የረሃብ አደጋ በኬንያና ሶማልያ | አፍሪቃ | DW | 09.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የረሃብ አደጋ በኬንያና ሶማልያ

የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራትን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት  የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽ ትናንት ናይሮቢ ዉስጥ ከኬንያዉ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።ዘገቦች እንደጠቆሙት ሁለቱ ባለሥልጣናት  የደቡብ ሱዳንን  ጦርነት፤ ሶማሊያ ለሠፈረዉ ለአፍሪቃ ኅብረት ጦር

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:31

የረሃብ አደጋ በኬንያና ሶማልያ


«አሚሶም» ሥለሚደረገዉ ድጋፍ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪቃ ሐገራትን ሥለመታዉ ድርቅ  እና የረሃብ አደጋ ስለተደቀነበት ከ 11 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በአጠቃላይ ስለ ምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ተነጋግረዋል። ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከዉይይታቸዉ በኋላ በጋራ መግለጫ  ሰጥተዋል።  ባለፈዉ ማክሰኞ መቃዲሹን የጎበኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽ  ዓለም የረሃብ አደጋ ለተደቀነበት 6,2 ሚሊዮን የሶማልያ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ትናንት ናይሮቢን በጎበኙበት ወቅት ጥሪ አድርገዋል። ጉተረስ በናይሮቢዉ ጉብኝታቸዉ በሰሜናዊ ኬንያ በተለይ አርብቶ አደሮች በረሃብ አደጋ ክፉኛ መጠቃታቸዉን ገልፀዉ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በኬንያ በተከሰተዉ ከፍተኛ ድርቅ ረሃብ አደጋ የተደቀነበትን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድጋፍ እንዲደርግ ጥሪ አቅርበዋል።     


« በመጀመርያ ደረጃ በድርቅ አሳዛኙ ነገር ሰዎች ይሞታሉ፤ ይህ መቆም ይኖርበታል።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን ርምጃ መዉሰድ ይኖርበታል። ኬንያን እያወከ ስላለዉ ድርቅ በተመለከተ ለኬንያ መንግሥትና ሕዝብ ሙሉ ትብብርን እንደምሰጥ መግለጽ እፈልጋለሁ። የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኬንያ ያላትን ግንኙነት አይቶ ይበልጥ በመለገስ ሃገሪቱን ይደግፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በኬንያ የድርቁ ወቅት በመራዘሙና ሃገሪቱ ያላት ምንጭ በማለቁ ችግሩን በራስዋ ለመወጣት እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ተደቅኖባታል። »  
   
በኬንያ በተከሰተዉ ከፍተኛ ድርቅ በሽዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶች አልቀዋል። ከዚህ ሌላ በድርቁ ምክንያት የግጦሽ ሳር እና ዉኃን በመሳሰሉ ችግሮች ምክንያት  በአርብቶ አደሮች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ዳርጎአል።ይህንኑ ተከትሎ በማዕከላዊ ኬንያ ላይኪፒያ በሚባል አካባቢ አንድ ሰፊ እርሻና የከብት ርባታ ያለዉ እንግሊዛዊ በታጠቁ እረኞች ተገድሎአል።  
የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸዉ የተመድ ዋና ፀሐፊ ጉተረሽ የሰዉና የከብቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ስላለዉ ድርቅ አሳሳቢነት ጥሪ ማድረጋቸዉን በማመስገን ነበር ንግግር የጀመሩት።  

« ብሔራዊ ድርቅ ተብሎ በኬንያ ስለታወጀዉ ስለአሳሳቢዉ ድርቅ ጥሪ በማድረጎና መንግሥቴን ለመርዳት በመፈለጎ ላመሰግኖ እወዳለሁ። የተመ ፤  ቀይ መስቀል እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘዉ ድርቁን ለመታገል እየሰሩ በመሆናቸዉ ከልብ አድናቆታችንን እንገልፃለን።»
ባለፈዉ ወር የኬንያ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢ ነዋሪዎች  የርዳታ ምግብ ለማኅበረሰቡ አቅርቦአል። በሶማልያ አዲስ ስለተመሰረተዉ መንግሥት ሃገራቸዉ መኩራትዋን ለአንቶንዮ ጉተሪሽ  የገለፁት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፤ ኬንያ የሶማልያ ስደተኞች በጦርነት የተመሳቀለችዋን ሃገራቸዉን በመልሶ ግንባታ እንዲሳተፉ ወደ ሃገራቸዉ ቶሎ እንዲመለሱ ለማስቻል እንደምትሰራ ገልፀዋል።  

« በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸዉ እንዲመለሱና ሃገራቸዉን እንዲገነቡ መርዳት  እጅግ ጥሩ ርምጃ  ነዉ።  ነገርግን ይህ ጥረት የሚመራዉ አግባብ ባለዉ ሁኔታ በሃገር ዉስጥና በዓለም አቀፍ ሕጎች ነዉ።» በዉይይቱ ላይ የኬንያዉ መሪ የደቡብ ሱዳንን ጉዳይም አንስተዋል።  

« ደቡብ ሱዳን ብሩንዲ እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሚመለከቱ ሌሎች ክልላዊ ጉዳዮችን ለመወያየት እድል አጋጥሞናል። በእነዚህ አገሮች ዉስጥ መረጋጋት እንዲሰፍን በጋራ በመስራት ልገሳችንን እንቀጥላለን። »  በናይሮቢ በሚገኘዉ ቤተ-መንግሥት ከነበረዉ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተጠቃለለ የተመድ ዋና ፀሐፊ ጉተሪሽ  የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሚከብርበት ጊዜ ሴቶች በፖለቲካ ሂደት  በሚታገሉለት እኩልነትና ጾታዊ ጥቃት የሚገጥማቸዉን ፈታኝ ሁኔታ ለመመልከት «ማታሪ» የተሰኘዉን በናይሮቢ የሚገኝዉን የጎስቋሎች መንደር ጎብኝተዋል።  

አዜብ ታደሰ / አንድሪዉ ቫሲኬ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic