የሣራ ባርትማን ሰቆቃ | አፍሪቃ | DW | 29.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሣራ ባርትማን ሰቆቃ

ከሁለት ምእተ ዓመት በፊት ሣራ ባርትማን የምትባል ሴት አውሮጳ ውስጥ ልክ እንደ ልዩ እንስሳ አውደ-ርእይ ላይ ቀርባ ትጎበኝ ነበር። ሣራ ባርትማን እጅግ ግዙፍ ዳሌና መቀመጫ ነበራት። እናም ለየት ያለው ሰውነቷን እየተመለከቱ በስሜት ለመዋጥ በርካቶች ይጎርፉ ነበር። የሣራ ባርትማን ታሪክ ዘረኝነትን፣ ጉስቊልናን እንዲሁም ብዝበዛን ያስተጋባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58

ታሪኳ ዘረኝነትን፣ ጉስቊልናን እንዲሁም ብዝበዛን ያስተጋባል

ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በ1810፤ ሣራ ባርትማን የምትባል አፍሪቃዊት ለንደን ከተማ ገባች። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በቤት ሠራተኛነት ታገለግል የነበረችውን ይኽች ሴት ወደ አውሮጳ ይዟት የተጓዘውም ቀጣሪዋ ነበር። ወደ አውሮጳ ከቀጣሪዋ ጋር የተጓዘችው በፈቃደኝነት ይኹን በግዳጅ ግልጽ አይደለም። ለበርካታ ዓመታት ግን አውሮጳ ውስጥ ልክ እንደ ዱር እንስሳ በየጎዳናው በበርካቶች ትጎበኝ ነበር። ግዙፍ መቀመጫዋን ለመመልከት የሚጎርፈው የጎብኚ ብዛት ለአሳዳሪዋ ልዩ የገቢ ምንጭ ነበር። ሣራ ወዲያው ነበር የሆቴንቶት ቬኑስ በሚል ስያሜ ዝነኛ የኾነችው። ሆቴንቶት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚገኙ የኮይኮይ ሕዝቦች ነጮች የሰጧቸው ስያሜ ነበር፤ ቬኑስ ደግሞ የሮማውያን የፍቅር ጣዖት። 

ስለሣራ የሚያውቊ የሚናገሩት ስለ ተወዳጅ ባሕሪዋ ነው። በብዙ አውሮጳውያን ዘንድ ግን ሣራ ከእንስሳ እንደማይሻል አንዳች አስፈሪ ፍጡር ነበር የምትታየው። የደቡብ አፍሪቃ የጾታ እኩልነት ኮሚሽነሯ ፉንዲ ንዚማንዴ ሣራ ምን ያኽል ዝቅ ተደርጋ ትታይ እንደነበር ያብራራሉ።  

"ይኽም የኾነበት ዋነኛ ምክንያት አፍሪቃ በጭለማ የተዋጠች አኅጉር ናት፤ እዚያ የሚኖረውም በአጠቃላይ ከሰው ልጅ ዝቅ ያለ ነው የሚል አስተሳሰብ ስለነበረ ነው። እናም ያ እምነታቸው አፍሪቃ ውስጥ ያኔ ያገኟቸው የኮይኮይ እና የሳን ሕዝቦችን እንዴት ያደርጓቸው እንደነበር ነው።  ግንኙነቱም እጅግ የከፋ ነበር፤ በዛ ላይ ከቅኝ ግዛት ዘመን ቀደም ብሎ ሴቶች በጥቅሉ ለኃላፊነት የሚበቁ ተደርገው አይቆጠሩም ነበር።  ስለዚህም በቀላሉ ለብዝበዛ የተጋለጡ ነበሩ።" 

አውሮጳ ከደረሰች ከአምስት ዓመት በኋላ ሣራ ባርትማን ፓሪስ ውስጥ በድህነት ማቃ ሞተች። ሞታም እንኳ ሣራ ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ክብር ተነፍጋለች። ሣራ ዝንጅሮ መሰል ናት ባለው የናፖሊዮን ቦና ፓርቴ ዋና ቀዶ-ጠጋኝ ጆርጅ ኩቭየ አካሏ ተቆራርጧል። በፓሪስ ስነ-ሰብ ቤተ-መዘክር ውስጥም ለ160 ዓመታት ግድም ሰዎች ቅሪተ-ዓጽሟን፣ ጠርሙስ ውስጥ የተቀመጠ አንጎሏን እና ሐፍረተ-ሥጋዋን እየተመለከቱ ዐይናቸውን ጎልጉለዋል። በድን አካሏ ከሕዝብ እይታ ገለል የተደረገው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1974 የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገ በኋላ ነበር።

ሣራ ባርትማን ከ200 ዓመት በፊት ገደማ ይኾናል ከሞተች። ኾኖም የገጠማት እጣ በዘር መድልዎ አገዛዝ ለማቀቊ ደቡብ አፍሪቃውያን በልዩ ኹኔታ ነው የሚታየው ይላሉ ፉንዲ ንዚማንዴ።

"እሷ ኹሉ ነገራቸው ተነጥቆ በእርዛት እና በአቅመ ቢስነት የማቀቊ ሰዎች የገጠማቸው እጅግ ሰቅጣጭ በደል አይነት ተምሳሌት ናት። እናም እሷ የሰው ልጅ በዓለማችን የገጠመው መጠነ-ሰፊ በደልና ሰቆቃ ተምሳሌት ናት።"

የዘር መድልዎ ጭቆና አገዛዝ በ1994 ሲያከትም የብዙዎች ትኩረት ሣርኪይ ላይ ኾነ። በርካታ ደቡብ አፍሪቃውያን ሣራን ያሚያስታውሷት ሣርኪይ በሚለው ስያሜ ነው። ደቡብ አፍሪቃ በኔልሰን ማንዴላ ዘመነ-መንግሥት የሣራ ባርትማን ቀሪ አካል እንዲመለስ ጥረት አድርጋለች። የሣራ በድን አካል ግን በስተመጨረሻ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተመለሰው በ2002 ነው። በምሥራቅ ኬፕ አውራጃ በተወለደችበት መንደር ሀንኬይ ውስጥ የሣራ ግብዓተ-መሬት የተፈጸመው ወደ አውሮጳ ከሄደች ከሁለት ምእተ ዓመት ግድም በኋላ ነበር። ዛሬም ድረስ ግን የሣራ ባርትማን ታሪክ ለብዙዎች ትምህርት ሊኾን ይችላል። 

 

ጄን አዬንኮ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

Audios and videos on the topic