የረሐብ ዑደት፤ መንስኤና መፍትሔዉ | ዓለም | DW | 27.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የረሐብ ዑደት፤ መንስኤና መፍትሔዉ

እርዳታ ፈላጊዉ ሕዝብ ቁጥር ከዓመት አመት ለመጨመሩ ብዙዎች ብዙ ምክንያት ይሰጣሉ።አብዛኞቹ ባንዱ ይስማማሉ።ተፎጥሯዊ በሚለዉ።ቀላሉ ከተጠያቂነት የሚያድነዉ ምክንያትም ይኸዉ ነዉ።የብሪታንያዉ የባሕር ማዶ ልማት ጥናት ተቋም ባልደረባ ወይዘሮ ክሪስቲና ቤኔት ግን አብዛኞቹ የሚያዉቁትን ግን ሚሸሽጉትን መንስኤ ያክላሉ።ግጭት እና ጦርነት እያሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:55

የረሐብ ዑደት፤ መንስኤና መፍትሔዉ

አረብ፤ አረብን ይገድላል-ያስገድላልም።እየገደለ፤ እያስገደለ፤ ተራዉን ሰዉ ለገዳይ ረሐብ አሳልፎ ይሰጣል።አፍሪቃ፤ እስያም በጥቂቱ ያዉ ነዉ።አዉሮጳ-አሜሪካ ከአረብ፤ አፍሪቃ፤እስያ ገዳይ አስገዳዮች መሐል የሚታዘዘዉን መርጦ እየደገፈ ሌላዉን ይገድላል።ግድያ፤ስቃይ፤ ረሐብ የጠናበት አረብ፤አፍሪቃ፤ እስያዊ ስደተኛ አዉሮጳ እና አሜሪካ እንዳይገባ ድንበር ይዘገባተል፤ አጥር ይታጠርበታል።እሕል ዉኃ ይለምናል።የዓመታት ዑደት።ዘንድሮ ብሷል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ የ37 ሐገር ሕዝብ የምግብ እርዳታ ይፈልጋል።28ቱ አፍሪቃ ናቸዉ።አንዷ ኢትዮጵያ ናት።                        

ስሙ፤ የምግብ እጥረት፤ ረሐብ፤ጠኔ፤ ችጋር እያለ የሚቀጥል ብዙ ነዉ።ታሪኩ በተለይ ምሥራቅ ላይ ረጅም፤ መንስኤዉ፤ አወዛጋቢ መፍትሔዉ ቀላል ግን የመፍትሔ ሰጪዉን ዓለም ጥቅም የማይጠብቅ በመሆኑ የማይፈታ ወይም እንዲፈታ የማይፈለግ፤ የሚወሳሰብ ነዉ።የዘንድሮዉ ደግሞ እስከ ዛሬ ከሚታወቀዉ የከፋ፤ ብዙ ሐገራትን የነካ ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ዘንድሮ ለምግብ እጥረት የተጋለጠዉ ሕዝብ ቁጥር ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት

ወዲሕ ታይቶ አይታወቅም።ሰባ ሚሊዮን ግድም።ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አፍቃኒስታን እስከ ደቡባዊ አፍሪቃ ዚምባቡዌ፤ ከሰሜን ምዕራብ አፍሪቃ ሞሪታንያ እስከ ካሬቢክ ሔይቲ ድረስ የ37 ሐገራት ሕዝብ የዉጪ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።

የምግብ እርዳታ ፈላጊዉ ሕዝብ ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ ከዓመት አመት ለመጨመሩ ብዙዎች ብዙ ምክንያት ይሰጣሉ።አብዛኞቹ ባንዱ ይስማማሉ።የአየር ንብረት መዛባት ወይም ተፎጥሯዊ በሚለዉ።ቀላሉ ከተጠያቂነት የሚያድነዉ ምክንያትም ይኸዉ ነዉ።የብሪታንያዉ የባሕር ማዶ ልማት ጥናት ተቋም ባልደረባ ወይዘሮ ክሪስቲና ቤኔት ግን አብዛኞቹ የሚያዉቁትን ግን ሚሸሽጉትን መንስኤ ያክላሉ።ግጭት እና ጦርነት እያሉ።

                    

«በአብዛኞቹ ሐገራት ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረዉ ድርቅ፤ግጭት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት ተዳምረዉ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ብዙ ሕዝብ ለገዳይ ረሐብ ተጋልጠዋል።ለበርካታ ዓመታት በጦርነት እና ግጭት የተመሰቃቀሉትን እንደ ደቡብ ሱዳን፤ ሶማሊያ እና የመንን የመሳሰሉ ሐገራት አሉ።በነዚሕ ግጭቶች ትላልቆቹ መንግሥታት ይሳተፋሉ።»

አፍቃኒስታን፤ ሊቢያ፤

የመን፤ሶሪያ፤ ኢራቅ ረሐብተኛዉን ዓለም በቅርብ የተቀየጡ ናቸዉ።በእነዚሕ ሐገራት  ሚሊዮኖችን ያሰደደ፤ ብዙ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለ እና ለረሐብ ያጋለጠዉ የዓየር ንብረት ለዉጥ አይደለም።ወትሮም ብዙ እርሻ የለም እና የሰብል መሳት ሊባልም አይችልም።

በተለይ እንደ ኢራቅና ሊቢያ የመሳሰሉት ሐገራት ሕዝባቸዉን አቀማጥሎ የሚያኖር የተፈጥሮ ሐብት ሞልቶ የተረፋቸዉ ናቸዉ።ሕዝብን ለረሐብ ያጋለጠዉ ጦርነት መሆኑ ግልፅ ነዉ።በእነዚሕ ሐገራት  መቶ ሺዎችን ገድሎ፤ሚሊዮኖችን እያሰደ፤ ብዙ ሚሊዮኖችን ለለማኝነት በዳረገዉ ጦርነት ኃያሉ ዓለም በቀጥታ ተሳታፊ ነዉ።

ኢትዮጵያዊዉ የግብርና ኤኮኖሚስትና ደማር ኢትዮ-አፍሪቅ የተሰኘዉ የምርምርና የአማካሪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ደምስ ጫን ያለዉ እንደሚሉት ደግሞ ደቡብ ሱዳን፤ ሶማሊያ ይሁን ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ያወደመና የሚያወድመዉ ግጭትም የድሆቹ ሐገራት ፖለቲከኞች የጫሩት ብቻ አይደለም።                         

የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንደዘገበዉ በርካታ ሕዝብ የዉጪ እርዳታ ከሚፈልግባቸዉ 37 ሐገራት 28ቱ የአፍሪቃ ሐገራት ናቸዉ።ከ28ቱ ሐገራት አስራ አንዱ በግጭት የሚታመሱ ናቸዉ።የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ደግሞ የጎላ ግጭትና ጦርነት ከማይታይባቸዉ ከአስራ-ሰባቱ የአፍሪቃ ሐገራት ቢያንስ አስራ-አራቱ አንድም በአንባገነኖች የሚገዙ፤ አለያም በመልካም አስተዳደር እጦት ግራ-ቀኝ የሚላጉ ናቸዉ።በግጭት ጦርነቱ ይሁን፤ በሙስናዉ፤ በአምባገነኖቹ ሥርዓት ይሆን በመልካም አስተዳደሩ እጦት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኃያላኑ መንግሥታት እጅ አለበት።

ከ1982 ጀምሮ ሶማሊያን ባወደመዉ ጦርነት እና ግጭት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አፍሪቃ ሕብረት፤ ከአዉሮጳ ሕብረት እስከ አረብ ሊግ ተካፋዮች ናቸዉ።ቪላ ሞቃዲሾን እንኳ በቅጡ መቆጣጠር የማይችለዉን መንግስት በመደገፍ ዩንናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግስታት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለጦር መሳሪያ፤ ለወታደሮችና ለወታደራዊ አማካሪዎች ይከሰክሳሉ።

ኢትዮጵያ፤ ጅቡቲ፤ ዩጋንዳ፤ ከኬንያ፤ ብሩንዲ ሶማሊያ ዉስጥ የሚዋጋ ጦር  አስፍረዋል።ከእነዚሕ ሐገራት አብዛኞቹ  የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላትን በተለያየ ደረጃ የሚረዱ፤ ተፋላሚዎችን ለማስታረቅ እንጥራለን የሚሉም ናቸዉ።እነዚሕ ሐገራት በሙሉ ሚሊዮኖች ለምግብ

እጥረት የተጋለጡባቸዉ መሆኑ ነዉ እንቆቅልሹ።

የመንን በሚያወድመዉ ጦርነት ዋናዋ ተዋጊ-አዋጊ ሳዑዲ አረቢያ ናት።ሊቢያን ከሐገርነት ወደ ትቢያ የለወጠዉ የምዕራባዉያን ወረራ ነዉ።የኢራቅ እና የአፍቃኒስታን፤ ጥፋት በዩናይትድ ስቴትስ የተጀመረ፤ በዩናይትድ ስቴትስ እና በታዛዥ ተባባሪዎችዋ የተጠናከረ፤የቀጠለም ነዉ።

ለሶሪያ ዉድመት የሶሪያ መንግስትእና ሩሲያን መሰል ደጋፊዎቹ ተጠያቂ ከሆኑ መንግሥትን ለሚወጉት አማፁያን ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት የምዕራባዉያንና የአረብ ቱጃር መንግሥታት የማይጠየቁት ጠያቂ ስለሌለባቸዉ ብቻ ነዉ።

ከየጦርነት፤ ግጭት፤ ቁርቁሱ የተረፈዉ ሕዝብ ለሞት በሚዳርግ ረሐብ የሚጠበሰዉ በራሱ በጦርነቱ ይሁን በዓየር ንብረት መዛባት፤ ዶክተር ደምስ እንደሚሉት በሁሉም የሚሳተፈዉ ዓለም በሙሉ መፍትሔ በማፈላለጉም እኩል ተሳታፊ መሆን አለበት። 

ብሪታንያዊቷ አጥኚ ወይዘሮ ክርሲና ቤኔት እንደሚሉት ደግሞ የረሐቡን አደጋ ለማስቀረት ቁጥር አንድ መፍትሔዉ ግጭትና ጦርነቱን በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ማስወገድ ነዉ።

                                

«ከሁሉም በፊት ግጭቶችን ለማስወገድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መደረግ አለበት።በመሠረቱ አሁን ሰዎች የሚራቡት በየአካባቢያቸዉ ምግብ ሥለሌለ አይደለም።ምግብ የሚገዙበት ገንዘብ ሥለሌላቸዉ ነዉ።ሥለዚሕ ባጣዳፊ የሚያስፈልገዉ የምግብ ርዳታ ብቻ ሳይሆን የምግብ መግዢያ ገንዘብም ጭምር ነዉ።ሰዎች ከየአካባቢያቸዉ ምግብ መግዛት እንዲችሉ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።ዘላቂዉ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ፈጣኑ መፍትሔ ለረሐብ የተጋለጡት ሰዎች ገንዘብ እንዲያገኙ ማድረግ ነዉ።»

ገንዘብ የለም።ለመስጠት ያሰበም የለም።የተለመደዉን ስንዴ ለችግረኛዉ ሕዝብ ለማቅረብ እንኳ መስጠት የሚችሉት መንግሥታት ርዳታ ለመስጠት እያንገራገሩ ነዉ።ዶክተር ደምስ እንደሚሉት «ለጋሽ» የሚባለዉ ዓለም ድሮም-ሆነ ዘንድሮ ቃል ለመግባት እንጂ ቃሉን ለማክበር ሲጥር ብዙ አይታይም።ኢትዮጵያን አብነት ይጠቅሳሉ።

ከደቡብ

ሱዳን እስከ ዩክሬን፤ ከየመን እስከ አፍቃኒስታን ያሉ ሐገራትን የሚያወድመዉን ጦርነት የሚቆሰቁሰዉ ኃያል፤ ሐብታም ዓለም የየግጭት፤ ጦርነቱ፤የየረሐብ መዓቱ ሰለባ ወደ ግዛቱ እንዳይገባ ድንበሩን እያጠረ ወይም ለማጠር እየተዘጋጀ  ነዉ።ብዙዎቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት ደግሞ ስደተኛ ወደ ግዛታቸዉ እንዳይገባ ለማሳገድ ለአፍሪቃ መንግሥታት ጠቀም ያለ ገንዘብ እየቸሩ ነዉ።

አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በበኩላቸዉ ድንበር ከማጠር ዕቅዳቸዉ በተጨማሪ ከሐገራት መሐል -ደሐ ሐገሮችን፤ ከሐይማኖተኞች መሐል ሙስሊሞችን መርጠዉ ከታላቅ ሐገራቸዉ ምድር ዝር እንዳይሉ አግደዋል።ፕሬዝደንቱ በቅርቡ ያረቀቁት በጀት ከፀደቀ ደግሞ ሐብታም-ኃያሊቱ ሐገር እመራዋለሁ ለምትለዉ ዓለም እስካሁን እያቅማማች፤ እየመረጠችም የምትሰጠዉ ምፅዋት በብዙ ሚሊዮን ዶላር ይቀንሳል።

ዶክተር ደምስ እንደሚሉት ረሐብ ለዘላቂዉ ለማስወገድ አብነቱ ረሐብተኛ ሕዝብ የሚኖርባቸዉ መንግሥታት ሕዝባቸዉን እራሳቸዉ በራሳቸዉ ለመቀለብ መጣር ነዉ።

 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic