1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ አፍሪቃ ጉባኤ እና የኒጀር መፈንቅለ መንግስት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 22 2015

ለሁለት ቀናት በሩሲያ ሴንትፒተርቡርግ ከተማ የተካሄደው የሩሲያ አፍሪቃ ጉባኤ ለስድስት የአፍሪቃ ሀገሮች ሩሲያ እህል በነፃ ለማደል ወስናለች።በሌላ በኩል ለቀጠናው የመረጋጋት ምልክት ተደርጋ ስትታይ የቆየችው ኒጄር በመፈንቅለ መንግስት እየታመሰች ነው።

https://p.dw.com/p/4UXbx
Russland-Afrika Gipfel
ምስል Vladimir Smirnov/TASS/dpa/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ ሀምሌ 22 ቀን 2015



በጎርጎሪያኑ  ሀምሌ 27 እና 28 ለሁለት ቀናት በሩሲያ ሴንትፒተርቡርግ ከተማ በተካሄደው  የሩሲያ አፍሪቃ ጉባኤ በጎርጎሪያኑ  2019 ዓ/ም  በሶቺ  በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት 45 መሪዎች  በቁጥር ዝቅ ብሎ 17 መሪዎች ብቻ  መሣተፋቸውን  ማክሰኞ ዕለት ከክሬምሊን የወጣው መረጃ ያሳያል።ሞስኮ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤውን ችላ እንዲሉ በማድረግ የምዕራቡን ዓለም ጫና ወቅሳለች። 
በጉባኤው የአፍሪካ የምግብ ዋስትና  አጀንዳ ነበር።የሩሲያው ፕሬዝደንት ብላድሚር ፑቲን በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው በዓለም ለተከሰተው የምግብ ቀውስ መፍትሄ ለመስጠት የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።ለችግር ለተጋለጡ የአፍሪቃ ሃገራት ሩሲያ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረቧን እንደምትቀጥልም ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሩሲያ፤ ዩክሬን ለገበያም ሆነ ለእርዳታ የምታደርገውን የእህል አቅርቦት ተክታ ማቅረብ ትችላለች ብለዋል። ሩሲያ በቀጣይ ሦስት እና አራት ወራት 50 ሺህ ቶህ እህል ለቡርኪና ፋሶ፤ ለዚምባብዌ፣ ለሶማሊያ፣ ለኤርትራ እና ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ለመላክ መዘጋጀቷንም አመልክተዋል። ጋዜጠኛ ማሪ ሙለር ግን በቂ አይለም ትላለች።
«ብዙ አይደለም፣ እህሉ ለስድስት፣ የአፍሪካ ሀገራት፣ ይላካል ተብሎ ተነግሯል። እነሱም ዚምባብዌ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ማሊ፣ኤርትራ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ናቸው። በመሠረቱ በአፍሪካ አህጉር ላሉ የሩሲያ ቁልፍ አጋሮች። በአብዛኛዎቹ እንደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና እንደ ማሊ ያሉ የዋግነር አሻራ ያረፈባቸው ናቸው።ለምሳሌ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል አይደሉም። እነዚህ ሀገሮች በተለይ በድርቅና በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው።»
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በቱርክ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት በጦርነት በምትታመሰው ዩክሬን ተዘግተው የነበሩ የዩክሬን ሦስት የጥቁር  ባህር ወደቦች ተከፍተው ወደ አፍሪካ አህጉር በሰላም ለመላክ ችላለች። ይሁንና ሞስኮ ከሳምንት በፊት ስምምነቱን  በማቋረጧ በአፍሪካ ሀገራት የምግብ እጥረት እንዳይፈጠር ስጋት ፈጥሯል።
 ባለፈው ሳምንት ሞስኮ ከስምምነቱ ለመውጣት መወሰኗን ተከትሎ «ምዕራቡ ዓለም እውነተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አገሮችን ከመርዳት ይልቅ የእህል ስምምነቱን ለፖለቲካ ትርፍ ተጠቀሞበታል»በማለት ገልፃለች። ስትል ተናግራለች። 
የአፍሪካ መሪዎች በበኩላቸው በሀገሮቻቸው ውስጥ የከፋ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ሩሲያን ከዩክሬን፣ ከተመድ እና ከቱርክ ጋር ወደ ውይይት እንድትመለስ መገፋፋቱን ቀጥለዋል። 
ንግድ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ሌላው የጉባኤው አጀንዳ ነበር።በ 2019 በሶቺ በተካሄደው  የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ የንግድ ልውውጥን በእጥፍ ለማሳደግ እና በአህጉሪቱ  የሩሲያን የመዋዕለንዋይ ፍሰት ለማሳደግ ትልቅ እቅድ ነበረው ።ይሁን እንጂ በሶቺ የተገባው ቃል ሊሳካ ባለመቻሉ የአፍሪካ መሪዎች ተስፋ ሳይሳካ ቀርቷል።
ባለፉት ዓመታት በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር (ከ13-€18 ቢሊዮን ዩሮ) አካባቢ  ነበር። እንደ ተንታኞች ገለጻ፣ በአንጻራዊነት  ሞስኮ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር አነስተኛ የንግድ ልውውጥ ታደርጋለች።ይህም ከቻይና እና ከምዕራባውያን ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ኢኮኖሚያዊ አጋር ያደርጋታል። የሩስያ  በአፍሪካ የውጭ ቀጥታ የመዋዕለንዋይ ፍሰትም 1% የሚሸፍን ነው። ያምሆኖ በሰሞኑ ጉባኤም ሩሲያ በአፍሪቃ የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንደምታሳድግ ተነስቷል።የዶቼቬለዋ ማሪ ግን ገፅታው ሌላ ነው ትላለች። 
«እንዲሁም የዋግነር በአህጉሪቱ ላይ መገኘቱ በመሠረቱ ለሩሲያ የውጭ ፖሊሲ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። እና አሁን እንደምናውቀው ዋግነር በማሊ እና  በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ አለ። ሀገራቱም ለዋግነር እና ለክሬምሊን የተፈጥሮ ሃብቶችን ያቀርባሉ። በአፍሪካ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት ዋናው ገጽታ ይህ ነው።»በማለት ገልፃለች።
በዚህ ሳቢያ ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት የሚተቹ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ «በተፈጥሮ ሀብት እና የጦር መሳሪያ ልውውጥ» ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ነው ይላሉ።
የፖሊሲ ተንታኝ ኦቪግዌ ኢጉጉ በበኩላቸው በአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት የደህንነት ስልጠናዎችን እና የፀጥታ አጋርነት እያደረገ የሚገኘው የዋግነር ቡድንም  አገልግሎቱ ነፃ አይደሉም።ይላሉ።
«የዋግነር አገልግሎቶች ነፃ አይደሉም። ስለዚህ የውል ስምምነቶች መኖር አለባቸው። እና እነዚህ ሀገሮች ለአገልግሎቶቹ መክፈል አለባቸው።ጥናት እንደሚያሳየው በብዙ አጋጣሚዎች እነዚህ አገሮች ክፍያ እየፈጸሙ ነው።እና በዶላር ከመክፈል ይልቅ አልማዝ ወይም ወርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሀብትን እየተጠቀሙ ነው።»
በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የጦር መሳሪያ ስምምነትም ትኩረት ስቧል። የጦር መሳሪያ ስምምነቶች ከአፍሪካ የሩሲያ የንግድ ልውውጥ በጣም ስኬታማው ነው። ከሁለት አመት በፊት ሩሲያ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ የጦር መሳሪያ አቅራቢ በመሆን ቻይናን ቀድማለች። 
አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ግብፅ እና ሱዳን ብቻ 94 በመቶውን በሩሲያ ሰራሽ መድፍ እንደሚገዙ ይገመታል።
ለአፍሪካ ሀገራት የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት ሩሲያ ትርፍ እና የጂኦፖለቲካዊ ተፅእኖን ለማግኘት እየሞከረች ነው።ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ጉባኤ ሩሲያ ሌላ ማትረፍ የምትፈልገው ነገር አለ።
«ለሩሲያ የጂኦፖለቲካዊ ሃይል የምትፈጥርበት መድረክ ነው። አዎ፣ አሁን ያለነው ከአፍሪካ ጋር ነው። አዎ፣ በምዕራባውያን የተገለልን ነን ግን፤ አሁንም በአፍሪካ ውስጥ አጋሮችን እያገኘን ነው።ለማለት ነው።ግን ደግሞ ግልፅ ነው።ዛሬ ለሩሲያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር  በዩክሬን ጦርነቱን ማሸነፍ ነው።»
የኒጀር አለመረጋጋት ለሳህል ቀጠና ስጋት
ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኒጀር ለቀጠናው የመረጋጋት ምልክት ተደርጋ ስትታይ ቆይታለች። በሀገሪቱ በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም የተሳካ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ሲደረግ በአጎራባች ሀገራት ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ሀይሎች  በተከታታይ አራት መፈንቅለ መንግስት አድርገዋል። በዚያ የስልጣን ሽግግር ወቅት በኒጀር የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት አልተሳካም ነበር።
ሰሞኑን ግን በኒጀር የነበረው ሰላም እና የመረጋጋት አልቀጠለም።ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም ከረቡዕ ጠዋት ጀምሮ በወታደራዊ የጥበቃ አባሎቻቸው ተይዘው ታስረዋል።የወታደራዊ ቃል አቀባይ በመንግስት ቴሌቪዥን ወጥተው እንተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን መነሳታቸውን እና የሪፐብሊኩ ተቋማት መበተናቸውን አስታውቀዋል።
ባዙም ራሳቸው ይህንን መቀበል አይፈልግጉም። «ሁሉም በብዙ ጥረት የተገኙ ስኬቶች ተጠብቀው ይቆያሉ» በማለት በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል። ይህንንም ሁሉም የዲሞክራሲ እና የነፃነት ወዳድ ኒጄሪያውያን  ይጠብቁታል  ሲሉም አክለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃሱሚ ማሱዱ በበኩላቸው  ስለ መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን ማውራት የፈለጉት ስለ «መፈንቅለ መንግስት ሙከራ» ብቻ ነው። ሚንስትሩ ሰራዊቱ በአጠቃላይ ከጉዳዩ  ጀርባ አይደለም። ሲሉ ለፈረንሣይ 24 የዜና ማሰራጫ ተናግረዋል።
እሳቸው ይህን በተናገሩ በአንድ ቀን ልዩነት ግን የኒጀር የፕሬዚዳንታዊ ጥበቃ ሃላፊ ጄኔራል አብዱራሃማን ቺያኒ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ መሆናቸውን ትናንት አርብ በሀገሪቱ የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ በይፋ ተናግረዋል።
ጄኔራል ችያኒ  የሐገሪቱ ሕዝብ እሳቸዉ ከሚመሩት የሐገር ደሕንነት አስከባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ(CNSP-) ጋር እንዲተባበር ጠይቀዋል።
ጄኔራሉ እንዳሉት ቡድናቸዉ የፕሬዝደንት መሐመድ ባዙምን መንግስት ከሥልጣን ያስወገደዉም የኒጄርንርን የፀጥታ፣የምጣኔ ሐብትና የማሕበራዊ ቀዉስን ለማስወገድ ነዉ።
የሰራዊቱ ወታደራዊ አዛዥ መፈንቅለ መንግስቱን መደገፋቸው  በጦር ኃይሉ ውስጥ የተናጠል ቡድን እንዳይፈጠር የታሰበ ይመስላል፤ ምክንያቱም በከፋ ሁኔታ ሱዳን ውስጥ እንዳለው አይነት ጦርነት ሊፈጠር ይችላልና።
በባማኮ ማሊ የሚገኘው የኮንራድ አድናወር ፋውንዴሽን የሳህል ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኡልፍ ላሲንግ ግን ኒጀር ከዚህ በኋላ ቀጠናውን የምታረጋጋ ሀገር አትሆንም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
«አሁን ኒጀር በጣም የተረጋጋች ሀገር ናት። በሳህል ውስጥ ያሉ ሌሎች ሀገራትን ማረጋጋት ትችላለች የሚባለው ትርክት ትልቅ ቅዠት ሆኗል። ስለዚህ ማሊን እና ቡርኪናፋሶን በሚያዋስነው ሶስት ማዕዘን አዋሳኝ  ድንበር ላይ የሚንቀሳቀሱ እንደ እስላማዊ ግዛት ያሉ አንዳንድ አክራሪ ቡድኖች ከመፈንቅለ መንግስቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።»
የኒጀር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በኒያሚ በተፈጠረው አለመረጋጋት እና ውድመት የተቃውሞ ሰልፎችን ከልክሏል።የአውሮፓ ህብረት ለኒጀር የሚሰጠውን እርዳታ እንደሚያቋርጥ ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኒጀር የሰብዓዊ ርዳታ መስጠቱን እንደቀጠለ ቢሆንም መፈንቅለ መንግስቱ ድንበር ከተዘጋ በኋላ የእርዳታ በረራዎችን ለማቆም መገደዱን አመልክቷል።
የባዙም መንግስት  ምን ያህል መጥፎ ነበር?
ኒጄሪያዊው ጋዜጠኛ ሴይዲክ አባ ለDW እንደተናገረው «ፕሬዚዳንቱ የፀጥታ መዋቅሩን ወዲያውኑ ባለማስቆጣጠራቸው ተሳስተዋል።»ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ሙሳ አክሳር  እንደሚለው ግን በፕሬዚዳንቱ አስተዳደር እርካታ ማጣት ለመፈንቅለ መንግስቱ እንደ ምክንያት ይነሳል። በጎርጎሪያኑ  2021 ምርጫ ወቅት ባዙም ከሁለት የስልጣን ዘመን በኋላ እንደገና ስልጣን ለመያዝ ባልቻሉት በቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ማሃማዱ ኢሱፉ ይደገፉ ነበር። ሙሳ አክሳር ለDW እንደተናረው በዚህ የተነሳ ባዙም ከሳቸው በፊት የነበሩት መሪ «ግልባጭ» ተደርገው ይወሰዱ ነበር፣ ይህም ብዙ ኒጀርያውያንን አሳዝኗል።አክሳር እንደሚለው የባዙም መንግስት በሀገሪቱ ለውጥ አላመጣም።
«መንግስት ምንም አይነት ለውጥ አላመጣም። ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገብቷል። ነገር ግን የወንጀል ድርጊቶችን የፈጸሙ  የገዥው የፓርቲ አባላት ምንም አልሆኑም።» ሲል ይተቻል።
በዋና ከተማዋ ኒያሚ  ያለው ስሜት ምን ይመስላል?
በአሁኑ ስዓት በዋና ከተማዋ ኒያሚ ያለው ስሜት የተደበላለቀ ነው።የDW ጋዛሊ አብዱ በዋና ከተማዋ ኒያሚ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል። አንድ አስተያየት ሰጪ « ወታደሩ ሁልጊዜ በፕሬዚዳንት ባዙም ደስተኛ አይደለም። ስለዚህ ለእኔ መሞከር ይሻላል  ከዚያ በአዲሱ ገዥ ላይ ምን እንደሚሆን እናያለን»በማለት ተናግሯል። 
ሌሎች ደግሞ መፈንቅለ መንግስት እና ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል። አንዲት አስተያየት ሰጪ ደግሞ «መፈንቅለ መንግስት ለዲሞክራሲያችን የኋልዮሽ እርምጃ ስለሆነ ለሀገር መጥፎ ነው። ስለዚህ ኢኮዋስ (የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ማህበረሰብ) እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን።»በማለት ስጋቷን ገልፃለች።
«ይህ ዲሞክራሲያችንን ወደ ኃላ የመለሰ ርምጃ ነው። ምክንያቱም መፈንቅለ መንግስት ለሀገር መጥፎ ነው።ስለዚህም ኢኮዋስን እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ ነገር እንዲያደርግ እንጠይቃለን።»
 ረቡዕ ዕለት የፕሬዚዳንት ባዙም ደጋፊዎች ለእሳቸው የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።በማግስቱ ደግሞ ተቃዋሚዎች የፒኤንዲኤስ ፓርቲ ዋና መሥሪያ ቤትን አውድመዋል።ነገር ግን ባዞም በህዝቡ ያን ያህል ተወዳጅ ናቸው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ይላል ጋዜጠኛ አክሳር። የመንግስትን ድጋፍ  የሚገድብ ሌላም ምክንያትም ይጠቅሳል።
«ነገር ግን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጽዕኖ አለ። በተለይ በቡርኪፋሶ ወይም በማሊ እየሆነ ባለው ነገር የኒጀር ማህበረሰብን ጨምሮ ህብረተሰቡን የሚመርዝ ፀረ ፈረንሣይ አመለካከት አለ።»
በማሊ ያለው ገዥው ወታደራዊ ጁንታ ፊቱን ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ወደ ሩሲያ እየዞረ ነው ። የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳውም የሩሲያ ደጋፊዎች ፕሮፓጋንዳ  ይመስላል።
ክስተቱ ለቀጠናው ምን ትርጉም አለው?
ባዙም የምዕራቡ ዓለም ታማኝ አጋር ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፣ በዚህ ስር ኒጀር የበለጠ ጠቃሚ ሚና መጫወት ነበረባት።በማሊ ያለው አለማቀፋዊ ወታደራዊ ዘመቻ በአምስት ወራት ውስጥ ሲያበቃ የሳህል አካባቢን ለማረጋጋት ኒጀር ለምዕራባውያን የጦር ሰፈር ትሆናለች የተባለች ብቸኛ ሀገር ነበረች።ፈረንሳይ ባለፈው አመት የመጨረሻ ወታደሮቿን ከማሊ ወደ ኒዠር አስጠግታለች።
 ለዓመታት  አሸባሪ ቡድኖች በመላው የሳህል ክልል እንቅስቃሴያቸውን እያጠናከሩ ሲሆን ኒጀርን ጨምሮ ደም አፋሳሽ ጥቃቶችን በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ ቆይተዋል።የአሁኑ ክስተትም ለአሸባሪዎች የተመቸ ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሯል። ለቀጠናውም  አለመረጋጋት ይፈጥራል።
በመሆኑም መፈንቅለ መንግስቱ ከተፈፀመ በኋላ የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ እና የልማት ሚኒስትር ስቬንጃ ሹልዜ ለባዙም ያላቸውን ድጋፍ ጠቁመው ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ እንዲመለስ ጠይቀዋል።
የጀርመን ጦር እና አጋሮቹ ከጎርጎሪያኑ 2018 ጀምሮ በኒጀር ወታደሮችን በማሰልጠን ላይ ነው።በአሁኑ ጊዜም ለአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ እየተዘጋጀ ነው።የሀገሪቱ  አለመረጋጋት እነዚህን ዕቅዶች ሁሉ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
ናይጄሪያዊ ተንታኝ ጂምባ ካካንዳ  ደግሞ ዓለምአቀፍ አጋሮች በኒጀር የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲሁም ልማት እና ዕርዳታ ይቀንሳል የሚል ሌላ ስጋት አላቸው።
«አጋር የሆኑ የውጭ መንግስታት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ሊመለሱ ነው። ድህነት ይባባሳል፣ የአደረጃጀት እጦትም ይባባሳል። ይህኔ ህዝቡ ተስፋ ይቆርጣል። ከዚያም መንግስት። ምክንያቱም በልማት ድጋፍ እጦት ሊመጡ በሚችሉት ማዕቀቦች  መንግሥት ተስፋ ቆርጦ በሕዝብ ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል።  ሽብርተኝነትን መዋጋት ከመሰለ ከትልቁ ጦርነትም ይስተጓጎላል።ይህም ቀጠናውን ወደ አለመረጋጋት ይወስዳል።»በማለት  አስጠንቅቋል።

Deutschland Berlin Annalena Baerbock (Bündnis 90/Die Grünen), Bundesaußenministerin
ምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance
Niger Protest in Niamey
ምስል AFP
ARCHIV Niger Niamey | Präsident Mohamed Bazoum
ምስል Boureima Hama/AFP/AP/dpa/picture allaince
Niger | General Tchiani übernimmt Macht nach Putsch gegen Präsident Bazoum
ምስል ORTN/Télé Sahel/AFP/Getty Images
Ägypten Niger Präsident  Mohamed Bazoum
ምስል Ludovic Marin/AFP
Zentralafrikanische Republik Bangui | Russische Wagner-Kräfte sichern Präsident Faustin-Archange Touadéra
ምስል Leger Kokpakpa/REUTERS
2nd Russia-Africa Summit: plenary session
ምስል Mikhail Tereshchenko/TASS/dpa/picture alliance
Russland, Sankt Petersburg | Zweiter Wirtschafts- und humanitärer Gipfel 2023, Russland - Afrika | Wladimir Putin, Präsident
ምስል Pavel Bednyakov/POOL/AFP/Getty Images


ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ