የሩሲያና የአሜሪካ የስለላ ጥልፍልፍ | ዓለም | DW | 12.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሩሲያና የአሜሪካ የስለላ ጥልፍልፍ

ሱትያጊን በሙያም፥ በእዉቀት፥ድፍረትም በስለላ አቅምም ፓወርስን አይደሉም። አሜሪካዊም አይደሉም። የፓወርስን ተልዕኮ በራሳቸዉ መንገድ ለመጋራት ግን የሙያ-ዜግነት ልዩነት፥የዘመን ርቀትም አልገደባቸዉም።

default

አስሩ ተጠርጣሪዎች-በስዕል

12 07 10


የሞስኮቫይቶች-ተቃርኖ። ባለፈዉ ሰኔ ሃያ ከኒዮርክ የተሰራጨዉ ዜና-ለዲሚትሪ ሱትያጊን-ከቁብ የሚገባ አይደለም።ለወዘሮ ኢሪና ኩሼንኮ ግን አስደንጋጭ ነበር።ዉበት፣ብልጠት ድፍረቷን የሚያደንቋት ልጃቸዉ ታሰረች።ሱትያጊን በእዉቀት፣ ብስለት ብልሐቱ የሚመኩበት ወንድማቸዉ በሰላይነት-ከተወነጀለ ጀምሮ-እንዳሳቡ፣አንዳቀረቀሩ ነዉ።አስራ-አንድ አመት።አርብ።ሰዉዬዉ-ከሞስኮ  ወጣቷ ከኒዮርክ ወደ ቪየና ተላኩ።ሱትያጊን ፈገግ-አሉ እንዳቀረቀሩ።ኩሽሼንኮም ተደሰቱ። «አሁን ምንም መናገር አልፈልግም» አሉ በኩራት ለጋዜጠኞቹ።እና ጀግና-ዉብ ሰላይ ልጃቸዉን ሊቀበሉ-ከመኪናቸዉ ገቡ።የዋሽንግተን-ሞስኮዎችን የስለላ ጥልፍልፍን አስታከን፣ በሞስኮቫይቶች ተቃራኒ-ምግባር እያጣቀስን ትዉስታ ምክንያቱን ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።
 ---------------------------

ፍራንሲስ ጌሪ ፓወርስ ከፓሻወር-አዉሮፕላን ማረፊያ ከፓኪስታን ያስነሳት ልዩ ዩ-ቱ አዉሮፕላን የሶቬት ሕብረትን ሰማይ እየሰነጠቀች ትከንፋለች።የፓይለቱ ችሎታ፥ ታማኝ-ቆራጥነት፥ የአዉሮፕላንዋ ፍጥነት፥ከሬዳራር ቁጥጥር ዉጪ ሽቅብ የመምጠቅ-ረቂቅነት በአሜሪካዉ ማዕከላዊ የሥለላ ድርድጅት CIA ተሞክሮ፥ ተፈትኖ ያለቀ ጉዳይ ነዉ።ግንቦት።አንድ።-1960 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)።አየሩም የሰጠ ነበር።

የሶቬት ሕብረት ግግር በረዶ እየቀለጠ ነዉ። የአሜሪካ ልዩ የስለላ አዉሮፕላኖች የሶቬት ሕብረትን ግዛት ጥሰዉ እየገቡ የወታደራዊ ተቃዋሟትን ፎቶ እያነሱ እንደሚጠፉ-የሶቬት ሕብረቱ የሐገር ፀጥታ ኮሚቴ KGB በምሕፃሩ ጠንቅቆ ያዉቃል።የCIA ሹማምንት የሞስኮ ባለንጦቻቸዉ እንደሚያዉቁ ቢጠረጥሩም ሞስኮዎች የእነዚያን ረቂቅ ልዩ አዉሮፕላኖችን ተልኮ የሚያከሽፉበት መሳሪያ እንደሌላቸዉ እርግጠኞች ናቸዉ።

ቨርጂንያ ሌሊት ነዉ።የላንግሌይ ሹማምንት ግን አልተኙም።ሲጋራቸዉን እያቦኑን የፓወርስን መልዕክት ይጠብቃሉ። ሞስኮ ጎሕ ቀደደ።የፓወርስ ልዩ አዉሮፕላን የስቫርድሎቮስክ አየር እየሰነጠቀች ብልጭ ድርግም ትላለች። የሶቬት ሚግ ሃያ ዘጠኝ እና ኤስ ዩ ዘጠኝ ጄቶች ሽቅብ-ወደ አሜሪካዋ ልዩ አዉሮፕላን  ተፈተለኩ።ከመሬትም ከሰማይም-ሚሳይሉ ይምዘገዘግ ገባ።ልዩ

Russland Spionage Physiker Igor Sutjagin wegen Hochverrat verurteilt

ኢጎር ሱትያጊን

አዉሮፕሏኗ ጋየች።

ቆራጡ፥ታማኙ አሜሪካዊ ሰላይ ተማረከ-ግንቦት 1960።

ሶቬት ሕብረት ምዕራቡን የምትቧጭር፥ የምትነክስበት ጥፍር-ጥርሷ ረግፎ፥ ምሥራቁን የምታቅፍ-የምዕራቡን ጫና የምትመክትበት ክንዷ ዝሎ ስትበታተን አናቷ ሩሲያ ብቻዋን ዉንን ዉን ማለቱ-   ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ቦሪስ የልሲንም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያይልባታል ባዮች ነበሩ።ሶቬት ሕብረት የተፈረካሰችበት ስንንተኛ፥ የCIAዉ የስለላ አዉሮፕላን የተመታችበት- ስልሳ ስምተኛ አመት በተዘከረ በሳምንቱ ወጣቱ የቀድሞ ሰላይ የሩሲያን የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን ያዙ።ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን።ግንቦት 8 1998።

ሰዉዬዉ-በጎርቫቾቭ-ይደነቁ እንጂ ጎርቫቾቭን አይደሉም።በየልሲን ይሾሙ እንጂ እንደ የልሲን አይደሉም።በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት አዉሮጳ የሚቀለጣጠፈዉን ስላላ-አፀፋ ስለላ በርሊን-ምሥራቅ ጀርመን ሆነዉ ይዘዉሩ የነበሩት ፑቲን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ሲይዙ-የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለሙያዉ ኢጎር ሱትያጊን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ የወታደራዊና የጦር መሳሪያ ጥናት ተቋም ሊቀመንበር ሆኑ።

ፑቲን ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ የድሮ መስሪያ ቤታቸዉን ኬጂቢን አፍርሰዉ ባዲስ መልክ ማዋቀሩን ጨርሰዉ ነበር። የሩሲያ የዉጪ የስላላ አገልግሎት (SVR-በሩሲያኛ ምሕፃሩ) እንዲጠናከር እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ባዘዙ ባመቱ-ሙያተኞቻቸዉ አንድ ሁለት ማለት ሲጀምሩ ኢጎር ሱቲያጊን አገኙ።1999 ሱትያጊን በሙያም፥ በእዉቀት፥ድፍረትም በስለላ አቅምም ፓወርስን አይደሉም። አሜሪካዊም አይደሉም። የፓወርስን ተልዕኮ በራሳቸዉ መንገድ ለመጋራት ግን የሙያ-ዜግነት ልዩነት፥የዘመን ርቀትም አልገደባቸዉም።

የሩሲያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሱትያጊን የሩሲያን የጦር መሳሪያ በተለይም የኑክሌር ሐይሏን የሚጠቁም መረጃ በአንድ የብሪታንያ ድርጅት በኩል ለCIA ሲያጮልጉ ነበር።አስራ-አምስት አመት ተፈረደባቸዉ።ዲሚትሪ ሱትያጊን ወንድማቸዉ ከተያዙ-ጀምሮ እንደሰጉ፥ በሐገር ከሐዲነት ከተወነጀሉ በሕዋላ እንደተሸማቀቁ ነዉ-የኖሩት።በቀደም ግን-አሉ የኢጎር ወንድም።
«ኢጎር ከአንድ ጄኔራል ጋር ያደረገዉ ዉይይት እንደነገረኝ ጉዳዩ በሁለቱ ወገኖች ትላልቅ ባለሥልጣናት መያዙ ግልፅ ነዉ።ምናልባት የሩሲያና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንቶች እጅ ሳይኖርበት አይቀርም።»

ሰኔ-22 1953።የኒዮርኩ ጋዜጣ አዟሪ ያዉ እንደወትሮዉ የማታዉን እትም ከዚያ ሕንፃ ለሚኖሩ ደንበኞቹ አድሎ ሳንቲሙን እያቃጨለ ወደ ሌላዉ ሕንፃ ሲሻገር አንድ ነገር አስተዋለ።በግራ እጁ ከሚያቃጭላቸዉ ሳንቲሞች የአንዷ ድምፅ የተለየ ነዉ።ታብረቀርቃለችም።ከሲሚቶዉ መሬት ላይ ጣላት ግምስ አለች።እሁለት ከተገመሰዉ የሳንቲሟ አካል የሆነ ነገር-ፎቶም፥ ስዕልም፥ ቁጥር፥ ፅሁፍ የሚመስል ረቂቅ ነገር ወደቀ።

የሳንቲሟ ታሪክ ከጋዜጣ አዟሪዉ ለአንድ ደንበኛዉ፥ ከደንበኛዉ ለአንድ የፖሊስ ልጅ፥ ከፖሊሱ ልጅ ለፖሊሱ ከፖሊሱ እያለ ከአሜሪካዉ ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ-FBI ጆሮ ደረሰ።ያቺ ጉደኛ ሳንቲም የያዘችዉ መልዕክት ከኬጂቢ ጠቅላይ ቢሮ ኒዮርክ ለሚገኘዉ የሶቬት ሕብረት ሰላይ የተላከ የተመሰጠረ መዕልዕክት ነዉ።

የFBI ባለሙያዎች ኒዮርክ ተቀምጦ የአሜሪካን ሚስጥር ወደ ሞስኮ የሚያንቆረቁረዉን ሰዉ በአራተኛ አመቱ ያዙት።ኮሎኔል ሩዶልፍ አቤል።ታሰሩ።1957።አዲሱ የሩሲያ የዉጪ የስላላ አገልግሎት SVR)  ኢጎር ሱትያጊን ካሰረ በሕዋላ ወደ ምዕራብ የሚያሻግረዉ ወይም ከዚያዉ ከምዕራብ የሚጠልፈዉ ሰላይ ለማግኘት-ማዉጠንጠኑ አልቀረም። አቤልን ብጤ በሳል፥ ብልጥ አስመሳይ ባለሙያ እንደማያገኝ ግን ያዉቀዋል።

እሷን አገኘ።አና ኩሽሼንኮን።ሰማያዊ አይኗን ወርወር ስታደረግ-ያየት ወንድ ወከክ አለማለት አይችልም።ጥቁር-ቀይማ ረጅም ፀጉሯን፥ ቀጭን ወገቧን አሳልፋ መቀማጫዋ ላይ ስትነሰንሰዉ ያያት ወንድ ሽቅብ ቁልቁል የሚደልቅ ልቡን መቆጣጠር ይሳነዋል።-ያዩዋት እንደሚሉት።ዉበትን ከናቷ፥ዲፕሎማሲያዊ ብልጥት፥የግድምድሞሽ ንግግርን ካባቷ ወርሳለች።

ኢጎር ሱትያጊን በሐገር ክሕደትና የሐገር ሚስትጥር አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ተከሰዉ ሞስኮ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ፥አና ኩሽሼንኮ በዉበት ብልጠቷ የምዕራቡን ሚስጥር ልትመገምግ ለንደን ገባች።2000።የአቤል አይነት ብሥለት፥ የሥለላ እዉቀት የላትም።ግን ልክ እንደ አቤል የሩሲያ ሰላይ ናት።በ2002 ያ ዉበት ካንድ ብሪታንያዊ ላይ አረፈ።

ሰላይ መሆኗ አይገርምኝም አሉ-ቀየድሞ ባለቤቷ አሌክስ ቻፕማን በቀደም።ሁል ጊዜ እራሷን እንደደበቀች፥ እንዳሸሸች፥በሚስጥር የምትኖር ነበረች።አከሉ።-ቻፕፓን ለብሪታንያዉ የስለላ ድርጅት በሰጡት ቃል።ወጣቷ የቤተሰብ ስሟን ኩሽሼንኮን በቻፕማን ለዉጧ፥ ትዳሯን አፍራሳ ኒዮርክ ተሻገረች።ነግድ ፍቃድ አወጣች።የምትነግደዉ ግን በርግጥ የአሜሪካን ሚስጥር ነበር።

የሩሲያ የስላላ አገልግሎት ኢጎር ሱትያጊን ላይ ያደረሰዉን ገመድ እየተረተረ-M16 ለተሰኘዉ የብሪታንያዉ የሥለላ ድርጅት ይሰልላሉ ያላቸዉን የቀድሞዉን የሩሲያ ጦር የስለላ ድርጅት ባልደረባ ኮሎኔል አሌክሳንደር ዛፖሮዢስኪን እና ሌሎች ሁለት ሰዎችን አስሯል።

የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ የስለላ ተቋማትም አልተኙም።ከሞስኮ እየተሸረበ ለንደን፥ ኒዮርክ፥ ቦስተን፥ ማሳቹስተስ፥ ቨርጂንያ፥ አልፎ-ተርፎ ቆጵሮስ ድረስ የተጠላለፈዉን መረብ ሲያጠኑ የከረሙት የCIA፥ የFBIና የተባባሪዎቻቸዉ ተቋማት ባለሙያዎች ያቀዱትን ለማድረግ የበላይ ትዕዛዝ ብቻ ነበር የሚጠብቁት።

የኢጎር ወንድም ዲሚትሪ ሱትያጊን ባለፈዉ አርብ እንዳስታወቁት ሚስጥሩ ለፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም ከደረሰ ዉሎ አድሯል።በኢራን ላይ አራተኛ ማዕቀብ ለማስጣል የሩሲያን ድጋፍ አበክረዉ የሚፈልጉት ኦባማ ግን ሩሲያን በዚያ ሰአት ማስቆጣት አልፈለጉም።ሰኔ-ዘጠኝ ማቀቡ በሩሲያ ድጋፍ ፀደቀ።በሁለተኛዉ ሳምንት ኦባማ ሩሲያዊ አቻቸዉን ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን ዋይት ሐዉስ ጋበዟቸዉ።በተለመደዉ ዲፕሎማሲያዊ ቃል ተሸነጋግለዉ ከጋዜጠኞች ተለዩ።

እሁድ ሰኔ-ሃያ ሰባት።ፕሬዝዳት ዲሞትሪ ሜድቬድቭ ከኦባማ ጋር ከተነጋገሩ ሁለተኛ ቀኑ ነበር።የኒዮርክ፥ የቦስተን፥ የኒዉጀርሲ የማሳቹስተስ ፖሊስ ይለቅም ገባ።ዘጠኙ የሩሲያ ሰላዮች ታያዙ።የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛ ኢቫን ፔረስ መረጃዉ ቀድሞ ከደረሳቸዉ አንዱ ነበር።
            
«የተወሰኑት ከሩሲያ የተላኩ ናቸዉ።ከካናዳ እና ከፔንስሎቬንያ የልደት ካርድ አግኝተዋል።አንዷ ግን የፔሩ ተወላጅ ሳትሆን አትቀርም።ያም ሆኖ እስካሁን የታወቀዉ አብዛኞቹ ሩሲያዊ መሆናቸዉ ነዉ።»

አንዷ እሷ ነበረች።የሃያ ስምንት አመቷ አና ቻፕማን ወይም ኩሽሼንኮ።በሳልስቱ የቆጵሮስ ፖሊስ አስረኛዉን ያዘ።ኮሎኔል አቤልና ብጤዎቻቸዉ በዚያ በራቀዉ ዘመን የሚመሰጥሩበት አይነት መሳሪያ ዛሬ ኋላ ቀር ነዉ።ፓይለት ፖወርስ የበረረባት ልዩ አዉሮፕላን ዛሬ ያረጀች ያፈጀች ናት።እነ አና ዘመን ሥለላ በኮፒዩተር የሚለጣጠፍ ነዉ።እንደገና ፔሬስ
«ስቴግኖ ግራፊ የተባለዉ የመልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር።መልዕክት መረጃና ሰነድ ለማስተላለፍ ይረዳል።በዚሕ ሥልት የተለያዩ መረጃዎችን ወደ ሞስኮ ይልኩ ነበር።ወይም ደግሞ አንዳቸዉ ካንዳቸዉ ጋር መልዕክት ይለዋወጡበት ነበር።

የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ ከሁለት ሳምንት በፊት ዋይት ሐዉስ ዉስጥ የተደረሰበትን ሥምምነት አላጡም።የሐገራቸዉ አስር ሰላዮች የመያዛቸዉ ዜና በአለም ሲናኝ ግን ያሉትን ከማለት ሌላ የዲፕሎማሲ-ፖለቲካዉ ወግ አይፈቅድላቸዉም ነበር።
«ለምን ይሕ እንደተደረገ ለኛ የተገለፀልን ነገር የለም።ጉዳዩን ለኛ ያስረዱናል የሚል ተስፋ አለኝ።አሁን ማለት የምችለዉ በቅርቡ በጣም ጥሩ ነገር መደረጉን ነዉ።» ጥሩዉ ነገር የላቭሮቭን መልዕክት የተረዱ ወገኖች እንደተረጎሙት ሜድቬድቬና ኦባማ ዋይት ሐዉስ ዉስጥ ያደረጉትን ዉይይት ነዉ።

የሥለላዉ ጥልፍ ልፍ በርግጥ የቀዝቃዛዉን ጦርነት ዘመን የተከተለ ያየኔዉ ሥልት የሚያስታዉስ ነዉ።የቀድሞ የምሥራቅ-ምዕራብ ጠላቶች ግን ዛሬ ወዳጅ ባይሆኑ እንኳን እንደወዳጅ እየሰሩ፥ እየተባበሩ ነዉ።ዋሽንግተን ሞስኮን መጋፋት ወይም ማስቀየም እንደማትፈልግ ሁሉ ሞስኮዎችም ዋሽንግተኖችን መቀናቀን አይሹም።አይችሉምም።

የሩሲያ ሰላዮች ከመያዛቸዉ በፊት የሁለቱ ሐገራት መሪዎች የደረሱበት ስምምነትም ይሕንኑ መስካሪ ነዉ።ሶቬት ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ፓይለት ፓወርስን ከኮሌኔል አቤል ጋር ለመቀያየር ሁለት አመት በሚስጥር መደራደር ባደባባይ መዛዛት፥ መፎካከር ነበረባቸዉ።በ1962 ተለወጡ።ብሪታንያ አስራቸዉ የነበሩ የሶቬት ሕብረት ጥንድ ሰላዮችን ፒተርና ሔለን ክሮገርን ሶቬት ሕብረት በያዘችዉ የብሪታንያ ሰላይ በጄራልድ ብሩክ በ1969  ለመቀየር ብዙ አመት ተደራድራለች።

ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ምዕራቡ አለም ከያኔዋ ሶቬት ሕብረት ጋር የመጨረሻዉን የተማረኩ ሰላዮች ልዉዉጥ ያደረገዉ በ1986 ነበር።ከልዉዉጡ ለመድረስ የዋሽንግተንና የሞስኮ መሪዎች ለአመታት ተሻኩተዋል።አሁን መሳሰሉ እንጂ ዉዝግብ ፉከራዉ ቀርቷል።ሩሲያዊዉ የወታደራዊ ጉዳይ አጥኚ አሌክሳንደር ጎልትስ እንደሚሉት ሁለቱም ወገኖች ቅሌቱን ማራገብ አልፈለጉም።አይፈልጉምም።
                 
«ይሕ የሚያመለክተዉ ሁለቱም ወገኖች ቅሌቱን ማጋጋም አለመፈለጋቸዉን ነዉ።ጉዳዩን ቶሎ መጨረስ መፈለጋቸዉን ነዉ።»

በርግጥም ቶሎ አለቀ።አና እና ዘጠኝ ባልደረቧቸዉን የያዘዉ አዉሮፕላን ቪየና አዉሮፕላን መረፊያ ሰወር ብሎ ቆሟል።ወዲያዉ ከሞስኮ የተነሳዉ ሌላ አዉሮፕላን እየተንፋቀቀ መጥቶ

Duell im Dunkel - Spionage im geteilten Deutschland

ትፍላጊዉን ሚስጥር በዚሕ ማጨቅ ይቻላል

ከኒዮርክ ከመጣዉ አዉሮፕላን ጎን ቆመ።አስሩ ከሞስኮ ወደ መጣዉ አራቱ ደግሞ ከኒዮክ ወደ መጣዉ አዉሮፕላኖች ገቡ።ዲሞትሪ ሱትያጎን እቤታቸዉ ናቸዉ።ሞስኮ።ወንድማቸዉን ኢጎርን እና ሰወስት ብጤዎቻቸዉን የጫነዉ አዉሮፕላን ለንደን ማረፉን ሰሙ።ተደሰቱ።ወይዘሮ ኢረና ኩሽሼንኮ አዉሮፕላን ማረፊያ ናቸዉ።ከቪየና የመጣዉ አዉሮፕላን መንገደኞች እየወረዱ።ፈገግ አሉ በኩራት።--ኩሽሼንኮ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic