የሩሜኒያና የቡልጋሪያ የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት | ኤኮኖሚ | DW | 18.05.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሩሜኒያና የቡልጋሪያ የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት

25 መግሥታትን ያቀፈው የአውሮፓ ሕብረት በያዘው ቀጣይ የመስፋፋት ሂደት ሩሜኒያንና ቡልጋሪያን በመጪው 2007 ዓ.ም. መጀመሪያ በዓባልነት ለመቀበል የጊዜ ገደብ አስቀመምጦ መቆየቱ ይታወቃል። ለመሆኑ እነዚህ ዕጩ አገሮች በወቅቱ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት? የአውሮፓ ኮሚሢዮን ከትናንት በስቲያ በጉዳዩ ያጠናቀረውን ወቅታዊ ዘገባ ይፋ አድርጎ ነበር።

የሕብረቱ መለያ ሰንደቅ ዓላማ

የሕብረቱ መለያ ሰንደቅ ዓላማ

እርግጥ ሁለቱ የባልካን አካባቢ አገሮች እስከዚሁ እስከታቀደው ጊዜ ድረስ ለዓባልነት የሚያበቁ የሕብረቱን የለውጥ መስፈርቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል። ነጻ የገበያ ኤኮኖሚና የዴሞክራሲ ሥርዓት በሕብረተሰቡ ውስጥ መቆናጠጥ መቻላቸው ግድ ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በሚገባ ያከበረ የፍርድ ሥርዓትም በሚፈለገው መጠን መዳበር ይኖርበታል። ሙስናን በመታገሉና የድንበር ጸጥታን በማረጋገጡ በኩልም እንዲሁ ብዙ ነው የሚጠበቅባቸው።

ቡልጋሪያና ሩሜኒያ ውሎ አድሮ የአውሮፓን ሕብረት መቀላቀላቸው ቀድሞ የተወሰነ፤ የማይለወጥ ያለቀለት ጉዳይ ነው። ጥያቄው መቼ? የሚለው ብቻ ይሆናል። እንደታቀደው በ 2007 ወይስ አንድ ዓመት ዘግየት ብሎ በ 2008 ዓ.ም.! የአውሮፓ ሕብረት ከነዚህ አገሮች ጋር ቀደም ሲል ያደረገው ስምምነት ሕብረቱ የሚፈለገውን ለውጥ በሚገባ በማራመዱ በኩል ከበድ ያለ ጉድለት ካየ የሚመለከታቸውን አገሮች በዓባልነት የሚቀበልበትን ጊዜ ሊያሸጋሽግ ይችላል የሚል ቁልፍ አንቀጽን የሚጠቀልል ነው።

የሕብረቱ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ከትናንት በስቲያ በአውሮፓ ፓርላማ በሰጡት መግለጫ “ሩሜኒያና ቡልጋሪያ፤ ሁለቱም አገሮች በሚቀጥሉት ወራት አንዳንድ ዕርምጃዎችን ዕውን ካደረጉ በጥር 1. 2007 ሕብረቱን ለመቀላቀል ሊዘጋጁ ይችላሉ” ብለዋል። በዚህ አቀራረብ የአውሮፓ ሕብረት በሁለቱ አገሮች ላይ ያልተጠበቀ መሰናክልም ነው ያስቀመጠው።

ግልጽ በሆነ አነጋገር የሕብረቱ ኮሚሢዮን ዕርምጃ ሁለቱ አገሮች ከአንድ ሙሉ ዓባል የሚጠበቁትን ቅድመ-ግዴታዎች ነጥብ በነጥብ ማሟላታቸውን ወሣኝ የሚያደርግ ነው። የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ባሮሶ በአውሮፓው ፓርላማ ንግግራቸው እየገፉ ሲሄዱ ይህው ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መሄዱ አልቀረም። በዚሁ መሠረት ቡልጋሪያ በተለይም በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ሙስናን ፍቱን በሆነ መንገድ እየታገለች ለመሆኗና ጉዳዩን በሕግ እየተከታተለች ተጠያቂዎቹንም በቁርጠኝነት ለመቀጮ እንደምታበቃ ገና ግልጽ መረጃ ማቅረብ ይኖርባታል።

ጥቂት ለዘብ ባለ መልክም ቢሆን ከሩሜኒያም የሚጠበቀው ተመሳሳይ ዕርምጃ ነው። የቡካሬስት መንግሥት እስካሁን ከአውሮፓ ሕብረት የሚቀርብለትን ገንዘብ በአግባብ ሥራ ላይ መዋል በመቆጣጠሩ በኩል፤ ለምሳሌ የዕርሻ ድጎማን ለገበሬዎች በቀጥታ መተላለፉን በተመለከተ አስተማማኝ ዋስትና ሊሰጥ አልቻለም ተብሎ ተወቅሷል። ባሮሶ በንግግራቸው ሂደት ሁለቱ ዕጩ አገሮች ለዓባልነት ታላቅ ጥረት ማድረጋቸውን ቢመሰክሩም ይህ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ በቡካሬስትና በሶፊያ ላይ ያለውን ጥርጣሬ አላለዘበውም። ሃቁ በርካታ ዘርፎች ስኬታማ ለሆነ የዓባልነት ዕጩነት በሚያበቃ መንገድ አለመለወጣቸው ነው።

ከነዚሁ መካከል የዕርሻ ልማትና የምግብ ምርቶች ደህንነት ዋስትና፤ የፍርድ ሥርዓት፣ የአገርግዛት ፖሊሲና ፊናንስ ይገኙበታል። እያንዳንዱ፤ የአውሮፓውን ሕብረት መቀላቀል የሚፈልግ አገር የሕብረቱን መስፈርቶችም ማሟላት ይኖርበታል። ቡልጋሪያና ሩሜኒያ ቀደም ሲል እንደታቀደው በመጪው 2007 ዓ.ም. መጀመሪያ የሕብረቱን ክለብ ለመቀላቀል የሚጠበቀውን ሁሉ ለማሟላት የሚቀሯቸው ጥቂት ወራት ብቻ ናቸው። ታዲያ ጠንከር ብለው የቀረቡትን ቅድመ-ግዴታዎች በዚሁ አጭር ጊዜ አርኪ በሆነ መልክ ማሟላት ሊኖርባቸው ነው።
እርግጥ ትችትና ወቀሳ ቢደረደርባቸውም ፈጠነም ዘገየ ቡልጋሪያና ሩሜኒያ ወደፊት የሕብረቱ ዓባል መሆናቸው በዚህም በዚያም የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህን የሚያረጋግጥ የሁለት ወገን ውል ከተፈረመ ቆየት ብሏል። ይሁንና የአውሮፓ ኮሚሢዮን ሁለቱ አገሮች ለውጦቻቸውን በሚገባ ካላራመዱ በመሠረቱ እንደ ዓባል መንግሥታት የሚገባቸውን ሁሉንም መብትና ገንዘብ በፊታችን ጥቅምት ወር በሚደረግ ውሣኔ ሊነፍጋቸው ይችላል። የሕብረቱ የመስፋፋት ጉዳይ ኮሜሣር ኦሊ ሬህን ስለዚሁ ሲያስረዱ፤
“የአውሮፓን ሕብረት የፊናንስ አውሎት በተመለከተ አሳሳቢ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ መላውን ዕርዳታ እናቋርጣለን። ይህ ገንዘባችንን ሃላፊነት በተመላው መንፈስ እንደምንገለገል የሚያሣይ ግልጽ ምልክት ነው።” ብለዋል። ቢዘገይ ከትናንት በስቲያ ወዲህ ገደብ የለሹ የመስፋፋት ስሜት ያለቀለት ነው የሚመስለው። እንግዲህ የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት የሚጠይቀው የራሱ ዋጋ አለው። ብራስልስም አሁን ዋጋውን እየጠየቀች ነው።

የሆነው ሆኖ ሩሜኒያና ቡልጋሪያ የለውጥ ዕርምጃቸውን አስመልክቶ ከአውሮፓ ኮሚሢዮን በኩል የቀረበውን ግምት አስደንጋጭ አድርገው አላዩትም። በተለይ ትችቱን ሻል ባለ መንገድ የተወጣችው ዕጩ አገር የሩሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሊን-ፖፔስኩ-ታሪቼያኑ ግምቱ አገራቸው ከአውሮፓው ኮሚሢዮን ያገኘችው ትልቁ የስኬት ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል። ኮሚሢዮኑ ባቀረበው ዘገባ ሩሜኒያ በእርሻ ልማቱ ዘርፍ በንጽህናና በተባይ ቁጥጥር ረገድ መሻሻል እንድታደርግ ይጠይቃል። የሕብረቱን ዕርዳታ በማከፋፈሉ በኩልም አስተማማኝ ሥርዓት እንዲኖርና የፊናንስ ተቋማት ተግባር በኮምፒዩተሮች እንዲሟላም የሚያሳስብ ነው።

ኮሚሢዮኑ ሩሜኒያ ሙስናን በመታገሉና የፍርድ ሥርዓትን በማሻሻሉ በኩል ላደረገችው ጥረት ዕውቅና ሲሰጥ ይሄው ቀጣይ እንዲሆንም ጠይቋል። የብራስልስ ባለሥልጣናት ለመላው አውሮፓውያን እጅግ ትልቅ ክብደት ባለው የአዲሱን የሕብረቱን የዳር ወሰን የወደፊት ዋስትና በተመለከተም በሩሜኒያ ጥረት መርካታቸውን ነው የጠቀሱት። ሩሜኒያ የሕብረቱ ዓባል ከሆነች ከኡክራኒያና ኮሞልዳቪያ አገሪቱን አቋርጦ በደ ማዕከላዊው አውሮፓ የሚዘልቀውን ሕገ ወጥ የሱስ ዕጽዋት፣ የጦር መሣሪያና የሰው ንግድ ከዚያው መግታቱ ግድ ነው።

ባለፈው ሣምንት ቡካሬስትን ጎብኝተው የነበሩት የጀርመን የወንጀል ምርመራ ባለሥልጣን ጌርኖት ማገር ሩሜኒያ በዚህ ጉዳይ ጥሩ ዝግጅት ማድረጓን መስክረው ነበር። የሩሜኒያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ቢሆን በዚህ ረገድ እርካታቸውን ነው የገለጹት። “ሙስናንና የድንበር ዋስትናን የሚመለከተው አንቀጽ ተነስቷል። ጥር 1. 2007 ዓ.ም. ሩሜኒያ የአውሮፓን ሕብረት መቀላቀል የምትችበት ቀን ሆኖ መቀመጡን ላሰምርበት እወዳለሁ። አማራጭ የተባለው 2008 በምንም ዓይነት መንገድ ጥያቄ ውስጥ አልገባም” ሲሉ ተናግረዋል።

የዘገባው ብያኔ ጠንከር አድርጎ የተጫነው ከሩሜኒያ ይልቅ ቡልጋሪያን ነው። የቡልጋሪያ የአውሮፓ ጉዳይ ሚኒስትር ሚግሌና ኩኔቫ የኮሚሢዮኑን አስተያየት መሟላት ያለባቸውን የቀሩትን ግዴታዎች ለመወጣት የቀረበ መርህ ነው ብለውታል። ቡልጋሪያ እንደ ሩሜኒያ ሁሉ በእርሻ ልማት ይዞታና የሕብረቱን ገንዘብ በማከፋፈሉ ጉዳይ ጉድለት ይታይባታል ተብላ በኮሚሢዮኑ ተተችታለች። የኮሚሢዮኑ ዘገባ በተለይ ሙስና፣ የተደራጀው ወንጀልና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ማጥራት ድርጊት ጨርሶ ግልጽ ሆኖ በሚታይ መጠን ትግል አልተደረገባቸውም የሚል ነው።

ሆኖም የአውሮፓ ሚኒስትሯ ሚግሌና ኩኔቫ አጠቃላዩን የወደፊቱን ሂደት የሚመለከቱት በተሥፋ ነው። ገና 227 ቀናት ይቀሩናል፤ ይሳካልናል ነው ያሉት። ሚኒስትሯ የኮሚሢዮኑን ዘገባ ትችት ቢዋሃደውም አስደንጋጭ አድርገው አልተመለከቱትም። “አንድ ቀነ-ቀጠሮ ተቀምቷል። ይሄውም ጥር 1 ቀን. 2007 ነው። ከዚህ በላይ ምን መግለጽ እንደሚቻል አላውቅም።” ብለዋል ሚኒስትሯ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ!

የአውሮፓ ሕብረት በያዘው ቀጣይ የመስፋፋት ራዕይ በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም. አሥር የምሥራቅና ደቡብ-ምሥራቅ አውሮፓ አገሮችን በመጠቅለል የዓባል መንግሥታቱን ቁጥር ከነባሩ 15 ወደ 25 ከፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው። በጊዜው ለዓባልነት በዕጩነት የቀረቡት በተለይ ፖላንድን፣ ቼክ ሬፑብሊክንና ሁንጋሪያን የመሳሰሉት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ሁኔታም ከሞላ-ጎደል የዛሬዎቹን የመሰለ ነበር። ሕብረቱ በቅድመ-ግዴታነት ያስቀመጣችውን የለውጥ መስፈርቶች አሟልተው መገኘት ነበረባቸው።
ግን ተቀባይነት ያገኙት ሁሉንም ነገር አሟልተው ነው ለማለት አይቻልም። ከዚህ አንጻር የአውሮፓ ኮሚሢዮን ከትናንት በስቲያ በሶፊያና በቡካሬስት አቅጣጫ ያስተላለፈው መልዕክቱ ወደፊት የመስፋፋቱ ሂደት ከበድ እያለ እንደሚሄድ የሚያመለክት ነው። እርግጥ እስከ 90ኛዎቹ ዓመታት ለረጅም ጊዜ በሶሻሊስት ማዕከላዊ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ሲያራምዱ በቆዩት የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ ሥርዓትን በተሟላ መልክ ማስፈኑ፤ ለዚሁ መሠረት የሆነውን የፖለቲካና ማሕበራዊ ለውጥም ማከናወኑ ጊዜን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሊጠበቅ አይገባውም።

እንዲያውም ሕብረቱን መቀላቀል የሚፈልጉት አገሮች መሠረታዊ መሥፈርቶቹን በተወሰነ ደረጃ ገቢር ካደረጉ በሚገባ ሊያሟሉት የሚችሉት ከሕብረቱ ውጭ ይልቅ ሕብረቱ ውስጥ ቢሆኑ ነው። ይህ ሃቅ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችና የባልቲክ መንግሥታት ባለፉት ዓመታት ባሳዩት ዕድገት በሚገባ ይንጸባረቃል። ስሎቬኒያ እንዲያውም ዛሬ በአስደናቂ ዕርምጃ የኤውሮ ምንዛሪ አገሮች ዓባል ለመሆን እስከመቃረብ ደርሳለች።
ቡልጋሪያና ሩሜኒያ እርግጥ እስከያዝነው ዓመት መጨረሻ የሕብረቱ ኮሚሢዮን እንደጠየቀው የለውጥ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ግን በሌላ በኩል እስካሁን ያደረጉት ዕርምጃ በታቀደው ጊዜ በዓባልነት ተቀባይነት እንዲያገኙ በቂ መሠረት የሚሆን ነው። የዓባልነቱን ጊዜ በአንድ ዓመት በማራዘም እነዚህን አገሮች ውጭ ከማቆየት በውስጡ ሆነው የጎደለውን እንዲያሟሉ ማድረጉ ይመረጣል፤ ፍቱንም ነው።