዛምቢክ እና ዚምባቤ በተፈጥሮ ጥሬ ሃብታቸዉ የበለፀጉ ናቸዉ። በአፍሪቃዉ ቀንድ ስልታዊ አቀማመጥዋ የምትታወቀዉ ኢትዮጵያም  ዘንድሮ ከሩስያ ጋር ይፋዊ የወዳጅነት ግንኙነትን የጀመረችበትን 120ኛ ዓመት በጋራ በማክበር ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል።  

በሳምንቱ መጀመርያ ሰኞ የአፍሪቃ ጉብኝታቸዉን በአንጎላ የጀመሩት የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከአንጎላዉ ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎረይንስ እና ከአንጎላ አቻቸዉ ከማኑኤል ዶሚንጎ አጉስቶ ተነጋግረዋል። ላቭሮቭ በዚህ ዉይይታቸዉ በሁለቱ ሃገራት መካከል ስላለዉ ረጅም ወዳጃዊ ግንኙነት አጽኖት ሰተዋል። ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ ከሩስያ ጋር የሚደረገዉ የጋራ የትብብር ሥራ የትምህርት ስልጠናን፤ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት፤ አልያም ወታደራዊዉ ዘርፍን ሁሉ እንደሚጠቃልል ነዉ ላቭሮቭ የጠቆሙት። ላቭሮቭ መዲና ሉዋንዳ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአፍሪቃ ችግር በአፍሪቃዉያኑ መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት ማመናቸዉን ነዉ ገልፀዋል።

«የአፍሪቃ ችግር አፍሪቃዊ መፍትሄን ይሻል በሚለዉ አቋም ላይ እኛም ፅኑ እም ነት አለን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፍሪቃዉያኑ ችግሮቻቸዉን የሚፈቱበትን መንገድና መፍትሄ ማክበር ይኖርበታል። በፖለቲካዊ እና በፋይናንስ ጉዳዮች ድጋፍ በመስጠት፤ እንዲሁም ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስልጠና በመስጠት ረገድ ሊረዳቸዉ ይገባል። ይህን በተመለከተ ሩስያ በንቃት በመሳተፍ ላይ ትገኛለች»

ላቭሮቭ ይህንኑ ንግግራቸዉን በናሚቢያ በሞዛምቢል እንዲሁም ዚምባቤ ላይ ደግመዉታል። በኢትዮጵያዉ ጉብኝታቸዉም ይህንኑ እንደሚናገሩ ይጠበቃል። የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪቃ ጉብኝት፤ ሩስያ ከአፍሪቃ ጋር ዳግም የወዳጅነት ግንኙነት መጀመር መፈልግዋን አመላካች ነዉ ሲሉ በቡርኪናፋሶ የቀድሞዉ ሶቭየት ኅብረት አምባሳደር፤ በመለጠቅ በማሊ የሩስያ ተወካይ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሞስኮ የሩስያ አፍሪቃ ምርምር ተቋም ተጠሪ ይቭጌኒ ኮርንዲያሶቭ ተናግረዋል።  

«በፈጣን እድገት ላይ የሚገኘዉ የአፍሪቃ አህጉር፤ የሃገራቱ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ጉድኝት ተፈላጊነትም የዛኑ ያህል እየጨመረ መቷል። በዓለማችን የሚታዩ አዳዲስ ችግሮች ማለት እንደ ከባቢ የአየር ለዉጥ፤ ሽብርተኝነትን መዋጋት፤ እንዲሁም አገር አቋራጭ የሆኑ ወንጀሎችን ለመታገል ያለ አፍሪቃ ሊሆን አይቻልም።»

ሩስያ ከአፍሪቃ ጋር በንግድና በኤኮኖሚዉ ዘርፍ ወዳጅነትዋን ማጠናከር ትፈልጋለች። ካርዲያሶቭ እንደሚሉት የሩስያ የጥሪ ማዕድን ፍላጎት ከምታመርተዉ ምርት በእጥፍ የጨመረ ነዉ። ለምሳሌ ሩስያ ማንጋኒዝ የተሰኘዉን የብረት አይነት 100 % ፍጆታዋን የምታስገባዉ ከዉጭ ነዉ። የክሮሚዩም ማዕድንን ፍጆታዋን 80% ዉን የምታስገባዉ ከዉጭ ሃገራት ነዉ። የኡራን የተሰኘዉ ማዕድን ፍጆታዋን በራስዋ የተፈጥሮ ሃብት ብቻ መሸፈን አትችልም። ስለዚህም ላቭሮቭ በደቡባዊ አፍሪቃ የመዓድን ኃብት የበለፀጉትን አራት የአፍሪቃ ሃገሮች መጎብኘት ያለምንም ምክንያት አይደለም። እንደሚታወቀዉ ናሚቢያ በኡራን መዓድን ምርት በዓለማችን ሦስተኛዋ ናት። ሞዛምቢክም የሩሲያ የነዳጅ አምራች ኩባንያ ሮዝንኔፍትን በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ በሚገኙት የነዳጅ ፍለጋ ኩባንያ ጋር እንዲሳተፍ ትሻለች።   

 በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የአፍሪቃ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ባደረጉት እንቅስቃሴ ድጋፍን አድርጋለች። ከነዚህ ሃገራት መካከል የናሚቢያዉ የ « SWAPO» ፓርቲ ተጠቃሽ ነዉ። «SWAPO»  በአሁኑ ወቅት የናሚቢያ ገዢ ፓርቲ ሲሆን ላቭሮቭ ባለፈዉ ማክሰኞ ናሚቢያን በጎበኙበት ወቅት አፍሪቃ በተመድ አንድ ቋሚ መቀመጫ ያስፈልጋታል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የላቭሮቭን ንግግር ያዳመጡት በሞስኮ የአፍሪቃ ምርምር ተቋም ተጠሪ ይቭጌኒ ኮርንዲያሶቭ በሶቭየት ኅብረት ዘመን ከአፍሪቃ ጋር የነበረዉ የጠበቀ ወዳጅነት በቀላሉ የሚረሳ አይደለም ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። ሞስኮ ላይ የሚገኙት የአፍሪቃ ጉዳይ ምሁሩ ሩስያዊ፤ ላቭሮቭ የጎበኝዋቸዉ የቀድሞ ሶቭየት ኅብረት አምስቱ የአፍሪቃ ታላላቅ ወዳጅ ሃገራት ማለት አንጎላ፤ ናሚቢያ፤ ሞዛምቢክ፤ ዚምባቤ እና ኢትዮጵያን "Big five" አምስቱ ታላላቅ ሲሉ ሰይመዋቸዋል።

ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ግንኙነት የመሰረተች ብቸኛዋ አፍሪቃዊት ሃገር ስትሆን ሁለቱ ሃገራት ዘንድሮ ይፋዊ የመንግስት ለመንግሥት የወዳጅነት ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት በማክበር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ዛሬ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ በሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ሃገር በሩስያ፤ ከ 20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ሞያዎች የከፍተኛ ትምህርታቸዉን እንዳጠናቀቁ በሩስያ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ግሩም አባይ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግምታቸዉን አስቀምጠዋል። በቀጣይ ከሩስያ ጋር ያለዉን ግንንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ግሩም ገልፀዉ ነበር።

«በኢትዮጵያና በሩስያ ፌደሬሽን መካከል የአየር ስምምነት ድርድሩ በቅርቡ ይቋጫል ብለን እናምናለን እሱ ካለቀልን የካርጎ በ,ራ እንጀምራለን፤ የካርጎ በረራ ከጀመርን አበባ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የኢትዮጵያ የዉጭ ንግድ አቅርቦት ዉጤቶችን ወደዚህ ማድረስ እንችላለን።»    

የላቭሮቭ የኢትዮጵያ ጉብኝት ይልቅ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀዉ ላቭሮቭ ከዩኤስ አሜሪካዉ አቻቸዉ ከሪክስ ቴልርሰን ጋር አዲስ አበባ ላይ መገናኘት ነዉ። እንደ አፍሪቃ ጉዳይ ምሁሩ ሩስያዊ ኮርንዲያሶቭ የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት ኃይልነት ለማሳየት አይደለም ባይ ናቸዉ።  በጋራ አሸባሪነት በጋራ ለመዋጋት፤ በአፍሪቃ የሚታየዉን ድህነት ለመቅረፍ ጥረት ለማድረግ እንጂ። የአፍሪቃ ኅብረት ዋና መቀመጫ የሆነችዉ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኙት የኃያላኑ መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስለምትገኘዉ ስለኢትዮጵያ፤ ሰላም፤ ስለሕዝቧ የመናገር ነጻነትና ዴሞክራሲስ ይወያዩ ይሆን? አብረን የምናየዉ ይሆናል።  

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች