የሩሢያ ጋዝና የአውሮፓ ጥገኝነት | ኤኮኖሚ | DW | 08.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሩሢያ ጋዝና የአውሮፓ ጥገኝነት

በጋዝ ዋጋ አለመግባባት ሳቢያ በሩሢያና በኡክራኒያ መካከል እንደገና የተነሣው ውዝግብ በማዕከላዊና ደቡብ ምሥራቅ፤ በምዕራብ አውሮፓ አገሮችም ጭምር ጠንካራ በሆነው በወቅቱ ክረምት ማሞቂያ እንዳይጠፋ፤ የኤነርጂ ችግርን እንዳያባብስ እያሰጋ ነው።

ጋዝ ማለፉ አቁሟል

ጋዝ ማለፉ አቁሟል

የሩሢያ የጋዝ አቅርቦት መሰናከሉ ከአሁኑ ሩሜኒያን፣ ቡልጋሪያን፣ ስሎቫኪያን፣ ሁንጋሪያንና መሰል ወጣት የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራትን ብርቱ ፈተና ላይ ሲጥል እጥረቱ የምዕራቡን ክፍል የኤነርጂ ኩባንያዎችንም እየተሰማ መሄድ ይዟል። የአውሮፓውያኑ መንግሥታት ኤኮኖሚ በሩሢያ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ጥገኝነቱ እስከምን ድረስ ነው? የሩሢያስ አቅርቦት አስተማማኝነት? ለአውሮፓ አማራጭ ማግኘቱ ቢቀር በአጭር ጊዜ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

ጋዝም ሆነ ሌሎች የኤነርጂ ምንጮች በዛሬው ጊዜ ከመቼውም በላይ የዘመናዊው ዕርምጃ ዕለታዊ አንድ አካል ናቸው። በዚህ በአውሮፓ ጀርመንን ጨምሮ በክረምቱ ወራት ከሁለት አንዱ ቤት የሚሞቀው በጋዝ ነው። ፍጆቱ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የተፈጥሮው ጋዝ ከዚህ ሌላ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨትና ለተለያዩ የንጥረ-ነገር ምርት ተግባራት፤ እንዲሁም ከዚህ ባሻገር በመጠኑም ቢሆን አውቶሞቢሎችን ለማንቀሳቀስም ግልጋሎት ላይ ይውላል።

እስካለፈው ሣምንት የጎርጎሮሣውያኑ አዲስ ዓመት መግቢያ ድረስ ኡክራኒያን አቁዋርጦ ወደተቀረው አውሮፓ የሚዘልቀው የጋዝ መተላለፊያ ቧምቧ በአግባብ እየሰራ ነበር። ከዚያን ወዲህ ግን ሩሢያ ፍሰቱን ቀጥ አድርጋዋለች። ምክንያቱ አሁንም እንደገና የሁለቱ ሃገራት መንግሥታዊ የጋዝ ኩባንያዎች ተቀባዩ ናፍቶጋዝና አቅራቢው ጋዝሮም በዋጋ ጭቅጭቅ የተነሣ የአቅርቦቱን ውል በማራዘሙ ረገድ ከስምምነት ሊደርሱ አለመቻላቸው ነው። ከሶሥት ዓመታት በፊት፤ ልክ እንዳሁኑ በዘመን መለወጫው ዕለት ተፈጥሮ የነበረ ተመሳሳይ ውዝግብ በአውሮፓ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የወቅቱን የአውሮፓን ሕብረት የመንፈቅ ርዕስነት ይዛ የምትገኘው የቼክ ሬፑብሊክ የአውሮፓ ሚኒስትር አሌክሣንድር ቮንድራ ሁኔታውን ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።

“የሕብረቱ ርዕስ ቼክ ሬፑብሊክና የአውሮፓው ኮሚሢዮን አቅርቦቱ በፍጥነት እንዲቀጥል፤ ሩሢያና ኡክራኒያም እንደገና ይደራደሩ ዘንድ ይጠይቃሉ። ሁኔታው በአሁን መልኩ በረጅም ጊዜ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው”

በጊዜው ጀርመንና ምዕራብ አውሮፓ ጭምር የሚቀርብላቸው ጋዝ ድንገት ሲቀንስ ያደረባቸው ስጋት የኤነርጂ አማራጭ የመሻት ክርክርን ነበር ያስከተለው። ሩሢያ በምዕራብ አውሮፓ ላይ ቧምቧውን ጨርሳ ብትዘጋ ምንድነው የሚሆነው? ከጥገኝነቱ ለመላቀቅ ምን አማራጭስ አለ? እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች የአውሮፓን ሕብረት በሰፊው አነጋግረዋል። ሆኖም አማራጭ ማግኘቱ እስከዛሬ ቀላል ነገር አልሆነም።

ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ሩሢያ በጋዝ ሃብትም በሰፊው የታደለች አገር ናት። ከዓለም የተፈጥሮ ጋዝ ሃብት ሲሶው በዕጇ ነው የሚገኘው። ታላቁ የአገሪቱ የጋዝ ሞኖፖል ጋዝፕሮም በክሬምሊን መንግሥት ሙሉ ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ደግሞ ንግዱን የፖለቲካ ተጽዕኖ የማያጣው ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር የጋዝፕሮም ደምበኞች ችግር እንዳይገጥማቸው ከክሬምሊንና ከቭላዲሚር ፑቲን ጋር ጥሩ ግንኙነት ማድረጋቸው ግድ ነው። በዚሁ ለምሳሌ ለሩሢያ በፖለቲካ ታማኝ የሆነችው ጎረቤት ቤላሩስ በርካሽ ዋጋ ጋዟን ታገኛለች። የኡክራኒያ ዕጣ ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው።
ኡክራኒያ ለሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ድርጅት ናቶና ወደ አውሮፓ ሕብረት ለመቅረብ የምታደርገው ጥረት ለሞስኮ የሚዋጥ ሆኖ አልተገኘም። እንግዲህ የጋዝ አቅርቦቱን መለጎም እንደ ቅጣትም ጭምር መሆኑ ነው።

እርግጥ የሩሢያና የኡክራኒያ የጋዝ ውዝግብ በሁለቱ አገሮች መካከል ተወስኖ አልቀረም። በሂደቱ ውስብስብ እየሆነ ነው የሚገኘው። ኡክራኒያ የሩሢያ የጋዝ ደምበኛ ብቻ አይደለችም። ወደ ሌሎች መተላለፊያም ጭምር እንጂ። አውሮፓውያን ሃገራት አንድ አምሥተኛውን ጋዝ ከሩሢያ የሚያገኙት ኡክራኒያን በሚያቁዋርጥ ቧምቧ አማካይነት ነው። ሩሢያ ለምዕራብ አውሮፓ የምታስተላልፈው 80 በመቶ ጋዟም እንዲሁ! የሁለት ወገን ጥገኝነት አለ ማለት ነው። ኡክራኒያ የሩሢያን ጋዝ ለራሷ፤ ሩሢያም በፊናዋ ጋዟን ወደ አውሮፓ ለማሻገር ኡክራኒያን ትፈጋለች።

ሃቁ ይህ ሲሆን ሁሉም የንግዱ ተሳታፊዎች አውሮፓውያን፣ ኡክራኒያም ሀነች ሩሢያ ወደፊት ከእርስበርሱ ጥገኝነት ቢላቀቁ ደስታቸው ነው። የአውሮፓ ሕብረት በዚህ አቅጣጫ ጥረት ማድረጉ አልቀረም። ለምሳሌ ጀርመንና ሩሢያ ምሥራቅ ባሕርን የሚያቁዋርጥ የጋዝ ቧምቧ ለመዘርጋት ስምምነት አድርገዋል። በባሕር ላይ ቧምቧው መዘርጋቱ ብዙ ገንዘብና ጥረት የሚጠይቅ አድካሚ ሥራ ቢሆንም ከሩሢያ አመለካከት አንጻር የኡክራኒያን ተጽዕኖ የሚቀንስ በመሆኑ ሞስኮም የምትመርጠው ነው። የአውሮፓ ሕብረትም ከሩሢያ ጥገኝነት የተላቀቀ የኤነርጂ ፖሊሲ ለማስፈኑ በወቅቱ ቅድሚያ መስጠቱን የቼክ ሬፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሬክ ቶፖላኔክ ሰሞኑን አጥብቀው እያስረገጡ ነው።

“የአውሮፓን የኤነርጂ አቅርቦት ማሻሻሉ አንዱ ትልቁ ውጥናችን ነው። ሕብረቱ ከዓባልነቱ ውጭ ከሆኑ አገሮች የአቅርቦት ጥገኝነት ነጻ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ በተለይ ከባልቲክ አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማስፋፋት እንፈልጋለን”

ግን ይህ በሌላ በኩል አውሮፓ በሩሢያ ጋዝ ላይ ያለባትን ጥገኝነት ቢቀር ለጊዜው አይለውጠውም። ጀርመንን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በወቅቱ ሁለት-ሶሥተኛ የጋዝ ፍላጎቷን ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች በምታስገባው የምትሸፍን ቢሆን ከሲሶ የሚበልጠው የሚመጣው ከሩሢያ ነው። የሩሢያ የጋዝ ክምችት ታላቅነት ሲታሰብ ግን ጀርመን ከኔዘርላንድ፤ ኖርዌይና ብሪታኒያ የምታስገባው ጋዝ በአማካይ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱ፤ በአንጻሩም የሩሢያ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ለዚህም ነው ጀርመንና በአጠቃላይም የአውሮፓ ሕብረት ለሩሢያ አማራጭ የሆነ ሰፊ የጋዝ ገበያ ለማግኘት በመጣር ላይ ያሉት።

በዚሁ መሠረትም ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘልቅ ሩሢያ የማትሳተፍበት ታላቅ የቧምቧ መስመር ለመዘርጋት ናቡኮ የተሰኘ ፕሮዤ ከዓመታት በፊት መታቀዱ ይታወቃል። የፕሮዤው ዓላማ የተፈጥሮን ጋዝ ከካስፒያን ባሕር ወደ አውሮፓ ማስተላለፍ መቻል ነው። ይሁንና አቅራቢዎች ሊሆኑ የሚችሉት አገሮች አዘርባይጃን፣ ካዛክስታንና ቱርክሜኒስታን ወይም ኢራን እስካሁን በፕሮዤው አንሳተፍም በማለታቸው ሃሣቡ ሊከሽፍ እያሰጋው ነው የሚገኘው። ለአውሮፓውያኑ ምክንያቱ የሩሢያ ተጽዕኖና ከመጋረጃ በስተጀርባ እነዚህ አገሮች ፕሮዤውን እንዳይቀበሉ የምታካሂደው ተግባር ነው።

እርግጥ በሌላ በኩል ሩሢያም ለአውሮፓ ጋዝ ማቅረቡን መተዋ ሲበዛ ያጠራጥራል። ምክንያቱም ሶሥት አራተኛው የሩሢያ ነዳጅ ዘይትና ዘጠና በመቶው የተፈጥሮ ጋዟ በወቅቱ የሚፈሰው ወደዚሁ ወደ ምዕራብ አውሮፓ ነው። ሌላ አማራጭ ገበያ የላትም። ቻይናን ብንወስድ አገሪቱ የኤነርጂ ጥሟን ለማርካት በሩሢያ ላይ ጥገኛ አይደለችም። ከዚሁ በተጨማሪ በሁለቱ አገሮች መካከል የዘይትም ሆነ የጋዝ ቧምቧ የለም። ታዲያ ሩሢያ የምዕራብ አውሮፓ የኤነርጂ አቅርቦቷን ብታቆም ሃብቷ ላይ ቁጭ ብላ መቅረቷ ነው። ይህ ደግሞ ለጋዝፕሮም ውድቀቱ ይሆናል።