የሩሲያና የአውሮፓው ኅብረት መሪዎች ጉባዔ፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የሩሲያና የአውሮፓው ኅብረት መሪዎች ጉባዔ፣

የሩሲያና የአውሮፓው ኅብረት መሪዎች፣ በምሥራቃዊው ሩሲያ ፣ ከብራሰልስ 8,000 ከሞስኮ 6,000፣ ከቻይና ድንበር ደግሞ 30 ኪሎሜትር ብቻ ራቅ ብላ በምትገኘው ከተማ፣

default

የሩሲያና የአውሮፓው ኅብረት መሪዎች ጉባዔ፣በካባሮቭስክ፣

በ ካባሮቭስክ ፣ ጉባዔ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተመለከተ። በዚሁ ጉባዔ የሩሲያው ርእሰ-ብሔር ፣ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፣ የአውሮፓው ኅብረት ከቀድሞዎቹ የሶቭየት ኅብረት ግዛቶች ጋር ለመቀራረብ የሚያደርገውን ጥረት ከማውገዛቸውም፣ ዩክሬይን ያለባትን የጋዝ ክፍያ ዕዳ እንድትክፍል፣ አውሮፓ ያግዛት ዘንድ አሳስበዋል። ጂዎርጂያና ሩሲያ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ድንገተኛ ጦርነት በማካሄዳቸው የሻከረ መስሎ የነበረው የሩሲያና የአውሮፓው ኅብረት ግንኙነት ፣ የአርስ በርስ መተማመንን በመገንባት በአዲስ መልክ የሚገነባበት አመቺ ሁኔታ መፈጠሩም ተነግሯል።

---ተክሌ የኋላ፣--

ከብራሰልስ የ 10 ሰዓት በረራ ጊዜ የምትወስደው የ 9 ሰዓት ልዩነትም ያላት ፣

እጅግ ራቅ ብላ የምትገኘው ከተማ ፣ ካባሮቭስክ፣ ለጉባዔ አስተናጋጅነት የተመረጠች ያለምክንያት እንዳይደለ ለማወቅ አላስቸገረም። ሩሲያ በዓለም ውስጥ አጅግ በግዙፍነት የአንደኛነቱን ደረጃ የያዘች ሀገር መሆኗን ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ ካጠገቧ አማራጭ የንግድ ተባባሪ ማለትም ቻይናም እንደምትገኝ ለማስገንዘብ ሳትፈልግ አልቀረችም። እንደ መልክዓ ምድራዊው ርቀት የሁለቱ ወገኞች ጥቅም ያን ያህል የተራራቀ ቢሆንም፣ ጉባዔው ማቀራረብ የሚቻልበት የዕድል በር እንዲከፈት ማብቃቱ አልቀረም ነው የተባለው። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፣ ጉባዔው ባጣሙን እንዳረካቸው የገለጡ ሲሆን የወቅቱ የአውሮፓው ኅብረት ፕሬዚዳንት የቼክ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ቫክላቭ ክላውስም ውይይቱ ፍሬያማ ነበረ ሲሉ ገልጸዋል። ጉባዔው እርስ በርስ መግባባቱን እንዲሻሻል፣ መተማመኑም እንዲጠናከር ማድርጉ ተነግሮለታል። የአውሮፓው ኅብረትና ሩሲያ፣ በካውካሰስ ጦርነት፣ ከዩክሬይንም ጋር ተፈጥሮ በነበረው፣ የጋዝ አቅርቦትን በሚመለከተው ንትርክ ሳቢያ ፣ ግንኙነታቸው ቀዝቀዝ ብሎ እንደነበረ ቢታወቅም ፣ በአሁኑ ጉባዔ፣ የመቀራረቡ መንፈስ ተሻሽሎ ነው የታየው። እርግጥ ነው ከሞላ ጎደል ለሁሉም ከባድ ጉዳዮች መፍትኄ በመሻቱ ረገድ፣ ስምምነት ላይ መድረስ ቀርቶ በሓሳብ መቀራረብ አልተቻለም። ለምሳሌ ያህል፣ የሩሲያው ርእሰ ብሔር ሜድቬዴቭ፣ አገራቸው የአዲሱ የኃይል ምንጭ ቻርተር አባል እንዳልሆነችና አሁን በሠፈረው ደንብም ባለመስማማቷ እንደማትፈርም ነው ያስገነዘቡት። እርሳቸው እንዳሉት፣ ደንቡ፣ የተጠቃሚዎችን ጥቅም እንጂ፣ የምርቱን አቅራቢዎች አላጤነም። ስለሆነም የበኩላቸውን የማሻሻያ ሐሳብ አቅርበዋል። የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ፣ የቀረበው የኃይል ምንጭ ቻርተር እንዲሁ ሊጣል የሚችል አይደለም ነው ያሉት።

«የኛ ሐሳብ፣ በግልፅ የሩሲያን የመፍትኄ ሐሳብ አቅርቦ ፣ ከቻርተሩ ሳያፈነግጡ መወያየት ነው። የቀረበው ሰነድ ግን የጥያቄ ምልክት ሊቀርበበት አይገባም። »

ካሉ በኋላ ከዚህ ጋር በማያያዝ የሚከተለውን ቃል ሰንዝረዋል።

«እንደምታውቁት ሁሉ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፣ እነዚህም በይፋ የሚታወቁ ናቸው። የኃይምን ምንጭን ችግር በተመለከተ፣ ሁለቱም ወገኖች፣ የአውሮፓው ኅብረትና ሩሲያ፣ የታቻለንን ሁሉ በማድረግ ፣ ለሁሉም የሚበጅ ሁኔታ መፍጠር አለብን። የኃይል ምንጭ ካስተሣሠሩን ነገሮች መካከል አንዱ ነው። አውሮፓ ከሩሲያ የኃይል ምንጭ እንደሚሻ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። እንደሚመስለኝ ሩሲያም ጥሩ ደንበኞች ሊኖሯት ይገባል፣፣ እንደእኛ ፣ እንደ --የአውሮፓው ኅብረት የመሰለ ማለት ነው---ስለዚህ እርስ በርስ ጥገኞች መሆናችንን በአወንታዊ መልኩ እንተርጉመው። በእርግጥ በዚህ መንፈስም ነው በፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ የቀረበውን ሐሳብ የምንመረምረው።»

ባሮሶ ፣ ከሀገር አገር በድንበር መተላለፊያዎች ሊያጋጥሙ የሚቻሉ ችግሮችን ለመቋቋም ፣ ከዩክሬይን ጋር በመተባበበር ፣ አስቀድሞ የሚያስጠነቅቅ አውታር እንደሚተከል አስታውቀዋል። ሩሲያ ለአውሮፓ ጸጥታ ይበጃል ብላ ያቀረበችውን ሓሳብም የአውሮፓው ኅብረት ሊወያይበት ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል። የአውሮፓው ኅብረት በቅርቡ የመሠረተው፣ የምሥራቅ ሸሪኮች የተሰኘው ትብብር፣ በቻባሮቭስክ አጅንዳ ተይዞ ተመክሮበታል። ሩሲያ ግን አልተቀበለችውም። ሩሲያ በጆርጂያና ዩክሬይን አማካኝነት ፀረ ሩሲያ ፖለቲካ ሊሠራ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባት ነው ያስገነዘበች። ሁለቱም ወገኖች፣ ለፋይናንስ ቀውስና ለፀጥታ ችግሮ በጋራ መፍትኄ መሻት እንደሚበጃቸው፣ ንግድን ፣ የኃይል ምንጭንና የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃን በተመለከትም በጣሙን ተቀራርቦ መሥራት እንደሚጠቅማቸው ተነግሯል። ብዙዎቹ ጥያቄዎች በአንጥልጥል ቢገፉም ወደፊት በውይይት መፍትኄ ሊያገኙ እንደሚገባ ይታመንበታል።

ተክሌ የኋላ ፣ ሒሩት መለሰ