የሣምንቱ ኤኮኖሚ ነክ ዜና | ኤኮኖሚ | DW | 25.01.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሣምንቱ ኤኮኖሚ ነክ ዜና

ከሣምንቱ የኤኮኖሚ ነክ ዜና መካከል ዓበይቱ በወቅቱ እየተካሄደ ያለው የዳቮስ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ነው።

አንጌላ ሜርክል

አንጌላ ሜርክል

ዓመታዊው የ 2007 የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ስዊትዘርላንድ መዝናኛ ከተማ ዳቮስ ላይ ተከፈተ። ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የጀርመኗ መራሄ-መንግሥት ቻንስለር አንጌላ ሜርክል አገራቸው በወቅቱ የአውሮፓ ሕብረትና የ G-8 መንግሥታት ርዕስነቷ የምትከተለውን መርህ ዘርዝረዋል። አንጌላ ሜርክል እንዳሉት በአውሮፓው ሕብረት የመንፈቅ ርዕስነት ዘመናችው ተግባራችውን የሚያካሂዱት “ለአዲስ ዋስትና የበለጠ ነጻነት” በሚል መርሆ ነው።

የጀርመኗ መራሄ-መንግሥት የዓለም ንግድን በተመለከተ ሲናገሩም የግኦባላይዜሺንን ተጽዕኖ ለመታገል ሲሉ ገበዮቻቸውን የሚገድቡት አገሮች በተሳሳተ መንገድ እያመሩ ነው ብለዋል። በአንጌላ ሜርክል ዕምነት የተሰናከለውን የዓለም ንግድ ድርድር ለማነቃቃት ከሁሉም ወገን ልዝብና መኖሩ አስፈላጊ ነው። አምሥት ቀናት በሚቆየው የዳቮስ መድረክ ጉባዔ 2,500 ገደማ የሚጠጉ የፖለቲካና የንግድ ዘርፍ ተጠሪዎች ይሳተፋሉ።

የቻይና ኤኮኖሚ በተፋጠነ ዕድገት መራመዱን እንደቀጠለ ነው። የቤይጂንግ መንግሥት እንዳስታወቀው የአገሪቱ የኤኮኖሚ ውጤት ባለፈው 2006 ዓ.ም. 10,7 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል። ይህ ደግሞ ከ 1995 ወዲህ ከፍተኛው የዕድገት መጠን መሆኑ ነው። ቻይና ከአሥር በመቶ በላይ የሆነ ዕድገት ስታሣይ የአሁኑ በተከታታይ ለአራተኛ ዓመት ይሆናል።

የጀርመን ኤኮኖሚ ደግሞ በዚህ በአዲሱ ዓመት 1,7 በመቶ ዕድገት እንደሚያሣይ እየተተነበየ ነው። ሰሞኑን ይፋ የሚወጣ አንድ የመንግሥታቱ የኤኮኖሚ ዘገባ ረቂቅ እንዳመለከተው ሥራ-አጥነት በግማሽ ሚሊዮን ገደማ ይቀንሣል ተብሎ ይገመታል። ግምቱ ከጸና ካለፈው ዓመት ሥራ-አጥ ብዛት ሲነጻጸር አሥር ከመቶ መሆኑ ነው። የኤኮኖሚው ዘርፍ ተጠሪዎች በበኩላቸው ከመንግሥቱ ትንበያ የላቀ ዕድገት ይጠብቃሉ።